ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አማርኛ የሚኮላተፉ፣ ነፍሰ ገዳይ ወታደሮች....-ሬድ ሲ ዳይቪንግ ሪዞርት ፊልም
አንድ የማይታወቅ መንደር- እዚህ እዛ ተፈራርቀው በተመሰረቱ የሳር ጎጆዎችና በድንጋይ በተሰሩት ህድሞዎች መካከል የጥይት ድምፅ ያንባርቃል። አቧራ በለበሰው መንገድ በፒክ አፕ መኪና የተጫኑና ኤኬ 47 ጠመንጃ ያቀባበሉ ወታደሮች መንገዱን እየሰነጠቁ ይጓዛሉ።
የቆሸሸ ነጭ ጉርድ ቲሸርት የለበሰና ጡንቻው ፈርጠም ያለ ወታደር፣ ባንዳና ጭንቅላታቸው ላይ ያሰሩ፣ ጥቁር መነፅር ሻጥ ያደረጉ ወታደሮች በቤቶቹ ላይ ጥይት ማዝነብ ጀመሩ፤ ቦምብ በመወርወርም ቤቶቹን እንዳልነበር አወደሟቸው።
በሚጋዩ ቤቶችና በሚጮሁ ድምፆች መሃል ላይም የአንድ ግለሰብ ድምፅ ይሰማል 'ማይ ካንትሪ ኢዝ ብሮክን፤ ዴዝ ኢዝ ስፕሬዲንግ፤ ዘ ኒው ገቨርንመንት ኢዝ ዌጂንግ ዋር ኤጌይንስት ዘ ሬብልስ' (ሃገሬ ፍርስርሷ ወጥቷል፤ ሞት በዝቷል። አዲሱ መንግሥት በአማፂያን ላይ ጦርነትን አውጇል) በማለት እየሆነ ያለውን ይተርካል።
ለአባቶቻቸው ቃል የተገባላቸውን ትንቢት ለማስፈፀም ለ2700 አመታት ያህል የጠበቋትን የቅድስቲቷና የተስፋይቷ ምድር ጉዞም እንደጀመሩ ይኸው ድምፅ ያበስራል።
ይህ በቅርቡ ኔትፍሊክስ ላይ ለእይታ ከበቃው 'ዘ ሬድ ሲ ዳይቪንግ ሪዞርት' መግቢያ የተቀነጨበ ነው። በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተው ይህ ፊልም በ1970ዎቹ ሞሳድ ቤተ እስራኤላውያንን ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል ለመውሰድ የነበረውን አደገኛና መስዋእት የተሞላበት ተልዕኮ የሚያሳይ ነው።
ኦፐሬሽን ብራዘርስ (ትዕይንተ ብራዘርስ) በሚል የሚጠራው በዚህ ሚስጥራዊ ተልእኮ ሞሳድ ሃሳዊውን 'አሮስ' ሪዞርት ከሱዳን መንግሥት በሊዝ ይገዛል። ሪዞርቱን ለስለላ ስራው እንደ ሽፋን በመጠቀም ቤተ እስራኤላውያንን በመርከብ ነዳጅ አስመስሎ በማውጣት በሲናይ በረሃ በኩል በጀልባ ለማስገባት የተደረገ ተልእኮ ነው።
በእስራኤላዊው ጌዴዮን ራፍ ተደርሶ ዳይሬክት የተደረገው ይህ ፊልም ላይ የቤተ እስራኤላውያንን እንቅስቃሴ ሲያስተባብር የነበረው ፈረደ አክሎም በአፍሪካዊ አሜሪካዊው ሚካኤል ኬኔዝ ዊልያምስ ከበደ ቢምሮ በሚል ገፀ ባህርይ ተወክሏል።
በዚህ ፊልም ሌላኛው አፍሪካ አሜሪካዊ ክሪስ ቾክ ቤተ እስራኤላውያንን ወክለው ተውነዋል። ኢትዮጵያን አስመስሎ ናሚቢያ በተቀረፀው በዚህ ፊልምና በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያኖች (ቤተ እስራኤላውያኖችን) ለመውሰድ በተደረገው ትግል የኢትዮጵያውያን ቁጥር ከእጅ ጣቶች አይበልጥም።
"ደም የጠማቸው፣ ነፍሰ ገዳይ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች"
ፊልሙ ሲጀምር ኢትዮጵያ የሚል ፅሁፍ በመኖሩ ብቻ እንጂ ይህቺ የጦር አውድማ የምትመስለው መንደር አካባቢ የት እንደሆነም ለመገመት ይከብዳል።
አማፂያን ተብለው እርስ በርስ የሚዋጉትም ሆነ ወታደሮቹ እነማን እንደሆኑ ምንም አይነት ፍንጭ ስለማይሰጥ ፊልሙን ለተመለከቱት ኢትዮጵያውያን ግራ አጋብቷል።
በተለይም ፊልሙ ሲጀምር አካባቢ ደም የጠማቸው አውሬዎች ተደርገው የተሳሉት ወታደሮች ከአለባበሳቸው ጀምሮ ፤ የሚጠቀሙት አማርኛ ኮልታፋ ከመሆኑ አንፃር ኢትዮጵያ በወቅቱ የነበሯት ወታደሮች ምን አይነት ናቸው? የሚል ጥያቄንና ትችቶችንም በማስተናገድ ላይ ነው።
ፊልሙ ላይ የርስ በርስ ጦርነት እንደነበር ዋነኛው ገፀ ባህርይ ከሚተርከው ውጭ ምንም የሚያሳይ ነገር የሌለ ሲሆን ቤተ እስራኤላውያን ከኢትዮጵያ ወታደሮች ለማምለጥ የነበረውን ሞት ቀረሽ ትንቅንቅና በየቦታው ወታደሮች ባዩዋቸው ቁጥር አፈሙዝ መደገናቸው ሲታይ፤ በጊዜው የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት በቤተ እስራኤላውያን ላይ ጦርነት አውጆ ነበር ወይ የሚል ጥያቄም አጭሯል።
