"መውለድ አልፈልግም"

ካሮላይን ሚቼል
የምስሉ መግለጫ, ካሮላይን ሚቼል

ልጅ መውለድ አንፈልግም የሚሉ ሴቶች ቁጥር እየጨመረ፣ የወሊድ መጠንም እየቀነሰ መጥቷል።

ልጅ ላለመውለድ በምክንያትነት የሚቀመጡት ነጥቦች የተለያዩ ናቸው። የአየር ንብረት ለውጥ ፍራቻ፣ የገንዘብ ማነስ እና የጤና እክልን መጥቀስ ይቻላል።

በሌላ በኩል “ልጅ አለመውለድ ነጻ ፈቃዳችን ነው” የሚሉም ሴቶች አሉ።

ማኅበረሰባዊ ተቀባይነቱ ግን እምብዛም ነው። ይህም ሴቶቹ ላይ አሉታዊ ስሜት ያሳድራል።

በዩናይትድ ኪንግደም ‘ብሪስትል ቻይልድ ፍሪ ውሜን’ የተባለ ስብስብ አለ። ልጅ መውለድ የማይፈልጉ ሴቶች፣ ልጅ መውለድ ለማይፈልጉ ሴቶች ያቋቋሙት ማኅበር ነው። ከ500 በላይ አባላት አሉት።

ከእነዚህ ሴቶች አንዷ የ46 ዓመቷ ካሮላይን ሚቼል ናት። ብሪስትል ውስጥ ከባለቤቷ ጋር ትኖራለች። ወጣት ሳለች ልጅ አለመውለዷ አያሳስባትም ነበር። ዕድሜዋ ሲገፋ ግን ልጅ ከወለዱ ጓደኞቿና ወዳጆቿ የሚሰነዘርላት ጥያቄ ተበራከተ።

“ልጆች አልፈልግም በማለቴ እንደ ልዩ ፍጥረት መታየት ጀመርኩ። አቋሜ ተቀባይነት የሌለው እንደሆነ ተሰማኝ” ትላለች።

ማኅበረሰቡ ዝግጁ የሆነው ልጆች ለሚወልዱ ሴቶች ብቻ ነው የምትለው ካሮላይን “ከሕይወት የመገለል ስሜት ውስጥ ይከታል” ስትል ነው የምትገልጸው።

በሁሉም ሁኔታዎች ውስጥ ለእናቶች በተመቻቸ ዓለም ውስጥ “ከሰዎች ጋር መገናኘት ራሱ” ከባድ ነው ትላለች።

ልጆች ያሏቸው ሴቶች ዓለም “ልጆች ላልወለዱ ሴቶች ምቹ ናት” ብለው ሊያስቡ እንደሚችሉ ታምናለች። እውነታው ግን ይህ አይደለም።

ከጓደኞቿ መካከል አብዛኞቹ ልጆች አሏቸው። እሷ ስላልወለደች መጥፎ እንዲሰማት በቀጥታ ያደረጉት ነገር ባይኖርም ሁሉም ተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸው በራሱ “ነገሮችን ከባድ ያደርጋቸዋል” ትላለች።

ካሮላይን ልጅ መውለድ እንደማትፈልግ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ናት። በውሳኔዋም “እርግጠኛና ደስተኛ” እንደሆነች ብትናገርም አንዳንዴ ውሳኔዋ ላይ ጥያቄ ማንሳቷ አልቀረም።

በባህል ተቀባይነት ያለውና ለሴቶች “ተፈጥሯዊ” ተብሎ የሚወሰደው ልጅ መውለድ መሆኑን ሳትጠቅስ አታልፍም።

እአአ በ2022 በወጣ ጥናት መሠረት፣ እስከ 30 ዓመታቸው ድረስ ልጅ የማይወልዱ ሴቶች ቁጥር መጨመሩን ያሳያል።

ከዩናይትድ ኪንግደም በተወሰደ አሐዝ መሠረት፣ እአአ በ1990ዎቹ ከተወለዱ ሴቶች 50.1% ያህሉ በ2020 በ30ዎቹ ዕድሜ ክልል እስከሚደርሱ ድረስ ልጅ አልወለዱም።

ሜጋን ስታንሊ ልጅ መውለድ እንደማትፈልግ እርግጠኛ ነበረች።

ከ19 ዓመቷ ጀምሮ ላለመውለድ ጥረት ስታደርግ ነበር። ይህም ማምከን (sterilize ማድረግን) ይጨምራል።

የወር አበባዋ ሲመጣ የሚሰማትን ከፍተኛ ሕመም በመግለጽ “በየወሩ በዛ ሕመም ማለፍ አያስፈልግም” ትላለች።

“ማምከን የወር አበባን እንደማያቆም አውቃለሁ። ግን የወር አበባ ሕመምን ይቀንሳል” ትላለች።

አሁን 31 ዓመቷ ነው። ሐኪሞች “በጣም ወጣት ነሽ” ወይም “ኋላ ላይ ሐሳብሽን ብትቀይሪስ” የሚል ምላሽ እንደሚሰጧት ትናገራለች።

