የኢኳዶሩ ፕሬዚዳንታዊ እጩ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በጥይት ተመትተው ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በኢኳዶር በሚደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እጩ ተወዳዳሪ የሆኑት ፈርናንዶ ቪላቪሴንሲዮ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በጥይት ተመትተው ተገደሉ።
የአገሪቱ ብሔራዊ ምክር ቤት አባሉ ፈርናንዶ ረቡዕ ዕለት በሰሜናዊቷ ኪቶ ቅስቀሳቸውን እንደጨረሱ ነው ጥቃቱ የተፈጸመባቸው።
እጩው ፕሬዚዳንት መኪና ውስጥ እየገቡ በነበረበት ወቅት አንድ ግለሰብ ወደፊት ተጠግቶ ጭንቅላታቸውን በጥይት እንደመታውም የምርጫ ዘመቻው አባል ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።
የአገሪቱ የወቅቱ ፕሬዚዳንት ጉለርሞ ላሶ “ወንጀለኛውን ፈልገን ሳንቀጣው አናርፍም” ሲሉም ቃል ገብተዋል።
የ59 አመቱ ፖለቲከኛ በሦስት ጥይት ተመትተው መሞታቸውን የዓይን እማኞች ተናግረዋል።
ጥቃት ፈጻሚው ከደህንነቶች ጋር በነበረ የተኩስ ልውውጥ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን በኋላም ሕይወቱ ማለፉን የአገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በማኅበራዊ ሚዲያ አስታውቀዋል።
በጥቃቱ ሌላ የምክር ቤት እጩ ተወዳዳሪ እና ሁለት ፖሊሶችን ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎች ቆስለዋል ተብሏል።
የመጀመሪያው ዙር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከአስር ቀናት በኋላ እንዲካሄድም እቅድ ተይዞ ነበር።
በዘንድሮው ምርጫ ተወዳዳሪ የማይሆኑት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ላሶ ግድያው “እንዳስደነገጣቸውና ቁጣም እንደፈጠረባቸው” ተናግረዋል።
በተጨማሪም “የተደራጁ ወንጀሎች ይህንን ያህል ርቀት ተጉዞ እዚህ መድረሱን ገልጸው፣ ነገር ግን ሕግ ማስከበሩ ተፈጻሚ ይሆንባቸዋል” ሲሉም ተደምጠዋል።
በኢኳዶር ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ እያንሰራራ የመጣው የአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪ ወሮበላ ቡድኖች መበራከት የዘንድሮው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዘመቻም ዋነኛ ትኩረት ሆኗል።
ባለፈው ወር ከተደራጁ ወንጀሎች ጋር በተገናኘ በርካታ ግድያዎች መፈጸማቸውን ተከትሎም የአገሪቱ መንግሥት በሦስት ግዛቶች ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና የሰዓት እላፊ ገደብ ጥሏል።
የተገደሉት ፖለቲከኛ በምርጫ ዘመቻቸው በአገሪቱ ውስጥ የተንሰራፋውን ሙስና ለመቅረፍ መደረግ ያለበትን ጥረት አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
ጋዜጠኛ የነበሩት ፈርናንዶ ሙስናን ጨምሮ የአካባቢ ጥበቃ ላይ ባተኮሩ ዘገባዎቻቸው ይታወቃሉ። ባለፈው ሳምንት እሳቸውና የምርጫ ቅስቀሳ ቡድናቸው የአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪ ነው ከተባለ የወሮበሎች ቡድን መሪ ዛቻ እንደደረሳቸው ተናግረዋል።
ባለትዳር እና የአምስት ልጆች አባት የሆኑት ፈርናንዶ በአገሪቱ ውስጥ በሚደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከስምንት እጩዎች መካከል አንዱ ነበሩ።