በተለይም አንድ አስር አመት የማይሞላውን ህፃን የሚያሳድዱበት ቦታ ስራቸው መግደል ብቻ እንደነበር አሳይ ነው የሚሉም አልታጡም። በሰብሎች መሃል ሲጫወት የነበረው ህፃን ልጅ ተኩሱን ሲሰማ እግሬ አውጭኝ ብሎ መንገዱን ሰንጥቆ ይሮጣል።
የወታደሮቹም መኪኖች ሰብሉን እየጨፈላለቁ ተከተሉት። እሱ ልቡ እስክትሰነጠቅ ቢሮጥም ከሚከተሉት መኪኖች ማምለጥ አልቻለም። ወታደሮቹ ህፃኑን ሲያዩት ነፍሱ ከስጋው ልትላቀቅ በሚመስል ሁኔታ ደንግጦ ያያቸዋል።
ባንዳና ጭንቅላቱ ላይ አስሮ መነፅር ያደረገው ወታደር 'የማሽን' ጠመንጃውን ያንደቀድቀው ጀመር። ፊልሙ ላይ ዋነኛ ገፃባህርይ ሆኖ የሚጫወተው ታዋቂው የሆሊውድ ተዋናይ ክሪስ ኤቫንስ በርካታ ነፍስ ያለው በሚመስል ሁኔታ ከሞት መንጋጋ ፈልቅቆ ልጁን አፈፍ አድርጎ ሮጠ።
በመኪና ከሚከተሉት ወታደሮች በተጨማሪ ቆንጨራ ያነገቡና የእንስሳት ቀንድ አንገታቸው ላይ ያሰሩት ወታደሮች ደም እንደጠማት ውሻ እያበዱና እየተኮሱ ቢከተሏቸውም አልደረሱባቸውም።
ወታደሮቹንም ካመለጡ በኋላም ነጮቹ የሞሳድ ሰራተኞች እንደ 'ሙሴ' እየመሯቸው ሱዳን የሚገኘው ጌዳሬፍ መጠለያ ሲደርሱ ይታያሉ። ከዚያ በኋላም ቤተ እስራኤላውያኖቹ ብዙ የማይታዩ ሲሆን፤ 2፡05 ርዝማኔ ባለው ፊልም ላይ የሞሳድ ጀብደኝነትና፣ የሲአይኤ ሚናን በከፍተኛ ሁኔታ በማጉላት ፊልሙ ይጠናቀቃል።
በፊልሙ ላይ ቤተ እስራኤላውያን ተብለው የተሳሉት ስደተኞች ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው የሚናገሩት ቃላቶች የተመጠኑ፤ አካባቢውን ቢያውቁትም የሚመሩት በነጮቹ እንዲሁም ባህላቸው፣ አለባበሳቸው፣ ፍቅራቸው ምንም አይነት መስተጋብራቸው አይታይም። ቤተ እስራኤላውያኖቹ ወደዚህ ኑ ሲባሉ ከመምጣት፣ ተኙ፣ ብሉ፣ ጠጡ ሲባሉ ትእዛአዝ ከመቀበል በስተቀር ምንም አይነት አስተዋፅኦ እንዳልነበራቸው ፊልሙ ያሳያል።
በተለያዬ አጋጣሚም በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን አደጋ ተጋርጦባቸው አንድ ነጭ ሲያድናቸው ማዬት ተአማኒነቱ ላይ ጥያቄን የፈጠረባቸው ጥቂቶች አይደሉም።
በድርጊት የተሞላውን ፊልም ለተመለከቱት አብዛኛው ኢትዮጵያዊያውያን ሊዋጥላቸው አልቻለም፤ 'ኢትዮጵያን የጦር አውድማ አድርጎ ከመሳል ጀምሮ፣ የኢትዮጵያዊ ቤተ እስራኤላውያን ታሪክ ከመሆኑ አንፃር ኢትዮጵያውያንን አለማሳተፉ፣ አማርኛ በትክክል መናገር የማይችሉና አማርኛ እየተኮላተፉ የሚያወሩበት ገፀ ባህርያን መሞላቱ፣ የታሪክ ግድፈት እንዲሁም በነጭ አዳኝነት (ዋይት ሴቪየር)ና የኢትዮጵያንም ሆነ የአፍሪካን የተለመደውን ጨለምተኛ ታሪክ አነጋገር ዘዬ የተከተለ በሚል ትችቶች አየቀረቡበት ነው።
ፊልሙን ከተመለከቱት አንደኛው ሰሚር አሊ በተደጋጋሚ ሆሊውዶች ራሳቸውን የሚክቡበትና፤ ታሪኩንና እውነታውን የካደ ነው በማለት ፊልሙን ይተቸዋል። የአምስት አመት ልጅ ይመስል አማርኛን በቅጡ የሚናገሩ ተዋንያን መሳተፍ ለሰሚር የሚዋጥ አይደለም።
የማህበረሰቡ አኗኗር፣ ታሪክ ላይ ምንም አይነት ጥናት ባለማድረጉም ቤተ እስራኤላውያን 'ሆቴል ሩዋንዳ' ከሚመስል ጭፍጨፋ እንደወጡ ተደርጎ ነው የተሳለው ይላል።
"ጀብደኛና ግድየለሽ" ብሎ በጠራው ፊልም ላይ በተለይ ኢትዮጵያውያን የተወከሉበት መንገድንም ይጠይቃል።
"ያው ለነሱ አፍሪካ ሲባል አንድ አይነትና እንደ አንድ አገር ነው የሚቆጥሩት፤ የተለያዬ ባህል፣ የፊት ገፅታ፣ቋንቋ፣ እምነት ያለ አይመስላቸውም። ሁሉንም ሃገራት በአህጉሯ አፍሪካ ነው እንጂ በዚህም አጋጣሚ የኢትዮጵያ ስም ሲጠራ አይሰማም። ዋነኛ ባለታሪኮቹን የሉም ማለት ይቻላል። ዝም ብለው እንዳልባሌ ነገር ነው የተቆጠሩት፤ እንደ እቃ አውጥተው አንጠልጥለው ያወጧቸው ነው የሚመስለው"በማለት ወቀሳውን ያቀርባል።
ማን ያውራ የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ?