በ29 ዓመቷ ከቀዶ ሕክምና ባለሙያ ጋር ቀጠሮ ይዛ ነበር።

“የሕክምና ታሪኬን ጨምሮ ሁሉንም ነገር አዘጋጀሁ። ከሥነ ልቦና ባለሙያ ምስክርነት ሳይቀር አዘጋጅቼ ነበር” ትላለች። ሆኖም ፈቃድ አላገኘችም።

በወቅቱ ለሦስት ወራት የቆየ የፍቅር ግንኙነት ውስጥ ነበረች። አሁን የሕይወት አጋሯ ሆነው አብረው ዘልቀዋል።

የወንድ ጓደኛዋ ልጅ መውለድ እንደማይፈልግና በሕክምና ታግዞ ላለመውለድ ቀዶ ሕክምና (vasectomy) እንዳደረገም ለሐኪሟ ነግራለች።

ሆኖም ግን የሐኪሟ ምላሽ “እሱ መውለድ የማይችል ከሆነ አንቺ ለምን የማምከን ሕክምና ያስፈልግሻል” የሚል ነበር።

“እሱ ሰውነቱ ላይ ያሻውን ካደረገ እኔስ ለምን በሰውነቴ ያሻኝን ማድረግ አልችልም?” ትላለች ሜጋን።

ሜጋን ስታንሊ
የምስሉ መግለጫ, ሜጋን ስታንሊ ከወንድ ጓደኛዋ ጋር

“አሁን የምጠብቀው እስከማርጥ ድረስ ነው” ትላለች።

ካሮላይን እንደምትለው ደግሞ ልጅ መውለድ የማይፈልጉ ሴቶች ስለ ጉዳዩ አለማውራታቸው ልጅ መውለድ ተቀባይነት እንዳለው መንገድ እንዲታይ የራሱ አስተዋጽኦ አለው።

“ስለ ነገሩ አናወራም። እናም ሁሉም ሴት ይወልዳል የሚል እሳቤ ነው ያለው። እናትነት ወደየትኛውም አቅጣጫ ስንዞር ያለ ነገር ይመስላል” ስትል ታስረዳለች።

“ከማኅበረሰቡ ባህል ጋር አብሮ አለመሄድ” ቀላል እንዳልሆነ ትናገራለች።

“የተለየ” ውሳኔ ባትወስን ኖሮ ሕይወት “ቀላል” ሊሆን እንደሚችል ታስባለች። ሆኖም ግን ሴቶች ምንም ይወስኑ ምንም “ውሳኔያቸው ተቀባይነት ያጣል። በውሳኔያቸው እንዲጸጸቱም ይደረጋሉ” ትላለች።

ፊዮና ፓውሊ
የምስሉ መግለጫ, ፊዮና ፓውሊ

ፊዮና ፓውሊ ከ12 ዓመቷ ጀምሮ ልጅ መውለድ እንደማትፈልግ ታውቅ ነበር።

እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው እናቷ ያለፈችውን ውጣ ውረድ በማየት ነው።

አሁን 49 ዓመት ሆኗታል። በብሪስትል መውለድ የማይፈልጉ ሴቶች ማኅበርን ትመራች።

አሁን የማረጥ ምልክቶችን ሰውነቷ ላይ ስታይ፣ አለመውለዷን በማሰብ “እንደማትደናገጥ” ትናገራለች።

“ምቾት ነው የሚሰማኝ” ስትል ስሜቷን ትገልጻለች።

ጥሩ ወላጅ መሆን እንደምትችል ፊዮና ብታምንም መውለድ ግን አትፈልግም።

ፊዮና ልክ እንደ ካሮላይን እና ሜጋን ልጅ መውለድ እንደማትፈልግ ለሰዎች ስትናገር እንደሚደነግጡ አስተውላለች።

“ይፀፅትሻል። ታዲያ የመኖርሽ ትርጉም ምንድን ነው? ልጅ ካልወለድሽ ሴት አይደለሽም” መባሏን ፊዮና ትናገራለች።

እሷ ልጅ መውለድ ባለመፈለጓ “ሰዎች ምቾት እንደማይሰማቸው” ትገልጻለች። እነሱም ምርጫ እንዳላቸው ሰዎች እንደማያስቡም ትገነዘባለች።

ልጅ መውለድ አልፈልግም በማለቷ “ልጆች ጠል” ወይም “ክፉ” ተደርጋ መወሰዷን ታስታውሳለች።

በሷ ዕይታ ግን ልጅ መውለድ አለመፈለግ “የማንነቷ አካል” ነው።

በዕድሜ ከገፋች በኋላ አንድ ቀን ከእንቅልፏ ተነስታ በውሳኔዋ እንደማትፀፀት ታምናለች።

ካሮላይን እንደምትለው፣ ልጅ ብትወልድ “ደስታ የራቃት እናት” ነበር የምትሆነው። ልጆች ባለመውለዷ ትኩረቷን የፍቅር ግንኙነቷና የግል ፍላጎቶቿ ላይ ማድረግ እንደቻለች ትናገራለች።

ሜጋንም ትስማማለች።

“ነገሩ የነጻነት ወይም የገንዘብ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የምርጫም ነው” ትላለች።