ሊባኖስን አለም አቀፉ ማህበረሰብ እንደረሳት የአገሪቱ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ተናገሩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ፉአድ ሲኖራ

ከእስራኤል ጋር በነበረው የአውሮፓውያኑ 2006 የመጨረሻ ጦርነት ወቅት የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አገራቸውን አለም አቀፉ ማህበረሰብ እንደረሳት ለቢቢሲ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ፉአድ ሲኖራ ሊባኖስ እንድትንኮታኮት መደረጓ ተቀባይነት እንደሌለው እና በአገሪቱ ሰላምን ለማስፈን ተነሳሽነት የለም ሲሉ ወቅሰዋል።

“በአሁኑ ወቅት የአገር ውስጥ፣ የአረቡ ዓለም እና በአለም አቀፍ ደረጃ እውነተኛ ጥረት የሚሻ ከባድ ፈተና ውስጥ እንገኛለን” ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

“ሁኔታዎች ምን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ በቅጡ ሳይረዱ ወደ ውድቀት አፋፍ እንዲሁም ወደ ቀውስ ውስጥ ሊገባ ይችላል” ያሉት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገራቸው በዚህ ውጥንቅጥ ውስጥ ያለችው የአሜሪካ አስተዳደር በራሱ ምርጫ በተጠመደበት ወቅት መሆኑን አስታውሰዋል።

“አገራችን ፕሬዚዳንት መምረጥ አልቻለችም ምክንያቱም በአገሪቱ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ቡድኖች በተለይም ሄዝቦላህ ከጀርባው የማይወጋው ፕሬዚዳንት አንፈልግም የሚል አቋም በጽኑ በመያዛቸው ምርጫ እንዳይካሄድ እንቅፋት ሆኗል” ሲሉ አስረድተዋል።

ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት የተደረገው የእስራኤል እና የሊባኖስ የመጨረሻ ጦርነት የተጀመረው የሄዝቦላህ ተዋጊዎች ድንበር ጥሰው የእስራኤል ወታደሮች ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን ተከትሎ ነው። በዚህም ጥቃት ሶስት ወታደሮች ሲገደሉ፣ ሁለት ወታደሮች ታግተው ለወር ወደዘለቀ ግጭት አገራቱን መርቷቸው ነበር።

በዚህ ወቅት በነበሩት ቀጣይ ቀናት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሊባኖስ መንግሥት ከተከሰተው ጥቃት ራሱን በማራቅ በይፋ መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል።

አሁን ያሉት የአገሪቱ የወቅቱ መሪዎች ተመሳሳይ ነገር ባለማድረጋቸው ህዝባቸውን ለመጥፎ ሁኔታዎች አጋልጠዋል ሲሉ ተችተዋል።

“የአሁኑ አስተዳደር በወቅቱ እንደነበረው እንደኔ መንግሥት አላደረገም። መንግሥቴ ሄዝቦላህ ድንበር አቋርጦ የእስራኤል ወታደሮችን እንደሚገድል እና እንደሚያግት መረጃው እንዳልነበረን እንዲሁም እንዳልተነገረን በግልጽ እስረግጠን አስረድተናል” ብለዋል።

“በዚህ ወቅት ግን የሊባኖስ መንግሥት ተመሳሳይ እርምጃ ሊወስድ አልቻለም። በወቅቱ ያደረግነው ነገር የጠቀመን የሊባኖስ መንግሥት እና ሊባኖስ በአንድ በኩል እንዲሁም በሌላ በኩል በሄዝቦላህ መካከል ልዩነት እንዲኖር ማድረግ ችሏል” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገራቸው ሉዓላዊነት ጥያቄ ውስጥ እንደገባ ያለምንም ማመንታት ነው አስተያየታቸውን የሰጡት።

ሊባኖስ በሄዝቦላህ ታግታለች ያሉት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ከሄዝቦላህ ጀርባ ደግሞ ኢራን አለች ብለዋል።

ሄዝቦላህ በኢራን በኩል በሶሪያ፣ በኢራቅ እና በየመን ጦርነቶች ተሳታፊ እየሆነ እንደመጣ ተናግረው ሊባኖስ በነዚህ ጦርነቶች ተሳታፊ ልትሆን አይገባም ብለዋል።