የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ አቋርጦት የነበረውን የምግብ ስርጭት በአነስተኛ መጠን ጀመረ

የዕርዳታ እህል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በኢትዮጵያ ከ20 ሚሊዮን የማያንሱ የዕርዳታ እህል ጠባቂዎች ይገኛሉ

የዓለም ምግብ ፕሮግራም የዕርዳታ ምግብ ለስርቆት መዳረጉን ተከትሎ በኢትዮጵያ አቋርጦት የነበረውን ስርጭት ዳግም በአስተኛ መጠን ለተጎጂዎች ማቅረብ ጀመረ።

ድርጅቱ የዕርዳታ ስርጭቱን ካቋረጠ ከሦስት ወራት በኋላ በአነስተኛ መጠን ስራውን ዳግም መጀመሩን ለአሶሲዬትድ ፕሬስ አስታውቋል።

የምግብ ድርጅቱ የዕርዳታ እህል ስርቆትን ተከትሎ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዕርዳታ ፈላጊዎች ባሉባት አገር ድጋፍ ማቆሙ በሰብዓዊ ድርጅቶች እና በጤና ባለሙያዎች ነቀፌታን አስከትሎበት ነበር።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም የዕርዳታ ስርጭቱን በአስተኛ መጠን በትግራይ ክልል የጀመረ ቢሆንም የአሜሪካ መንግሥት የሰብዓዊ ድርጅት የሆነው ዩኤስኤይዲ ግን የዕርዳታ ስርጭትን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት የስርዓት ማሻሻያ እንዲያደርግ የማደርገውን ድርድር ሳላጠናቅቅ ዕርዳታ አላቀርብም ብሏል።

ድርጅቱ የማቀርበው የምግብ ዕርዳታ ለታለመላቸው ሰዎች እንደሚደርስ እርግጠኛ ስሆን ስርጭቴን በተቻለ ፍጥነት ለመጀመር ዝግጁ ነኝ ስለማለቱ ኤፒ ጨምሮ ዘግቧል።

ለኢትዮጵያ ከሚቀርበው ዕርዳታ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዙት የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና ዩኤስኤይዲ የዕርዳታ ስርጭት በማቋረጣቸው ድጋፍ ጠባቂ የሆኑ 20 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን እና 800ሺህ ስደተኞችን ችግር ላይ ወድቀዋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም አዲስ የዘረጋውን የዕርዳታ ምግብ ስርጭት ቁጥጥር ለመፈተሽ ከሐምሌ 24/2015 ዓ.ም. ጀምሮ በትግራይ ክልል ባሉ 4 ወረዳዎች ለ100ሺህ ሰዎች ስንዴ እያደለ መሆኑን ለኤፒ ገልጿል።

ድርጅቱ የምግብ ዕርዳታ ስርጭቱ በሌሎች እጅ እንዳይገባ አዲስ ካስተዋወቃቸው የቁጥጥር ዘዴዎች መካከል ዕርዳታ ተቃባዮችን በዲጂታል ስርዓት መመዝገብ፣ የዕርዳታ እህል የያዙ ከቀረጢቶች ላይ ተጨማሪ ምልክት ማኖር፣ አስተያየት መቀበያ የስልክ መስመሮችን መክፈት እና ለአጋር ድርጅቶች ተጨማሪ ስልጣን መስጠትን የጨመረ ነው።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ይህ የቁጥጥር ስርዓት የዕርዳታ እህል ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ብቻ እንዲደርስ ያረጋግጣል የሚል እምነት ያለው ሲሆን የቁጥጥር ስርዓቱን በተቀረው የአገሪቱ ክፍሎች ለማስፋፋትም እቅድ እንዳለው ለኤፒ ገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካል የሆነው የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ መጠነ ሰፊ የዕርዳታ ምግብ ላልተገባ ዓላማ በመዋሉ የሚያቀርበውን የምግብ ዕርዳታ ሰኔ 02/2015 ዓ.ም. ማቋረጡ ይታወሳል።

የዕርዳታ እህል

የፎቶው ባለመብት, AFP

በረሃብ ለተጎዱ ሰዎች የተላከ ዕርዳታ በከፍተኛ ሁኔታ ዝርፊያ ተፈጽሞበታል፣ እንዲሁም ለሽያጭ ገበያ ላይ ውሏል በሚል የአሜሪካ መንግሥት የዓለም አቀፍ ልማት ተራድኦ ድርጅትም (ዩኤስኤአይዲ) ተመሳሳይ እርምጃ መውሰዱ ይታወሳል።

የዕርዳታ ምግብ ስርቆቱን በተመለከት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ባደረገው ምርመራ ከዕርዳታ እህል ስርቆት ጋር በተያያዘ የፌደራል መንግሥት አካላት እና የኤርትራ ኃይሎች ሰፊ ሚና አላቸው ብሎ ነበር።

ይህንን ክስ በተመለከተ የፌደራል መንግሥቱም ሆነ የኤርትራ መንግሥት የሰጡት ምላሽ የለም።

የምርመራ ኮሚቴው አስተባባሪ እና የትግራይ ክልል የሰላም እና የፀጥታ ቢሮ ጊዜያዊ ኃላፊ ጄኔራል ፍስሐ ኪዳኔ ለትግራይ ቴሌቪዥን ሲናገሩ ዕርዳታውን ላልተገባ ዓላማ እንዲውል የትግራይ ክልል ባለሥልጣናት፣ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ አስተባባሪዎች እና የዕርዳታ ሠራተኞችም ተሳትፈውበታል ብለው ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የምግብ ዕርዳታ ስርጭት መቋረጥን የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃውሞ ነበር።

ዩኤስኤአይዲ የዕርዳታ አቅርቦት ማቋረጡን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት በዩኤስኤአይዲ የተደረሰው ውሳኔ ‘ፖለቲካዊ’ ነው ሲል አጣጥሎት ነበር።

የኢትዮጵያ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ዕርዳታ የማቋረጥ ውሳኔ በተሰጠ በሳምንቱ እርምጃው “የጅምላ ውሳኔ” መሆኑን በመግለጽ፣ ሚሊዮኖችን መቅጣት “ፖለቲካዊ እንጂ ሰብአዊ ገጽታ የለውም” ብለው ነበር።