በእውነቱ ቤተ እስራኤላውያን በጉዟቸው ላይ አስተዋፅኦ አልነበራቸውም? የብዙዎች ጥያቄ ነው።
"በባቢሎን ተራራዎች ስር ተቀምጠን ፅዮንን ባሰብናት ጊዜ አለቀስን፤ ፅዮን ሆይ ቀኜ ትርሳሽ ምላሴም ከትናጋዬ ጋር ይጣበቅ እየሩሳሌምን ከፍ ከፍ ባላደርጋት።" ለ2700 አመታት ያሀል ቅዲስቲቷንና የተስፋይቱን ምድር እውን መሆን ሲጠብቁ የነበሩት የቤተ እስራኤላውያን በልባቸው የተታተመ ቃል ነው።
በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር 1948 የእስራኤል መንግሥት መመስረትን ተከትሎ የተለያዬ ሃገራት ነዋሪ የነበሩ እስራኤላውያንን ተሳባሰቡ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ ቤተ እስራኤላውያንም በልባቸው ወደሰነቋት እየሩሳሌም ለመሄድ የቆረጡት።
አቶ አዳነ ታደሰ በ1976 ዓ.ም ከጎንደር ፀዳ የምትባል አካባቢ ተነስተው መሬቷን ትተው ፊታቸውን ሳያዞሩ ጉዟቸውን ሌት ተቀን ወደሚያልሟት እስራኤል አደረጉ።
በወቅቱ 16 አመታቸው የነበሩት አቶ አዳነ 'ተነቅለው' በሚባል ሁኔታ ወላጆቻቸው፣ ወንድሞችና እህቶቻቸው፣ አጎታቸውና አክስቶቻው ሆነው ከሌሎች ቤተ እስራኤላውያን ጋር ሆነው ጓዜን ፣ማቄን ሳይሉ ረዥሙን ጉዟቸውን ወደ ሱዳን ያደረጉት።
"ኢትዮጵያ ውስጥ የጊዜው ነዋሪ ነው የነበርነው፤ ቋሚ ነዋሪ ሆነን አናውቅም፤ አንድ ቀን ኢየሩሳሌም እንደርሳለን በሚል ተስፋ ነው ስንኖር የነበረው" ይላሉ
በወቅቱ በነበረው የደርግ መንግሥት ከሃገር ሊወጣ ሲል የተያዘ ሰው እስር ሲብስም "ቀይ ሽብር" ይፋፋምብን በሚልም መገደልም ነበር። የተደበደቡ፣ ለእስር የተዳረጉ፣ እና የተገደሉም እንዳሉ በሃዘኔታ ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ ወታደሮች እንዳያዩዋቸው ጉዟቸውን ሲያደርጉ የነበረው ማታን ጠብቀው ሲሆን በተለይም አርማጭሆ እስኪደርሱ ያለው በጣም አሰቃቂ ገደል ከመሆኑ ጋርም ተያይዞ እግራቸውን የተሰበሩ እንዲሁም ተንከባለው ወድቀው ጉዳት የደረሰባቸው አሉ።
"ልጆችም ጫማ የሌላቸው በመሆኑ ይሄ አቃቅማ እሾሁ እግራቸውን ብጥስጥስ አደረገው፤ ውሃ በጭራሽ አይገኝም፤ ከተገኘም የቆሸሸ እንዲሁም የሞቀና መጠጣት የማይችል ነው፤ በረሃብና በውሃ ጥም ብዙዎች አልቀዋል" ይላሉ።
ፊልሙ ላይ የሞሳድ ሰራተኞች ከኢትዮጵያ ወታደሮች መንጋጋ ፈልቅቀው ቤተ እስራኤላውያንን እንዳዳኗቸውና ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው ተልዕኮ አካሂደዋል የሚል ቢሆንም በወቅቱ እስራኤል ከኢትዮጵያ ጋር ምንም አይነት የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ስላልነበራት እንደ ፊልሙ ሳይሆን ራሳቸውን አስተባብረው ሱዳን እንደደረሱም በወቅቱ የነበሩት አቶ አዳነ ይናገራሉ። "የሞሳድ ሰራተኞች ኢትዮጵያ ላይ በአካል አልደረሱም" ይላሉ
"ከነበርንበት ከአካባቢያችን ከደምቢያ፣ ላስታ፣ሽሬ፣ አክሱም፣ ወልቃይት፣ ጎንደር፣ ደምቢያ እንዲሁም ወገራ የነበሩትን ነጭ አይደለም ከዚያ አውጥቶ ከባዱን ድካም ሱዳን እስከምንደርስ ያሻገረን፤ እነዚህን ያደረጉትን እኔ ራሴ የማውቃቸው የቤተ እስራኤላውያን ማህበር አስተባባሪዎች ናቸው" ይላሉ
በፊልሙ ላይ ከበደ ቢምሮ ተብሎ የተወከለውና በእውነተኛው ከትግራይ አካባቢ የመጣው ፈረደ አክሎም ቤተ እስራኤላውያንን አስተባብሮ ሱዳን ያደረሳቸው አንደኛው መሪ እንደሆነ አቶ አዳነ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ።
