ተመራማሪዎች በዓይነ ቁራኛ የሚመለከቷቸው አራት አስትሮይዶች ምድርን የመምታት ዕድል ይኖራቸው ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, SPL
ብዙውን ጊዜ ስለ አስትሮይድ ሊያስቡ የሚችሉት የሳይንስ ፊልሞችን ሲመለከቱ አልያም ዜና ላይ አስትሮይድ ምድርን ሊመታ እንደሆነ ሲነገር ነው።
ነገር ግን በዓለም ላይ ትኩረታቸው በእነዚህ ግዑዝ አካላት ላይ የሆኑ በርካታ ድርጅቶች እና መከታታያ ጣቢያዎች አሉ፤ ይህም የሆነው በምክንያት ነው።
አስትሮይዶች ከ4.6 ቢሊዮን ዓመታት በፊት ምድር ያለችበት ስርዓተ ፀሀይ ሲፈጠር የተረፉ ድንጋያማ አካላት ናቸው።
ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚታወቁ አስትሮይዶች ያሉ ሲሆን አብዛኛዎቹ በማርስ እና በጁፒተር መካከል ሆኖ ፀሐይ በሚዞረው በዋናው አስትሮይድ ቀበቶ ውስጥ ይገኛሉ።
አንዳንዶቹ ወደ ምድር ቀርበው ይመጣሉ። ይህም የሕይወትን አመጣጥ እንድንረዳ ሊያግዙን እንደሚችሉ በዩናይትድ ኪንግደም ኦፕን ዩኒቨርሲቲ የፕላኔቶች እና የጠፈር ሳይንስ ፕሮፌሰር ኤመረተስ የሆኑት ሞኒካ ግሬዲ ይናገራሉ።
"ከእነዚህ ከዋክብት መካከል አንዳንዶቹ የሕይወት ግንባታ ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ ብዙ ኦርጋኒክ ውህዶች አሏቸው" ይላሉ።
"አንዱ መላምት፤ ሕይወት በምድር ላይ ሊኖር የቻለው የሕይወት ንጥረ ነገሮች በአስትሮይዶች አማካኝነት ወደ ምድር ስለመጡ ብቻ ነው" በማለት ያብራራሉ።

የፎቶው ባለመብት, NASA/Ben Smegelsky
አብዛኞቹ አስትሮይዶች ምንም ጉዳት የማያደርሱ እና ስጋት ሳያስከትሉ የሚያልፉ ቢሆኑም አንዳንዶቹ ግን ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባቸው ናቸው።
"ወደ ምድር የሚቀርቡ ቁሶችን በተመለከተ የበዛ ትኩረት አለ። ጉዳት እንደማያደርሱ ለማረጋገጥ እና አንዳንዴም ሊያስከትሉ የሚችሉትን ጉዳይ ለመተንበይ በሚያስችል ደረጃ በፀሀይ ዙሪያ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እስከሚታወቅ ድረስ በቅርበት ክትትል ይደረግባቸዋል"
"ከምድር በብዙ ርቀት ላይ ያልተለመደ አወቃቀር ያላቸውን ቁሶች እንፈልጋለን" ሲሉ በዩናይትድ ኪንግደም በኤዲንበርግ ዩኒቨርሲቲ የፊዚክስ እና የሥነ ፈለክ ትምህርት ቤት የምርምር ባልደረባ የሆኑት አጋታ ሮዝክ ይናገራሉ።
አስትሮይዶች በግዝፈታቸው ሲመደቡ፤ ትላልቆቹ አስትሮይዶች የሚፈጥሩት ስጋት እምብዛም ነው። ሮዝክ "የት እንዳሉ እና ወዴት እንደሚሄዱ በትክክል እናውቃለን" በማለት ምክንያቱን ያብራራሉ።
"እንቅስቃሴያቸውን የሚቆጣጠሩትን ሕጎች በሚገባ ተረድተናል፤ እንዲሁም ያልተለመዱ ነገሮች ሲፈጠሩ እነሱን በማጥናት ይበልጥ ልንረዳቸው ችለናል" ይላሉ።
በጸሀይ ዙሪያ የሚያደርጉት ዙረት እስከሚታወቅ ድረስ ስጋት የመፍጠር ዕድል ያላቸው ትናንሾቹ፣ ያልተለዩት [አስትሮይዶች] ናቸው" በማለት ያክላሉ።
እንደ ተመራማሪዎች ገለጻ ከሆነ፤ ከዋና ዋና አስትሮይዶች መካከል በአሁኑ ጊዜ ክትትል እየተደረገባቸው ያሉት ሦስቱ ናቸው።
አንዲት ተጨማሪ አስትሮይድ ደግሞ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ናሳ ጥናት ሊያደርግበት ተልዕኮ ወስዷል።
1. አፖፊስ

