የሃዋይ ሰደድ እሳት ታሪካዊቷ ላሃይና ከተማን አወደማት

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በአውሎ ንፋስ ምክንያት የተቀሰቀሰው የከፋ የሰደድ እሳት በሃዋይ ማዊ ደሴት ላይ የምትገኘውን ታሪካዊቷ ላሃይና ከተማን አወደማት።
የግዛቲቷ የአሜሪካ ምክር ቤት አባል ብሪያን ሻትዝ ላሃይና “ሙሉ በሙሉ በእሳት ወድማለች” በማለት በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ጽፈዋል።
በማዊ ግዛት ቢያንስ ስድስት ሰዎች መገደላቸውን ባለስልጣናቱ ረቡዕ ዕለት ገልጸዋል።
የማዊ የጤና ማዕከላት የእሳት ቃጠሎ ጉዳት በደረሰባቸውና በጭስ በታፈኑ ህመምተኞች መጨናነቃቸው ተነግሯል።
“የእሳት አደጋ ሰራተኞች አሁንም እሳቱን ለመቆጣጠር እየሞከሩ ነው። የመጀመሪያ እርዳታ ሰጪዎችና ነፍስ አድን ሰራተኞችም በህይወት ያሉትን በመፈለግ ላይ ናቸው” ሲሉም ብሪያን ሻትዝ ተናግረዋል።
አንዳንድ ሰዎች በፍጥነት እየተንቀለቀለ እየተዛመተ ከነበረው የእሳት ነበልባል ለማምለጥ ወደ ውቅያኖስ ዘለው ስለመግባታቸው ረቡዕ ማለዳ ሪፖርት ተደርጓል።
የአሜሪካ የባህር ጠረፍ ጥበቃ ቢያንስ 12 ሰዎችን ከውቅያኖስ አውጥቶ መታደጉን አስታውቋል።
የማዊ ግዛት ከንቲባ ሪቻርድ ቢሰን ጁኒየር በበኩላቸው በርካታ መኖሪያ ቤቶች እና የንግድ ተቋማት ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን በአንድ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።
12 ሺህ ያህል ነዋሪዎች ባሉባት ላሃይና ከተማ ነዋሪ በከተማዋ ወደብ ያሉ ጀልባዎች እየተቃጠሉ መሆናቸውን ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።
“ከፊልም የተቆረጠ ትዕይንት ነው የሚመስለው። የጦርነት ፊልም” ሲሉም ክሪሲ ሎቪት የተባሉ ነዋሪ ለሃዋይ ኒውስ ናው ተናግረዋል።
በማዊ ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን በአሁኑ ወቅት በትክክል ለማወቅ አስቸጋሪ መሆኑን የገለጹት ባለስልጣናቱ የሟቾች ቁጥርም ሊጨምር እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
ወደ 2 ሺህ 100 የሚሆኑ ነዋሪዎችም ተፈናቅለዋል።
በላሃይና ነዋሪ የነበሩ ደብዛቸው የጠፋ የቤተሰብ አባላቶቻቸው ስጋት እንዳሳደረባቸው በርካቶች ተናግረዋል።