ከአቶ አዳነ በተጨማሪ በጉዳዩ ላይ ከፍተኛ ምርምር አድርጎ "Red Sea spies: The true story of Mossad's fake holiday Resort" በሚል ርዕስ መፅሀፍ የፃፈው የቢቢሲው ጋዜጠኛ ራፊ በርግም ፈረደ አክሎም ቤተ እስራኤላውያንን በማስተባበር ደረጃ ከፍተኛ የጀግንነት ታሪክ እንዳለው ነግሮናል።
ፈረደ አክሎም በህይወት ባይኖርም በህይወት ያሉና ጉዞውን ያስተባበሩት አቶ ተገኘ የሚባሉ የደምቢያ ተወላጅ እንደነበሩ የሚናገሩት አቶ አዳነ በመንገድ ላይ ሊያጋጥማቸው ስለሚችሉ ችግሮች እንዲሁም ህዝቡን በማስተባበር፣ ከሞሳድ ጋርም በመቀናጀት ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።
ፊልሙ እንደሚያሳየው ሞሳድ ከኢትዮጵያም ይሁን ከሱዳን እንዳወጣቸውና ቤተ እስራኤላውያን ምንም ሚና እንዳልነበራቸው ቢያሳይም ራፊ እንደሚለው ይህ ከእውነት የራቀ ነው።
በኦፐሬሽን ብራዘርስ ላይ 7ሺ የሚሆኑ ቤተ እስራኤላውያን ከመንደራቸው በእግራቸው አቆራርጠው ሱዳን እንደደረሱና ከኢትዮጵያ ወደ ሱዳን በሚያደርጉት ጉዞም ሞሳድ ምንም ሚና እንዳልነበረው ይናገራል።
ሱዳንም በመድረሳቸው ምክንያትም ነው የሞሳድ ሰራተኞች ወደ እስራኤል ሊወስዷቸው የቻሉት ይላል
"የማዳን ስራ ሳይሆን የማድረስ ስራ ነው የተሰራው። ቤተ እስራኤላውያኑ ሱዳንም ከደረሱ በኋላ ከፍተኛ ሚና ነበራቸው የሞሳድ ሰላዮችም ሆነው ያገለገሉም ነበሩ" ይላል።
አቶ አዳነ በሱዳን መጠለያ የደረሱት ከአንድ ወር የእግር ጉዞ እልህ አስጨራሽና ፈታኝ ጉዞ በኋላ ሲሆን ለአስራ ሶስት ወራትም የሱዳን ቆይታቸው ሰቆቃ የተሞላበት እንደነበር ያስታውሳሉ።"ተዳክመናል፣ ተጎሳቁለናል፤ ለአስራ ሶስት ወራትም በጭብጥ ሽምብራ ውለን አድረናል" በማለት ፈታኙን ጊዜ ያስታውሱታል።
ረሃቡ፣ ጥማቱ ይባስ ብሎ ህፃናትን የሚገድል አንከል የሚባል በሽታ ገብቶ ፈጃቸው። በቀን ውስጥ አምስት፣ ስድስት ሰዎች የሚሞቱበት በአንድ ቀንም እስከ ሃያ አምስት ሰዎች የቀበሩበት ጊዜም እንደነበር ያወሳሉ።
አራት ሺ የሚሆኑ ስደተኞችም እንደ ቅጠል ረግፈዋል። እሳቸውም ጊዜው ቢረዝምና ሶስት አስርት አመታት ቢያልፍም ታናናሽ እህቶቻቸውንና ወንድማቸውን የነጠቃቸውን የሱዳን የስደት ጊዜ ትናንት የተፈጠረ በሚመስል ሁኔታና ሃዘናቸውን በሚያሳብቅ ሁኔታ በቁጭት ያወሩታል።
የሁለት አመቷ እናትዬ፣ የአራት አመቱ ታምራት፣የስምንት አመቷ ተጓዳ፣ የህፃን አንጀታቸው አልችል ብሎ፤ ያለውን ፈታኝ ሁኔታ ሊቋቋሙ ባለመቻላቸው ጨቅላ ሰውነታቸው ይህችን አለም ተሰናብታ ሄዳለች። ሱዳን በገቡ በአራት ወራቸውም ነው ላይመለሱ ያንቀላፉት።
የተስፋይቱን ምድር ለማየት ጓጉተው ተንከራተው ህይወታቸውን ያጡትንም በአመት አንድ ቀን ቤተ እስራኤላውያን በፀሎት እየሩሳሌም ላይ ይዘክሯቸዋል።
የኦፐሬሽን ብራዘርሰ በጀልባ ወደ እስራኤል መውሰድ እንዳቆመ በጥቂት ሳምንታት ወደ ሱዳን የገቡት አቶ አዳነ ኦፐሬሽን ሞሼ (ትዕይንተ ሙሴ) አካል ሲሆኑ ወደ እስራኤልም የተወሰዱት በአውሮፕላን ነው።
እህት ወንድም ፣ ቀብሮ በተለይም ለወላጆቻቸው በጣም ፈታኝ የነበረ ቢሆንም "የተስፋይቱ ምድር ሲደርሱ" በርከክ ብለው መሬቷን ስመዋል።
የፊልሙ ባለታሪክ አካል ከመሆናቸው አንፃር እንዴት አዩት? ምንም እንኳን የሞሳድን አስተዋፅኦ ባይዘነጉም የቤተ እስራኤላውያን ልፋት፣ እንግልት፣ ስቃይ፣ ታሪክና ማንነት በፊልሙ ላይ ምንም ትኩረት አልተሰጠውም ይላሉ።