የፎቶው ባለመብት, NASA
በግብፅ የሁከት እና የጥፋት አምላክ ስም የተሰየመው አፖፊስ፤ የተገኘው እ.አ.አ በ2004 ነበር።
ይህ አስትሮይድ ምድርን የመምታት አነስተኛ ዕድል ያለው ይመስል ነበር።
ነገር ግን ናሳ በኋላ ላይ "አፖፊስ ቢያንስ ለ100 ዓመታት ምድርን የመምታት ዕድል እንደሌለ እርግጠኛ" መሆኑን አስታውቋል።
"በአሁኑ ወቅት በሚያዝያ 5፤ 2021 ዓ.ም. ምድርን በሠላም እንደሚያልፍ እናውቃለን" ሲሉ ሮዝክ ተናግረዋል።
"ከተገኘበት ጊዜ አንስቶ ሰፊ የምድር ላይ የክትትል ዘመቻዎች ተካሂደውበታል። ጂኦስቴሽነሪ ሳተላይቶች ባሉበት ርቀት አቅራቢያ፤ በቅርብ እንቅስቃሴ ያደርጋል። ለምድር ያለው ቅርበት አስትሮይዱ እንዲለጠጥ እና ቅርጹን እንዲለውጥ ሊያደርገው ይችላል ብለን እናስባለን።"
ናሳ እንደሚገልጸው፤ የምድር ስበት አፖፊስ በፀሀይ ዙሪያ ያለውን እንቅስቃሴ እንዲቀይር የሚያደርግ እና በአስትሮይዱ ላይ አንዳንድ ትናንሽ የመሬት መንሸራተቶችን እንዲከሰት የሚያደርግ ስበት ይፈጥራል።
የአፖፊስ አማካይ ዲያሜትር 340 ሜትር ሲሆን ይህም የሦስት የእግር ኳስ ሜዳዎች ርዝመትን ያክላል።
አስትሮይዱ ከምድር ገጽ በ32,000 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያልፋል። ይህ ርቀት በዓይን እንዲታይ ያደርገዋል።
2. 2024 ዋይአር4

የፎቶው ባለመብት, ATLAS
ይህ አስትሮይድ መጠኑ ከ53 እስከ 67 ሜትር እንደሆነ ይገመታል። ግዝፈቱ ባለ 15 ወለል ሕንጻን ይስተካከላል እንደማለት ነው።
እ.አ.አ በ2032 አስትሮይዱ 2024 ዋይአር4 ምድርን ሊመታ የሚችልበት አነስተኛ ዕድል እንዳለ በቅርቡ መታወቁን ተከትሎ በዓለም ዙሪያ ዜና አርዕስት ሆኖ ነበር።
ተመራማሪዎች ምድርን ሊመታ የሚችልበት ዕድል አንድ 32ተኛ እንደሆነም ጭምር ገምተው የነበረ ሲሆን በኋላ ግን ይህ ግምት በናሳ ውድቅ ተደርጓል።
የኦፕን ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሩ ግሬዲ፤ "ከምድር ጋር ሊጋጩ የሚችሉ አስትሮይዶችን ከመመልከት ጋር የሚያያዘው አንዱ ፈተና ይህ የመሆን ዕድሉ ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል መወሰን ነው" ይላሉ።
"በፀሀይ ዙሪያ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በደንብ ለማጥራት የምናደርገው ክትትል መቀጠል አለብን" በማለት ያክላሉ።
2024 ዋይአር4 ጨረቃን የመምታት ዕድሉ አሁንም 3.8 በመቶ ነው። ግን ግጭቱ ቢፈጠርም እንኳን የጨረቃን እንቅስቃሴ እንደማይለውጥ ናሳ አስታውቋል።
3. ዲዲሞስ እና ዲሞርፈስ

