ኡጋንዳ ባወጣችው ጸረ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ ሕግ ምክንያት የዓለም ባንክ ብድር አቆመ

የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ኡጋንዳ ጸረ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ ሕግ ማውጣቷን ተከትሎ የዓለም ባንክ አዲስ ብድር እንደማይሰጥ አስታወቀ።

የዓለም ባንክ ኡጋንዳ ያወጣችው ሕግ መሰረታዊ ከሆኑ እሴቶቼ ጋር ይቃረናል ብሏል።

በኡጋንዳ ከዚህ ቀደምም የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነቶች ሕገ ወጥ የነበሩ ሲሆን ግንቦት ላይ በጸደቀው አዲሱ ሕግ መሰረት ደግሞ የዕድሜ ልክ እስራት ይጠብቃቸዋል።

የዓለም ባንክ ለሁሉም ኡጋንዳውያን ያለምንም ልዩነት “ከድህነት እንዲወጡ፣ መሰረታዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ እና ሕይወታቸውን እንዲያሻሽሉ ለመርዳት” ቁርጠኛ መሆኑን ገልጿል።

ኡጋንዳ በበኩሏ የዓለም ባንክ የወሰደውን እርምጃ ኢፍትሃዊ እና ግብዝነት ነው ስትል አጣጥላዋለች።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኡጋንዳ አምባሳደር የገንዘብ ተቋሙን እርምጃ በጣም የከፋ ነው ብለዋል።

አምባሳደር አዶኒያ አየባሬ የዓለም ባንክ የአሰራር ዘዴ እና የቦርዱን ውሳኔ እንደገና የማጤን ጊዜው አሁን ነው ሲሉም በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።

ኡጋንዳ ተግባራዊ ያደረገችው የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ ሕግ፣ ከ18 ዓመት በታች ከሆነ ሰው የተመሳሳይ ጾታ ወሲባዊ ግንኙነት የፈጸመና የኤችአይቪ ቫይረስ በደሙ ከሚገኝበት ሰው ጋር ወሲብ የፈጸመ ላይ የሞት ቅጣትንም ጥሏል።

ሕጉ ከጸደቀ በኋላ አንድ ቡድን ወደ ኡጋንዳ አሰማርቶ የነበረው የዓለም ባንክ ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ ሕጉ “በመሰረታዊነት የዓለም ባንክ ቡድን እሴቶችን ይቃረናል” ብሏል።

የዓለም ባንክ ራዕይ “ዘር፣ ጾታ ወይንም ተመሳሳይ አፍቃሪነትን ሳይለይ” ሁሉንም ያካተተ እንደሆነም አትቷል።

በዚህም ምክንያት በሕጉ ውስጥ የተካተቱ አዳዲስ እርምጃዎች እስኪገመገሙ ድረስ “ለኡጋንዳ አዲስ ብድር እንዲጸድቅ ለሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አይቀርብም” ብሏል።

የዓለም ባንክ ውሳኔንም ተከትሎ የኡጋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዲኤታ ኦኬሎ እርምጃው ከሌሎች አገራት ጋር ሲወዳደር ወጥነት የለውም ሲሉ ተችተዋል።

“የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን የማይታገሱ በርካታ የመካከለኛው ምስራቅ አገራት አሉ። ተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎችንም የሚቀጡት በመስቀልና በመግደል ነው” ሲሉም መናገራቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

“በአሜሪካ ውስጥ በርካታ ግዛቶች የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን የሚቃወሙ ወይንም የሚገድቡ ሕጎችን አውጥተዋል። ታዲያ ለምን ኡጋንዳ ላይ አነጣጠራችሁ?” ሲሉም ጠይቀዋል።

ሕጉ አድሏዊ እንደሆነና የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ ዜጎችን መብት የሚጥስ ነው በሚል የኡጋንዳ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ሕጉ እንዲሻር ለፍርድ ቤት አቅርበዋል።

የፍርድ ሂደቱ መቼ እንደሚጀመር ግልጽ አይደለም።

ከዓለም ባንክ በተጨማሪ አሜሪካ በጸረ ተመሳሳይ አፍቃሪ ሕግ ምክንያት በኡጋንዳ ላይ ማዕቀብ ጥላለች።