"አለም ማወቅ የነበረበት የኛን ልፋት ነበር፤ ህፃን፣ አዛውንት ርቀቱ ሳይበግራቸው 600 ኪ.ሜትር አቆራርጠው፤ አንድ ቀንም ቢሆን በአካል ያላይዋትን ሃገር በእምነታቸው እየሩሳሌም፤ የተቀደሰች ስፍራ፤ የተስፋይቱ ምድር በሚል፤ ምግቡም ውሃውም እንደሚያልቅ ገብቶናል፤ የሞተው ሞቶ የዳነው ድኖ እንደርሳለን የሚል ተልእኮ ነበር የያዝነው። ይህንን ፊልሚ አይናገርም" ይላሉ
አብዛኛው ቤተ እስራኤላውያን የገጠር ሰዎች እንደመሆናቸው መጠን የአለም ካርታ አይተው አያውቁም፤ እስራኤል በካርታ ላይ የት እንደምትገኝ በወቅቱ የነበሩት ፅንሰ ሃሳቡ ባይኖራቸውም "እየሩሳሌም ሁልጊዜ ከልባችን የተቀመጠች ናት" ይላሉ
"ፅኑ እምነታችንን ቀርቶ፤ አራት ሺ ሰዎች ህይወታቸውን ሰውተዋል፤ እኔ ራሱ ሁለት እህቶቼን አንድ ወንድሜ መንገድ ላይ ቀርተዋል፤ የእኔን ድካም፣ ማንነቴን፣ ባህሌን፣ እኔ ምን አይነት ችግር እንዳጋጠመኝ፣ ምን አይነት አስተዋፅኦ እንዳደረኩ ፊልሙ አይናገርም" ይላሉ።
የታሪክ ግድፈቶች
ፊልሙ በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ ከማለቱ አንፃር ሙሉ በሙሉ እውነት መሆን ባይጠበቅበትም ታሪክን እንደገና መፃፍም ሆነ ሙሉ በሙሉ ግን መካድ አይችልም ይላሉ የሙያው ተንታኞች ። ፊልሙ ላይ ለምሳሌ ኢትዮጵያ የባህር በር እንደሌላት ይናገራል፤ ወቅቱ ግን የደርግ ጊዜ ከመሆኑ አንፃር ኢትዮጵያ የአሰብንና የምፅዋ ወደቦችን ትጠቀም የነበረና ባህር በር የነበራት ወቅት ነው።
ራፊም አንዳንድ ጉዳዮች ለፊልሙ ማሳመሪያ ተብለው የገቡና እውነትነት የሌላቸው ሁኔታዎችንም ጠቅሶልናል። የሱዳን ወታደሮች በሺዎች የሚቆጠሩ ቤተ እስራኤላውያን ስደተኞችን እንደጨፈጨፉ ቢያሳይም ይህ አልተፈጠረም።
ሃሳዊ ሪዞርቱ ላይ ቤተ እስራኤላውያን እንደቆዩ የሚያሳየውም እንዲሁ፤ ከዚህም በተጨማሪ ሲአይኤ የዚህ ተልእኮ ላይ ከፍተኛ ሚና እንደነበረውና ቤተ እስራኤላውያንንም በአውሮፕላን እንደወሰዷቸውም ፊልሙ ቢያሳይም ሲአይኤም ሆነ አሜሪካ እንኳን ቤተ እስራኤላውያንን ልትወስድ ስለ ተልእኮው ምንም መረጃ እንዳልነበራት ራፊ ያስረዳል።
ራፊ ፊልሙ ጥቁር እስራኤላውያን (ቤተ እስራኤላውያን) መኖራቸውን በማሳየት ሚና እንደተጫወተ ቢገልፅም ፊልሙ ቤተ እስራኤላውያን የነበራቸውን ሚናም ሆነ ታሪክ አጉልቶ ባለማውጣቱ ያጣው ነገር እንዳለ ይናገራል።
የሁለት ሰዓት ፊልም እንደመሆኑ መጠን ሁሉንም የታሪክ ትዕይንቶች ማስገባት ባይቻልም እንደ ጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር ከ1981-1984 ድረስ ባለው አስራ አምስት ሚስጥራዊ የሆኑ ተልእኮዎች በመሬት፣ በአየር እንዲሁም በጀልባ ተከናውኗል ይላል።
የነጭ አዳኝነት በኢትዮጵያና በአፍሪካ ፊልሞች
ጥቁርም ሆኑ ግሎባል ሳውዝ (ከነጩ አለም ውጭ) ታሪክን እንነግራለን የሚሉ ፊልም ሰሪዎችም ዋነኛ ፈተናቸው በተለይም ከበጀት ጋር ተያይዞ፤ የታሪኩን ማእከል ወይም ዋነኛ ገፀ ባህርዩን ነጮችን (የነጮችን አዳኝነት ታሪክ እንዲያስገቡ መገደዳቸው እንደሆነ ይናገራሉ።
በዚህም ኃይሌ ገሪማ አድዋን ለመስራት ከፍተኛ በጀት ጠይቀው በነበረበትም ወቅት የሚኒልክ አማካሪ ነጭ ሰው እንዲያደርግ መጠዬቁን እንደ ምሳሌ የሚነሳ ነው። "የኔ እናት ወይም አያት በፊልሞች ላይ እንድትኖር ለማድረግ አንድ ነጭ ሰው ሊኖር ይገባል"በማለትም በአንድ ወቅት ተናግረዋል።
በአፍሪካ ላይ የሚያጠነጥኑ አንዳንድ ፊልሞችን ወደኋላ ሄደት ብለን ብናይ ለምሳሌ "queen of the jungle" ብናነሳ ትንቢት የተነገረላትና ወርቃማ ፀጉር ያላት አንዲት ነጭ አፍሪካን ስታድን የሚያሳይ ነው።
