ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጥቁር አሜሪካውያን ለሃሪ እና ሜጋን ፊልም ምን አይነት ምላሽ ሰጡ?
በቅርቡ በኔትፍሊክስ ለዕይታ የበቃው የሃሪ እና የሜጋን ታሪክ በርካታ አስተያየቶችን እያስተናገደ ነው።
ተከታታይ ፊልሙ ዘረኝነት፣ ቅኝ ግዛት፣ የነጭ የበላይነት፣ ታሪካዊ ኢ-ፍትሃዊነት፣ የሚዲያ አሉታዊ ገጽታ፤ ሌላም ሌላም ታይቶበታል።
ብሪንዲስ ሮበርትስ ይህንን ፊልም በእንባ ተሞልታ ነው ያየችው።
ልዕልት ዲያና ከተቀላቀለችበት ጀምሮ የዩናይትድ ኪንግደም የንጉሣውያን ቤተሰብ ሁኔታን በጥብቅ ተከታትላለች።
በፊልሙም ላይ ቤተሰቡ በማይታመኑ ወሬዎች ሲታመስ፣ የልዑል ሃሪ እና የወንድሙ ልዑል ዊልያም ግንኙነት መሻከር አሳዝኗታል።
ከዚሁ ሁሉ በላይ ግን ጥቁሮች ጭቆናን በሚያስተናግዱበት ደቡባዊ የአሜሪካ ግዛት ውስጥ ያደገችው የ65 ዓመቷ ጥቁር፣ ፊልሙ በዘር እና ዘረኝነት ላይ ግልጽ ውይይት እንዲኖር ማድረጉን እንደ በጎ ያየችው ነገር ነው።
በሜጋን የራሴን ተሞክሮ ማየት ችያለሁ ትላለች።
“ተናዳጅ ጥቁር ሴት ተብያለሁ። እንዲሁም ጥቁር ሴቶችን ለማዋረድ እና ለማሳነስ የሚደረጉ ዘለፋዎችን እና ስሞችን ሰምቻለሁ። እናም ሜጋን በተመሳሳይ የደረሰባትን አይቼ አዘንኩ” ትላለች።
ስድስት ተከታታይ ክፍሎች ባሉት በዚህ ፊልም ዘር ዋነኛ ማዕከላዊ ጉዳይ ነው።
ፊልሙ ከዚህ ቀደም በኦፕራ ዊንፍሬይ ቃለ መጠይቅ ከቀረበው ይዘት ውጪ ብዙም አዲስ ነገር አላካተተም።
ሜጋን ከኦፕራ ጋር በነበራት ቆይታ ስማቸው ያልተጠቀሰ የንጉሣዊ ቤተሰብ አባል የልጃቸው ቆዳ ምን ያህል “ሊጠቁር ይችላል” የሚል አስተያየት መስጠታቸውን ጠቅሳለች።
በዚህ ፊልም ላይ ሜጋን እና ሃሪ ከጥቁር እና ከነጭ ቤተሰቦች መወለድ ላላሰለሰ የሚዲያ ዘመቻ፣ የዘረኝነት ጥቃት እና ዘለፋ ምክንያት እንደሆነች ይናገራሉ።
ብሪንድስ፣ ሜጋን የደረሰባትን በቅርበት ተከታትላለች። ሜጋን ከሠርጓ በኋላ፣ በአውሮፓውያኑ 2018 በዘረኞች ስትሰደብና ስትዘለፍ ብሪንድስ በትዊተር ‘ሰሴክስ ስኳድ’ በሚል ሃሽታግ ከጎኗ ቆማ ነበር።
ይህንን ማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻም በዋነኝነት ጥቁር ሰዎች የደገፉ ሲሆን፤ በዚህም ለሃሪ እና ለሜጋንም ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል።
'የዘረኝነት ጥቃት በኢንተርኔት'
ልጃቸው አርቺ የመወለዱ ዜናን አስመልክቶ የቀድሞ የቢቢሲ ጋዜጠኛ የነበረው ዳኒ ቤከር፣ ጥንዶቹ የህጻን ዝንጀሮ እጅ ይዘው የሚያሳይ ፎቶ በትዊተር ለጠፈ። ዝንጆሮው ህፃኑን አርቺን ለማመላከት የተደረገ ነበር።
“በፎቶው ላይም ንጉሣዊው ህጻን ከሆስፒታል ሲወጣ የሚል ጽሁፍ ነበር። ይህንን ነበር መጀመሪያ ያየሁት” ብሏል ልዑል ሃሪ።
ዳኒ ቤከር ይቅርታ ከጠየቀ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከሥራው ተባሯል።
አሜሪካዊው የቴክኖሎጂ ሥራ ፈጣሪ ክርስቶፈር ቡዚ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የሃሪ እና የሜጋን ልጆችን ከጦጣዎች ጋር ማነጻጸር፣ እንዲሁም ሜጋንን ለመግለጽ ጥቁርነትን ባወረደ መልኩ ስያሜ የሆነው ‘ኒገር’ የሚለው ቃል በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ መዋሉን ተገንዝቧል።
