በጣሊያኗ ደሴት አቅራቢያ በደረሰ የጀልባ መስጠም አደጋ የ41 ስደተኞች ህይወት አለፈ

ስደተኞችን የጫነች ጀልባ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በጣሊያኗ ደሴት ላምፔዱሳ አቅራቢያ በደረሳ የጀልባ አደጋ የ41 ስደተኞች ህይወት አለፈ።

ከመስጠም አደጋ የተረፉ አራት ስደተኞች ጀልባዋ ከቱኒዝያዋ ስፋክስ ተነስታ ወደ ጣሊያን እያመራች እንደነበርም ለኃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።

ከአይቮሪኮስት እና ከጊኒ የመጡት አራቱ ስደተኞችም ረቡዕ ዕለት ላምፔዱሳ መድረሳቸውንም አስታውቀዋል።

በያዝነው የጎሮጎሳውያኑ ዓመት ከሰሜን አፍሪካ ወደ አውሮፓ ለማቋረጥ የሞከሩ ከ1 ሺህ 800 በላይ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

ከአደጋው የተረፉ ሶስት ወንዶች እና አንዲት ሴትና ሶስት ህጻናትን ጨምሮ ጀልባዋ 45 ስደተኞችን አሳፍራ እንደነበርም ግለሰቦቹ ለነፍስ አድን ሰራተኞቹ ተናግረዋል።

ሰባት ሜትር ርዝመት ያላት ጀልባ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ነበር የቱኒዝያዋን ስፋክስ ለቃ የወጣችው። በከፍተኛ ማዕበልም መመታቷንም ተከትሎ በሰዓታት ውስጥ የመስጠም አደጋ አጋጥሟታል።

በጀልባዋ ውስጥ ተሳፍረው ከነበሩ ስደተኞች መካከል 15ቱ ብቻ የህይወት አድን ልብስ ለብሰው እንደነበር ተገልጿል።

የዕቃ ጫኝ መርከብም የስደተኞቹን ህይወት የታደገች ሲሆን በጣሊያን ወደሚገኝ የባህር ጠረፍ ጠባቂ መርከብ መወሰዳቸውንም አክለዋል።

የጣሊያን የባህር ጠረፍ ጠባቂ ዕሁድ እለት በአካባቢው ሁለት ጀልባዎች የመስጠም አደጋ እንደገጠማቸው ሪፖርት ቢያደርግም አሁን አደጋ የደረሰባት ጀልባ አንዷ ስለመሆኗ የተገለጸ ነገር የለም።

ከላምፔዱሳ በ130 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የወደቧ ከተማ ስፋክስ በአውሮፓ የተሻለ ህይወትን ለሚሹ ስደተኞች መሸጋጋሪያ መሆኗን የቱኒዝያ ባለስልጣናት ተናግረዋል።

የጣሊያን ጠባቂ ጀልባዎች እና የበጎ አድራጎት ቡድኖች በላምፔዱሳ የደረሱ 2 ሺህ ስደተኞችን በቅርብ ቀናት ውስጥ መታደጋቸውን አስታውቀዋል።

በቅርብ ወራት ወዲህ በቱኒዝያ የዘረኝነት ጥቃቶች ተቀጣጥለው መቀጠላቸውን ተከትሎ በርካታ ስደተኞች አገሪቷን ለቀው ወደ አውሮፓ ለማቅናትም ሙከራ እያደረጉ ይገኛሉ።

ወደ አውሮፓ ለማቅናትም በሚደረገው ሙከራ ከጎሮጎሳውያኑ 2014 ጀምሮ በማዕከላዊ ሜድትራንያን ባህር ከ17 ሺህ በላይ ስደተኞች መሞታቸውንና መጥፋታቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መዝግቧል።