የምዕራቡ አለም ከአንድ ቢሊዮን በላይ ህዝቦች በላይ የሚኖሩባትን አህጉር በተለይም በፀሃፍያን ዘንድ የምትመሰልበትን መንገድ ሽሙጣዊ በሆነ መልኩ በፃፈበት "ሃው ቱ ራይት አባውት አፍሪካ (ስለ አፍሪካ እንዴት መፃፍ እንችላለን) በሚለው ፅሁፉ ቢንያቫንጋ ዋይናይና
"የመፅሃፋችሁን ሽፋን በየቀኑ የምናገኛቸውን አፍሪካውያንን ፎቶ ሳይሆን ኤኬ 47 ጠመንጃን የተሸከመ፤ የሽምቅ ውጊያ፣ የተራቆቱ ጡቶች፤ የገጠጡ አጥንቶችን አድርጉ" በማለት ምዕራባውያን ስለ አፍሪካ ሲፅፉ በተደጋጋሚ የሚያወጧቸውን ፎቶዎች በማየት በነገር ሸንቆጥ አድርጓቸዋል።
ረሃብ፣ ችግር፣ ጦርነት፣ እርስ በርስ መጨፋጨፍ ብቻ በተሞላችባት በሆሊውዷ አፍሪካ ላይ ይህንን ሲቀርፉ የሚታዩትና ሲያድኑ የሚታዩትም ነጭ ሰዎች ናቸው።
ከነዚህም ውስጥ ብዙዎች የሚጠቅሷቸው "ብለድ ዳይመንድ" ዘረኛ ነጭን ወክሎ የሚጫወተው ቅጥረኛው ነፍሰ ገዳይ ሊዮናርድ ዲካፕሪዮ ጥቁሩን ሴራሊዮናዊና ልጁን ሲያድን ከጥቁር ነፍሰ ገዳዮች ሲያድንም ይታያል። የፊልም ልሂቃን ቆጥረው ከማይዘልቋቸው መካከል አምስቴድ፣ ቲርስ ኦፍ ዘ ሰን፣ ክራይ ፍሪደምና በኢትዮጵያ ረሃብ ላይ የሚያጠነጥነው ቢዮንድ ቦርደርስና ሌሎችም ይገኙበታል።
የባርነትን ታሪክ እንደገና ከመፃፍ ጀምሮ፣ ኔቲቭ አሜሪካውያንን ሰው በላ አድርጎ መሳል፣ አፍሪካውያንን ነፃ በማውጣትና በመርዳት ነጮችን የአዳኝነት ታሪክ ስፍራ ሆሊውድ እንደፈጠራላቸው ተችዎች ይተነትናሉ።
በዚህም ፊልም ላይ ኢትዮጵያውያንን ማዳን ብቻ ሳይሆን ሱዳን ውስጥ ያለን አንድ ብሔር የሰው ስጋ እንደሚበሉ የሚነገርበት፤ የፀጥታ ኃይሉ ምንም ርህራሄ የሌለውና (ያልተፈጠረ ታሪክ በመጨመር) ሱዳናውያን ኢትዮጵያውያን ሲጨፈጭፉ የሚያሳየው ዝም ብሎ የሚወሰድ ሳይሆን ለዘመናት የላቁበት የታሪክ አነጋገር ዘያቸው እንደሆነ ተችዎች ፅፈዋል።
በብዙ ፊልሞች ዘንድ የተሳተፈው ያሬድ ሹመቴም ሆሊውድ ወይም የነጩ አለም ነጭ ጀግኖችን በመፍጠር የነጩን አለም ልዕልናንና የሞራል ከፍታን የማሳየት ተልእኮ ለዘመናት የመጣ ከመሆኑ አንፃር በዚህ ፊልም ላይ እንዳልደነቀው ይናገራል።
ከዚህ በላይ ግን ከፍተኛ ጥያቄን የፈጠረበት ፊልሙ ታሪክ እንደሚያይ ምንም አይነት እውቅና ያልተሰጠውና ሆሊውድ ፊልም ሲሰራ ተመልካቾቼ ከሚላቸው ዝርዝው ውስጥ ኢትዮጵያውያን እንዴለሉበት ኣሳይ ነው ይላል።
በቋንቋም፣ በመልክአ ምድርም፣ በታሪክ አካሄድም "ኢትዮጵያውያን ውሸት እንዴት ለምን ይነግሩናል ቢሉ ግድ እንደማይሰጣቸው የሚያሳይ ነው። ይላል
በተለይም ፊልሙን እንደ ኢትዮጵያዊ ሲያየው በጣም የሚጎረብጥ ሆኖ ነው ያገኘው። የሱ ክርክር ይህ የታሪካችን ክፍል ለምን ታዬ ሳይሆን የውክልና ጥያቄ ነው። የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ባህል አኗኗር፣ የቋንቋ ዘዬና መልክአ ምድር ጠንቅቆ የማያውቅ ፊልም ነው የሚለው ያሬድ "ኢትዮጵያ የሌለችበት ስለ ኢትዮጵያ የተሰራ ፊልም ነው።" ብሏል።
የተዘበራረቀ መልክዓ ምድር
ቤተ እስራኤላውያን የሰፈሩት ሽረ፣ አደጋሮም፣ ወልቃይትና ተከዜን ፣ወገራ፣ ዳባት አባጊዮርጊስ፣ ደምቢያ፣ ፀዳ፣ ማክሰኚት፣ ወደ ሰሜን ደግሞ ደጎማ፣ የመሳሰሉትን ቦታዎች ላይ እንደሆነ አቶ አዳነ ይናገራሉ።
ፊልሙ የተሰራው ናሚቢያ ሲሆን ታሪኩ የተፈፀመበት ቦታ ተብሎ የተወሰደውና የቤተ እስራኤላውያን መኖሪያ ደግሞ ከአባይ ወንዝ ዳርቻ ላይ ያለ ቦታ ይመስላል። የመልክአ ምድር አቀማመጡና የቤተ እስራኤላውያንን አሰፋፈር ግምት ውስጥ የከተተ አይደለም በማለትም ያሬድ ይከራከራል።