የፎቶው ባለመብት, NASA/Johns Hopkins APL/Steve Gribben
ዲዲሞስ፤ በግሪክ መንታ የሚል ትርጉም ያለው ስያሜ የተሰጠው አስትሮይድ ነው። ዲሞርፈስ እርሱን የሚሽከረከር ትንሽ ጨረቃ ነው።
ሁለቱም ቢሆኑ ለምድር ስጋት ይፈጥራሉ ተብሎ አይታሰብም። ይሁን እንጂ የሚያልፉት በአንጻራዊነት ከምድር ቅርብ በሆነ ርቀት ላይ ነው።
ሁለቱ አካላት እ.አ.አ በ2022 'ደብል አስትሮይድ ሪዳይሬክሽን ቴስት' የተባለ የናሳ ሙከራ ዒላማ ነበሩ። በዚህ ሙከራ ሰው አልባ መንኮራኩር ተልኮ ከዲሞርፎስ ጋር እንዲጋጭ የተደረገ ሲሆን በዚህ ሂደት መንኮራኩሩ ወድሟል።
የሙከራው ዓላማው ምድርን ሊያሰጉ የሚችሉ የጠፈር ድንጋዮችን በደህና መንገድ ማስወገድ ይቻል እንደሆነ ለመፈተሽ ነበር።
ዲሞርፎስ እና ዲዲሞስ ለዚህ ሙከራ የተመረጡት በጥንቃቄ ነበር። ከሙከራው ሁለቱም አካላት ከመሬት ጋር የሚተላለፉበት መንገድ ላይ አልነበሩም። ትንሽ ለውጥ ማድረግም በሚኖራቸው የምህዋር ግንኙነት ላይ አደጋን አይጨምርም።
"በተደረገው የመጀመሪያ የጠፈር መከላከያ ተግባራዊ ሙከራ ተልዕኮው ዲሞርፈስ በዲዲሞስ ዙሪያ ያለው እሽክርክሮሽ በመቀየር በጨረቃ ዲሞርፈስ ላይ ተጽእኖ አድርጓል" ይላል ሮዝክ።
"ይህ ለውጥ በዋነኛነት የተለካው በመሬት ላይ የተመሰረቱ ምልከታዎችን በመጠቀም ነው።
የመጋጨቱን ውጤት ለመመርመር የሚላከው የሄራ ተልዕኮ በሚቀጥለው ዓመት ከመጓዙ በፊት ይህንን ጉዳይ መከታተል እንቀጥላለን።"
4. ሳይኪ

የፎቶው ባለመብት, NASA
ናሳ፤ "በዋናው የአስትሮይድ ቀበቶ ውስጥ ከሚገኙ በጣም አስገራሚ ከሆኑት ነገሮች አንዱ" በማለት የሚገልጸው ሳይኪ የተገኘው እ.አ.አ በ1852 ነበር። ስያሜው የተሰጠውም ከግሪክ የነፍስ አምላክ ስም ነው።
ሳይኪ ከእኛ በጣም የራቀ ነው ሲሆን በጁፒተር እና በማርስ መካከል ሆኖ በፀሐይ ዙሪያ ይሽከረከራል። የተሰራውም ከብረት እና ከድንጋይ እንደሆነ ይታመናል።
ተመራማሪዎች አብዛኛው ብረት የተገኘው ፕላኔቶች የሚፈጠሩበት ስብርባሪ ከሚገኝበት ከፕላኔቴሲማል እምብርት እንደሆነ ያስባሉ።
ሳይኪን ማጥናት፤ የምድር እና የሌሎች ፕላኔቶች እምብርት እንዴት እንደተፈጠረ ሊገልጥ እንደሚችልም ያምናሉ።
በ2023 ናሳ የአስትሮይዱን ካርታ ለማስፈር እና ለማጥናት ተልዕኮ ጀምሯል።
አዳዲስ ግኝቶች

የፎቶው ባለመብት, NSF-DOE Vera C. Rubin Observatory
በዚህ ወር መጀመሪያ የቬራ ሩቢን ኦብዘርቫቶሪ የተባለው መከታተያ ጣቢያ አዲስ ቴሌስኮፕ በመጠቀም በ10 ሰዓታት ውስጥ ብቻ ከ 2,000 በላይ አዳዲስ አስትሮይዶችን እና ሰባት ለምድር የቀረቡ የጠፈር አካላትን እንዳገኘ አስታውቋል።
በምድር እና በጠፈር ላይ ያሉ ሁሉም ኦብዘርቫቶሪዎች በየዓመቱ በግምት 20,000 አስትሮይዶችን ያገኛሉ።
ፕሮፌሰር ግሬዲ፤ "የሌሊቱን ሰማይ በሙሉ በካርታ ለመቅረጽ ከፈለግህ በጣም በጣም ሰፊ የሆነ የመመልከቻ መስክ ሊኖርህ ይገባል። ቬራ ሩቢን ኦብሰርቫቶሪ ውስጥ የሚገኘው ቴሌስኮፕም ይህ ያለው ነው" ብለዋል።
ኦብዘርቫቶሪው፤ በፕሮጀክቱ የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አዳዲስ አስትሮይድዎችን አገኛለሁ ብሎ ይጠብቃል። ይህም ተመራማሪዎች ብዙ ተጨማሪ አስትሮይድዎችን እንዲመለከቱ እና ስለ የፀሀይ ስርዓታችን ተጨማሪ ፍንጮችን እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።















