ጥቁር ወንዶችን በአሰቃቂ ሁኔታ የገደለው የጄፍሪ ዳመር ፊልም ያስነሳው ውዝግብ

በርካታ ጥቁር ወንዶችን ለአመታት በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገድል የነበረውና በአስከሬናቸው ላይ አጸያፊና ኢሰብዓዊ ተግባራት የፈጸመው አሜሪካዊው ጄፍሪ ዳመር ታሪኩ ከሰሞኑ ወደ ፊልም ተቀይሮ ለዕይታ ቀርቧል።

ፊልሙ በኔትፍሊክስ ለዕይታ ከቀረበ በኋላ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተመልካቾች አይተውታል።

በሌላ መልኩ ለበርካቶች ስሜት ያልተጠነቀቀና የሟች ቤተሰቦችን ስሜት ግምት ውስጥ ያላስገባ በሚልም ከፍተኛ ትችት እያስተናገደ ይገኛል።

ፊልሙ ‘ሞንስተር፡ ዘ ጄፍሪ ዳመር ስቶሪ’ የሚል ርዕስ ተሰጥቶታል።

“እንደ ጥቁር ህዝብ ይህንን ፊልም መመልከት የለብንም። በጥቁር ልጆቻችን ላይ የፈጸመው ተግባር ከጭካኔ በላይ ነው” በማለት ራፐር ቦዚ ባድአዝ በትዊተር ገጹ አስፍሯል።

ጄፈሪ ዳመር 17 ታዳጊና ወጣት ወንዶችን ገድሏል። ወቅቱም ከአውሮፓውያኑ 1978 እስከ 1991 ድረስ ነበር።

አብዛኛዎቹ ሟቾች ጥቁር የተመሳሳይ አፍቃሪ ወንዶች ነበሩ።

በአሰቃቂ ሁኔታ ወንድሟን ያጣችው አንዲት ግለሰብ ፊልሙ መሰራቱ “ጨካኝ እና ግድየለሽ” ስትል ወርፋዋለች።

ሪታ ኢስቤል ወንድሟ ኢሮል ሊንድሴ ሲገደል ገና የ19 አመት ታዳጊ ነበር።

በአውሮፓውያኑ 1992 ልብ የሚሰብር ምስክርነት ለፍርድ ቤት ሰጥታም ነበር።

ነገር ግን አሁን በወጣው ባለ 10 ተከታታይ ፊልም ያ ምስክርነቷ ቃል በቃል እንደሚቀርብ አልገመተችም ነበር።

“አንዳንዱን ትዕይንት ሳይ ሽብር ለቀቀብኝ። በተለይም ራሴን በስክሪን ላይ ስመለከተውና የተናገርኩት ቃል በአንዲት ተዋናይት ሲደገም ማየት ያለፍኩበትን ሃዘን ዳግም መኖር ነው” በማለት ለኢንሳይደር ተናግራለች።

ስግብግብነት ነው

ሪታ እንደምትለው ኔትፍሊክስ እውነተኛ ታሪኩን ወደ ፊልም ሲቀይር ቢያንስ የተጎጂዎቹን ቤተሰብ ማሰብ ነበረበት።

ኔትፍሊክስ ከፊልሙ ገቢ ለተጎጂዎች ልጆች እና ልጅ ልጆቻቸው ቢያንስ የተወሰነ ገንዘብ መስጠትም እንደነበረበት ታስረዳለች።

“ከዚህ ታሪክ የተወሰነ ገንዘብ ቢያገኙ ምናልባትም ይህንን ያህል ጭካኔ እና ግድየለሽ ናቸው የሚለው አይሰማቸው ይሆናል። በሰዎች ኃዘን ገንዘብ ማግበስበስ፣ ትርፍ ማግኘት ስግብግብነት ነው” ብላለች።

ባለፈው ሳምንት የሟቹ ሊንድሴይ የአጎት ልጅ ኤሪክ ፔሪ ቤተሰቡ በተከታታዩ ፊልም ደስተኛ እንዳልሆኑ በትዊተር ገጹ አስፍሯል።

“እንደገና የሰዎች ኃዘን እንዲያገረሽ ማድረግ፣ እንደገና ሰዎች በስቃይ ውስጥ እንዲሆኑ መፍቀድ ለምን? ስንት ፊልሞችና ጥናታዊ ዘገባዎ ናቸው የሚሰሩት?” ሲልም ይጠይቃል።