ቤተ እስራኤላውያኑ በስደትም ላይ ትንሽ ተጉዘው ውሃ ውስጥ ይገባሉ። አካባቢውን በደንብ ለሚያውቀው ያሬድ ከጎንደር ተነስቶ የአርማጭሆ በረሃን አቋርጦ፤ የሱዳንን ድንበር ለመሻገር ወደ ጎጃም በመተከል አድርገው ካልሄዱ በቀር፤ በኢትዮጵያ መልክአ ምድር ውስጥ አባይን ሊያቋርጡ፤ ውሃውን ሊያቋርጡ የሚችሉበት ምንም አይነት የመልክአ ምድር ግጥጥሞሽ እንደሌለም አበክሮ ይናገራል።
"ፊልሙ ላይ ሆን ተብሎ አንዲት ኢትዮጵያዊ ባህር ውስጥ ስትሰጥም አጉልቶ ለማሳየት በሚል ለማየት የተፈጠረ ይመስለኛል። ይህ አሁን እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ በከፍተኛ ሁኔታ ይረብሻል።" ይላል
ከመልክአ ምድር መዘበራረቅ በተጨማሪ በጣም ያሳዘነው ኢትዮጵያዊ ውስጥ የኖሩ ቤተ እስራኤላውያን ከመሆናቸው አንፃር አለባበሳቸው፣ ቋንቋቸው ኢትዮጵያዊ መሆን ሲገባው አማርኛ መናገር የማይችሉና የሚኮላተፉ ገፀባህርያት መጠቀማቸው ነው።
"ይህ በጣም ለኔ ጎርብጦኛል፣ አናዶኛል። የተናደድኩት ለምንድን ነው እንደዚህ የምሆነው ለምንድን ነው ብዬ ስል ለታሪኩ ሳይሆን መታመን የፈለጉት እኛ በጭራሽ፤ እንደ ፊልም ተመልካች አልተቆጠርንም" ይላል
ፊልሙን ለምን ኢትዮጵያ አልሰሩትም የሚለው ዋነኛው ጥያቄው የሆነው ያሬድ በ70ዎቹ ላይ የነበረ ታሪክን እንስራ ቢሉ እንደማይከለከሉ ያምናል። ኢትዮጵያ የታየችው እንደ ታሪክ ማሳያ ወይም ማሟሻ ተደርጋ ከመሆኑ አንፃር ጉግል አድርገው በቀላሉ መመለስ የሚችሏቸውን ታሪኮች ስተዋል ይላል።
"ስለ መኪና ጎማ ፊልም ብትሰሪ የመኪና ጎማ ስታሳየኝ አጣመምከኝ አይልም፤ ምክንያቱም አንደበት የለውም። እኛም አንደበት እንዳለው አስተያየቱን እንደሚሰጥ አካል አልታየንም።" ይላል።
እስራኤላውያን በጀርመን የነበረውን እልቂት የሰሩት ታሪኩን አበላሽተው ሳይሆን እንደ ታሪኩ ባለቤት እውቅና ሰጥተው ሲሆን ይህም ሆሊውድ ላይ አብዛኞቹ ትልልቅ ስቱዲዮዎች ባለቤት ስለሆኑ ተፅእኖን መፍጠር ችለዋል ይላል።
የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ላይ ያጠነጠነው ዘ ኢንተርቪው ፊልም ፕሬዚዳንቱ ክብሩን ዝቅ የሚያደርግ ነው በሚል የሶኒ ፊልም ላይ ሳይበር አታክ አድርሰዋል።
"ኢትዮጵያን የሚያዋርድ ነገር ተሰርቶ ኢትዮጵያም ምንም አትልም።ይህ የሚያሳየው የመናቅ ደረጃችንን ነው" ይላል
ኢትዮጵያን አይወክልም ብሎ የሚሞግቱ ሰዎችና ኢኮኖሚያቸው፣ ደህንነታቸውና ገበያቸው ላይ ችግር የሚያመጣ ስለሌለ ቸልተኝነት እንደፈጠረ ይገልፃል።
ስለ ቻይና ቢሰሩ ቻይና የሚመስሉ ሰዎች እንደማያመጡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለታሪኩ ታማኝ አልሆኑም በማለትም ያስረዳል።
የመፃፍ ነፃነት እስከምን ድረስ
ፊልሙ በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ ከማለቱ አንፃር ያልነበሩ የታሪክ ሁነቶችን ማስገባት ይቻል ይሆን? የፀሐፊው ነፃነትስ እስከምን ድረስ ነው የሚሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ።
መነሻውን ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ ቤተ እስራኤላውያን ነበሩ በማለት ልብወለድና ፀሐፊው በምናቡ የሚመላለሱ ታሪኮችን ማካተት እንደሚቻል ያሬድ ያስረዳል።
እንዲህ አይነት ነፃነት ካለ ስህተቱ ታዲያ ምን ላይ ነው? ያሬድ ምላሽ አለው።