ክርስቶፈር ኩባንያው ቦት ሴንትኖል በትዊተ፣ በሜጋን ላይ ለደረሱት ጥላቻ የተሞላባቸው ይዘቶች ምንጭ የሆኑት ጥቂት ቁጥር ያላቸው፣ ነገር ግን ከፍተኛ ተጽእኖ መፍጠር የሚችሉ አካውንቶች መሆናቸውን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ በፊልሙ ላይ ተካቷል።
“በሆነ ምክንያት እሷን የማይወዱ ሰዎች የሉም እያልኩ አይደለም። ነገር ግን የእነዚህን የጥላቻ መልዕክቶች ሰፋ ባለ መልኩ ስንመለከታቸው እና አካውንቶቹንም ስናይ በዘር ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ የሚጠቁም ነው” ይላል።
የንጉሣዊ ቤተሰቦች ጉዳይ ተንታኝ የሆነችው አሜሪካዊቷ አርኤስ ሎኬ በበኩሏ በሜጋን ላይ የደረሰው “ሚሶጊኖይር” ነው ትላለች፤ ይህም ማለት ሰዎች ጥቁር እና ሴት ስለሆኑ ብቻ የሚደርስ ጥላቻ እንደሆነም ትገልጻለች።
“ዩናይትድ ኪንግደም ልክ እንደተቀረው ዓለም ሁሉ ራሳቸውን እነዚህን ከተለያየ ሕይወት የመጡ ዘመናዊ ጥንዶች እንደተቀበሉ ማየት ይፈልጋሉ። ነገር ግን ሜጋን ያጋጠማት አሉታዊ ምላሽ እና የዘረኝነት ጥቃት ምን ያህል ማኅበረሰቡ ሥራ መስራት እንዳለበት የሚያሳይ ነው” ትላለች።
ይህም “ራሳችንን የምንመለከትበት እና በትክክለኛ ማንነታችን መካከል የሚደረግ ጦርነት መሆኑን ፍንትው አድርጎ ያሳየ ነው” በማለት ታስረዳለች።
በርካታ ጥቁር አሜሪካውያን ሃሪ እና ሜጋን ስለ ዘረኝነት መናገራቸው እንዲሁም ፊልሙ ባርነት እና ቅኝ ግዛት ስላደረሰባቸው ጫናዎች ማሳየቱን እንደ በጎ ቢመለከቱትም፤ ሜጋን በዩናይትድ ኪንግደም ብቻ በጥቁርነቷ ስለደረሰባት መድልዎ መናገሯ ትችት እንዲገጥማት ምክንያት ሆኗል።
ሜጋን ከጥቁር እና ከነጭ መወለዷን ገልጻ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እስክትደርስ መድልዎ ተፈጽሞባት እንደማያውቅ ወይም እንደ ጥቁር ሴት እንዳልታየች አንድምታ ባለው መልኩ ተናግራለች።
ስታድግ በርካታ ጥቁር ቤተሰቦች እንደሚያደርጉት እናቷ ስለ ዘረኝነት፣ መድልዎ እንዲሁም ጥቁሮች በአሜሪካ ስለሚገጥማቸው ፈተና አልነገረችኝም ብላለች።
ይህንንም በማለቷ በአንዳንዶች ወቀሳ እንዲደርስባት ምክንያት ሆኗል።
“በጥቁር እናት በአሜሪካ ውስጥ አድርጋ ወላጆቿ ስለ ጥቁርነት አልነገሩኝም ማለት አልገባኝም። እንደ ጥቁር ሴት እንድናያት ትፈልጋለች፣ ነገር ግን ይሄ ከእኛ አውነታ ጋር ይጻረራል” ብሏል አንድ የትዊተር ተጠቃሚ።
ሌሎች ደግሞ ሜጋን ሃሪን ከማግባቷ በፊት ራሷን እንደ ጥቁር ትመለከት ወይንም ትገልጽ ነበር ወይ? የሚለው እንዲብራራላቸው ጠይቀዋል።
ብሪንድስ በበኩሏ በአሜሪካ ውስጥ በጥቁሮች መካከል የቆዳ ቀለም መለያየት እና የሚሰጠው ደረጃን በምክንያትነት ገልጻ፣ ሜጋን ቀይ የቆዳ ቀለም ስላላት የተለየ የሕይወት ልምድ እንዳላት በመጥቀስ መውቀስ እንደማትፈልግ አስረድታለች።
“ተፈቅዶልሻል ማለት ተቀብለውሻል ማለት እንዳልሆነ ሜጋን የተገነዘበችበት ወቅት ነው” በማለት አንድ ግለሰብ ትዊት አድርገዋል።
“በርካታ ጥቁሮች ያጋጠማቸው ጉዳይ ነው። በነጮች ተቀባይነትን ለማግኘት የሚደርስባቸውን ስቃይና ውርደት እንዴት ያነጻጽሩታል የሚለው ነው።”
ለብሪንድስ በሃሪ እና በሜጋን ተከታታይ ፊልም ራሳቸው በአንደበታቸው ስለተፈጠሩት ጉዳዮች መስማቷ ስሜታዊ አድርጎኛል ትላለች። በተለይም ንጉሣዊ ቤተሰቡ ይህንን ዕድል ማስመለጡ።
“ተቋሙ ልዑል ሃሪ እና ሜጋን የነበራቸውን ከፍተኛ ስፍራ አልተረዳውም። እነዚህ ጥንዶች የብሪታንያን ተራውን ህዝብ እንዲሁም ሌሎቻችን ልንደርስባቸው የማንችልባቸውን የኮመንዌልዝ አገራት ዜጎች መልካም ግንኙነት መፍጠር ይችላሉ። ይህ ዕድል ማምለጡ በጣም አሳዛኝ ነው” ብላለች ብሪንድስ።