ሜክሲኮ ውስጥ በማፊያዎች ታግተው ከነበሩት አሜሪካዊያን ሁለቱ ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ባለፈው ሳምንት በጠራራ ፀሐይ በሜክሲኮ የማፊያ ቡድን ታግተው ከነበሩት አራት አሜሪካዊን ሁለቱ ተገደሉ።
በሕይወት የተረፉት ሁለቱ ደግሞ ተለቀው ወደ አሜሪካ ተመልሰዋል።
አራቱ አሜሪካዊያን ወደ ሜክሲኮ አቅንተው የነበረው ለውበት ቀዶ ጥገና እንደነበረ ተዘግቧል።
ከአጋቾቹ መሀል አንድ የ24 ዓመት ወጣት በታማውሊፓስ ግዛት በቁጥጥር ሥር ውሏል።
አራቱ አሜሪካዊያን ባለፈው ሳምንት ታግተው የነበረው መኪናቸውን ከቴክሳስ ከተማ ድንበር ባሻገር ወደ ምትገኝ ማታሞሮስ ከተማ እያሽከረከሩ ወደ ሜክሲኮ በመጓዝ ላይ ሳሉ ነበር።
መሣሪያ ተደግኖባቸው ሲታገቱ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምሥል በአንድ ክፍት ፒክአፕ መኪና ላይ ታስረው ሲጫኑ ያሳያል።
በቅርብ ርቀት ሆና ድርጊቱን ስትመለከት የነበረች አንዲት የ33 ዓመት ሜክሲኳዊት በአጋቾቹ ተተኩሶባት ሕይወቷ አልፏል።
የዋይት ሐውስ ብሔራዊ ደኅንነት ካውንስል ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ለሞቱት አሜሪካዊያን ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተዋል።
ከእገታው የተለቀቁት ሁለቱ አሜሪካዊያን በከፍተኛ ሁኔታ በታጠቀ የሜክሲኮ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች አጀብ ወደ አሜሪካ ድንበር ገብተዋል።
ኤፍቢአይ ባወጣው መግለጫ ጥፋተኞቹ ታድነው ለሕግ እንዲቀርቡ ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ጥረቱ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
የሜክሲኮ ፕሬዝዳንት አንድሬስ ማኑኤል ሎፔዝ ኦብራዶር በተፈጠረው ሁኔታ ማዘናቸውን ገልጠዋል፤ ለሟች ቤተሰቦችና ለአሜሪካዊያን በጠቅላላ መጽናናትን ተመኝተዋል።
ድርጊቱን ፈጽመዋል ተብለው የሚታመኑት ‘የገልፍ ካርቴል’ በመባል የሚታወቁ የአደገኛ ዕጽ አዘዋዋሪ ቡድን አባላት ናቸው።
ይህ ቡድን በሜክሲኮ 100 ዓመት ያስቆጠረ እውቅ የማፍያ ቡድን ነው።
እነዚህን አራት አሜሪካዊያን ለማገት ቡድኑ ለምን እንደፈለገ ግን ለጊዜው ግልጽ የሆነ ነገር የለም።
አንዳንዶች ምናልባት በሁለት የማፍያ ቡድኖች መሀል በነበረ መታኮስና መቆራቆስ መሀል የአጋጣሚ ነገር ሆኖ ተገኝተው በስህተት የታፈኑ ሳይሆኑ እንዳልቀሩ ይገምታሉ።
የአሜሪካ ፌዴራል የምርመራ ቢሮ አሜሪካዊያኑን ከእገታ ለማስለቀቅ 50ሺ ዶላር አቅርቦ ነበር።
በታማውሊፓስ ግዛት የምትገኘው ማታሞሮስ ከተማ በሜክሲኮ ለደኅንነት ፍጹም አደገኛ ከሚባሉ ከተሞች አንዷ ናት።
የከተማዋ በርካታ ሰፈሮቿም በማፍያ ቡድኖች ቁጥጥር ሥር ነው ያሉት። በከተማዋ የሚገኘው ፖሊስ አቅሙ ከማፍያ ቡድኖቹ ያነሰ ነው።
የማፍያ ቡድኖቹ ዋንኛ መተዳደሪያም የኮኬይን ንግድ ነው።