አክሎም “ወንድሟን አሰቃይቶ የገደለውን ግለሰብ የአጎቴ ልጅ ስታይ በፍርድ ቤት የደረሰባትን የስሜት መቃወስ እና መረበሽ እንደገና ማሳየት በጣም ያሳዝናል፤ ከማመን በላይ ነው” ብሏል።

ዳመር ከአሰቃቂ ግድያ በተጨማሪ ሰዎችን በመብላት እና ከአስከሬኖች ጋር ወሲብ ፈፅሟል። በአውሮፓውያኑ 1992 ከተፈረደበት ከሁለት ዓመት በኋላ በእስር ቤት በሰው እጅ ህይወቱ ጠፍቷል።

በወቅቱ ወንጀሎቹን መፈጸሙን ለመጀመሪያ ጊዜ የዘገበችው ጋዜጠኛ አን ኢ ሽዋርትዝ ተከታታይ ፊልሙ “ድራማ ለመፍጠር ሲባል ትክክለኛ መረጃዎችን መስዋዕት አድርጓቸዋል” ስትል ለኢንዲፔንደንት ተናግራለች።

የቀድሞዋ የወንጀል ጋዜጠኛ በርካታ ትክክለኛ መረጃዎችን ታሪኩን ለማሳመር ሲባል “ከእውነታው ጋር ሙሉ በሙሉ የሚመሳሰል አይደለም በሚል የጥበብ ነጻነታቸውን ተጠቅመዋል” ትላለች።

በተጨማሪም በወቅቱ የነበሩት የከተማዋ ፖሊሶች “ዘረኞች እና ተመሳሳይ አፍቃሪ ጠሎች ናቸው መባሉ ትክክል አይደለም” በማለት ታስረዳለች።

ከፍተኛ ተመልካቾችን ያስተናገደው ፊልም

ኔትፍሊክስ መጀመሪያ ላይ ፊልሙ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ ይዘት አለው በሚል ፈርጆት ነበር።

በኋላ ግን ከከፍተኛ ውግዘት በኋላ ይዘቱ እንዲነሳ ተደርጓል።

ሆኖም ውዝግቡ ፊልሙ ከፍተኛ ተመልካቾችን እንዲያገኝ ከማድረግ አላገደውም።

በኢንዲዋይር መረጃ መሰረት ኔትፍሊክስ ፊልም ማሳየት ከጀመረበት ወቅት አንስቶ በሳምንት ውስጥ ይህን ያህል ከፍተኛ ቁጥር በማግኘት የቁንጮነቱን ስፍራ ይዟል።

ፊልሙ በሳምንት ውስጥ ለ196.ሚሊዮን ያህል ሰዓታት ታይቷል።

በአሁኑ ወቅት በኔትፍሊክስ ከ60 በላይ ባሉ ሃገራት ቁጥር አንድ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ሆኗል።

ኔትፍሊክስ በፊልሙ ላይ ለቀረቡት ትችቶች ምላሽ ሰጥቷል።

በፊልሙ ጭብጥ ላይ በሰፈረው ጽሁፍ “ለማመን የሚከብዱ ወንጀሎችን የሚያጋልጥ ነው። እነዚህ ወንጀሎች የተፈጸሙት ተጋላጭ በሆኑ ታዳጊዎችና ወንዶች ላይ ነው። በፖሊስ ተቋማዊ ወድቀቶችና የመዋቅራዊ ዘረኝነት በነዚህ ማህበረሰቦች ላይ በማነጣጠሩም ለአስር ዓመት ያህል በግልፅ ግድያዎቹ እንዲቀጥሉ ምክንያት ሆኗል” ብሏል።

ፊልሙ በብዙዎች ዘንድ አሰቃቂና ለመመልከት የሚያዳግት ነው ተብሏል። አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ መግደል ብቻ ሳይሆን በአስከሬኖቹ ላይ የሚፈፅውም ተግባር ከሰው ልጅ እሳቤ በላይ ነው ተብሏል። በርካቶችም ፊልሙን ለማየት ከስሜታቸው ጋር ሲታገሉም እንደነበር አጋርተዋል።