"በዚህ ፊልም ላይ በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ ሲል የትኛው ነው እውነተኛ ታሪክ የሚለው ነው ጥያቄ ውስጥ የሚገባው፤ የትኞቹ ናቸው እውነተኛ ታሪክ ብሎ የሚከራከራቸው፤" ብሎም ይጠይቃል።
ሰዎቹ ኢትዮጵያዊ ካልሆኑ፣ ባህላቸው፣ ቋንቋቸው ከሌለ፤ ሃገሪቷ ኢትዮጵያ ካልሆነች፤ የታሪክ ግድፈት ካለበት ስለየትኞቼ ህዝብ ነው የሚያወሩት
"እንደሰውም አልተቆጠርንም፤ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ የሚያዋርድ ፊልም ነው፣ እንደ አፍሪካዊም የሚያሳፍር ነው፣ እንደ አንድ ፊልም ሰሪ የቤት ስራቸውን ያልጨረሱ ፊልም ሰሪዎች እንደ ተመልካች 'ማይኖሪቲ' ብለው ለሚያስቡት ታማኝ ያልሆኑበት ነው።" ይላል
ቤተ እስራኤላውያን በኢትዮጵያ
ስለ ቤተ እስራኤላውያን አመጣጥ ሁለት ማብራሪያዎች ይሰጣሉ ። አንደኛው ንግሥት ሳባ የእየሩሳሌምን ንጉስ ሰለሞን ልትጠይቅ ሄዳ ምኒልክ ተወለደ የሚል ሲሆን ይህ ግን ከአፈ ታሪክ ያልዘለለ እንደሆነ ኢትዮጵያ ላሉ ቤተ እስራኤላውያን የሚደረጉት እንቅስቃሴዎች ኃላፊ አቶ ንጉሴ ዘመነ አለሙ ይናገራሉ።
ቤተ እስራኤላውያን የሚያምኑትና መፅሀፍ ላይ የሰፈረው በሰባኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛው ቤተመቅደስ በፈረሰበት ሰዓት ይሁዳውያኖች መሰደድ ጋር ተያይዞ የመጣውን ነው።
ከ አስራ ሁለቱ ነገዶችም መካከል ዳን ተብሎ የሚጠራው ነገድ ወደ ግብፅ ተሰደደ፤ ከግብፅም የናይል ወንዝን በመከተል ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ሰፍረዋል።
በኢትዮጵያ በሚኖሩበት ወቅት ፈላሻ ወይም ካይላ የሚል ስያሜ ተሰጥቷዋል። አቶ ንጉሱ እንደሚናገሩት ፈላሻ የሚለው ቃል 'ሊፍሎሽ' ከሚለው የእብራይስጥ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም ሲሆን ከቦታ ቦታ የሚዞር ቋሚ ቦታ የሌለው ማለት ነው።
ካይላም እንዲሁ 'ክሂላ' የሚለው ከእብራይስጥ የተወሰደ ሲሆን አንድ ላይ የሚሆን በማህበር የሚሄድ ማለት ቢሆንም ለዘመናት ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ስድብ አገልግሏል። ቀጥቃጭ፣ አንጥረኛ፣ ቡዳ በሚልም ለዘመናት ሲገለሉ ሲዋረዱም ኖረዋል።
የእስራኤል መንግሥትን ምስረታ ተከትሎ ቤተ እስራኤላውያን ወደ እስራኤል የሚያደርጉትን ጉዞ የተጀመረ ቢሆንም በ1906 ዓ.ም ፕሮፌሰር ታይታሎቪች በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በመምጣት ጥናት አድርጎ ይሁዲዎች ኢትዮጵያ እንዳሉ ከዚያ 50 የሚሆኑ ወጣቶችን ወደ አውሮፓ እንደወሰደ አቶ ንጉሱ ይናገራል።
ኦፐሬሽን ሞሰስ፤ በጎርጎሳውያኑ 1980፣ 1981 ላይ የነበረ ሲሆን የሞሳድ ድርጅት ትብብር በማድረግ ከ7ሺ በላይ ይሁዲዎችን በሱዳን ምድር ይዞ የሄደበት ኦፐሬሽን ሲሆን ከዚያ በኋላ ደግሞ የቀሩት ይሁዲዎች ወደ አዲስአበባ በመሄድ በአዲስ አበባ የተደረገው ጉዞ ነው።
የመግሥት ለውጥ ከተደረገ በኋላ ኦፐሬሽን ሰለሞን (ትዕይንተ ሰለሞን) በጎርጎሳውያኑ 1991 ከ14ሺ600 በላይ ቤተ እስራኤላውያን በ36 ሰአታት ውስጥ ተወስደዋል።
ከዚያ በኋላም ትንንሽ ጉዞዎች የነበሩ ሲሆን ክንፈ ዮና፣ ሸአሪት ይሁዲ ኢትዮጵያ (የቀሩ ይሁዲዎችን መውሰድ) የሚሉም ተካሂደዋል።
በአዲስአበባና በጎንደር ያሉ የተመዘገቡ 8 ሺ 200 የሚጠባበቁ ቤተ እስራኤለውያን ያሉ ሲሆን፤ እስራኤል ሃገር ያለው የ2017 የእስራኤል ስታትስቲክስ መሰረት 150ሺ ቤተ እስራኤላውያን አሉ።