የአቶ ጌታቸው አስተዳደር በእነ ደብረ ጽዮን ቡድን ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራው የህወሓት ቡድን በክልሉ ውስጥ ሕግ እየጣሰ በመሆኑ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ።
ይህ የጊዜያዊ አስተዳደሩ መግለጫ የወጣው በደብረ ጽዮን (ዶ/ር) የሚመራው የህወሓት ቡድን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት እና ሌሎች የክልሉን ባለሥልጣናት ከኃላፊነታቸው ማንሳቱን በተመለከተ መግለጫ መውጣቱን ተከትሎ ነው።
ይህን የጊዜያዊ አስተዳደሩን ካቢኔ እና የዞን አመራሮችን ከኃላፊነት የማንሳት ውሳኔን ሕገወጥ ከማለት ባሻገር “የመንግሥት ግልበጣ” ነው ያለው ከፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት የወጣው መግለጫ፣ የደብረ ጽዮን ቡድን የጊዜያዊ አስተዳደሩን ስም የሚያጠፋ ያልተቋረጠ ዘመቻ እያካሄደ ነው ሲል ከሷል።
ሰኞ መስከረም 27/2017 ዓ.ም. ከአንድ ወር በፊት ሕገወጥ የተባለ ጠቅላላ ጉባኤ ያካሄደው እና ደብረጽዮንን በሊቀመንበርነት የመረጠው የህወሓት ቡድን ባወጣው መግለጫ፣ አቶ ጌታቸውን ጨምሮ የጊዜያዊ አስተዳደሩ የካቢኔ አባላትን፣ የቢሮ ኃላፊዎችን እና የዞን አስተዳዳሪዎችን ከኃላፊነት ማንሳቱን አሳውቋል።
በህወሓት አመራሮች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ በተካሄደው እና በምርጫ ቦርድ ዕውቅና ባልተሰጠው እንዲሁም ከፊል አመራሮቹ እና አባላቱ ባልደገፉት ጠቅላላ ጉባኤ ምክንያት በፓርቲው ውስጥ ክፍፍል መፈጠሩ ይታወሳል።
በጠቅላላ ጉባኤው ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል በሊቀመንበርነታቸው እንዲቀጥሉ መመረጣቸው የተገለጸ ሲሆን፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸውን ጨምሮ በህወሓት የአመራርነት ቦታ ላይ የነበሩ እና ጉባኤውን ተቃውመው ያልተሳተፉት ከኃላፊነት ከመነሳታቸው በተጨማሪ ከአባላነት ታግደዋል።
በዚህም ምክንያት በህወሓት ውክልና በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አመራርነት ቦታ ላይ የተቀመጡት ግለሰቦች ከድርጅቱ በመታገዳቸው ኃላፊነታቸውን እንዲለቁ እንደሚደረግ የደብረ ጽዮን ቡድን ሲገልጽ ቆይቷል።
አሁን በወጣው መግለጫ አቶ ጌታቸውን ጨምሮ በተለያዩ ደረጃዎች ላይ የሚገኙ የጊዜያዊ አስተዳሩ ባለሥልጣናትን አንስቶ ከፕሬዝዳንቱ በስተቀር ሌሎቹን የሚተኩ ግለሰቦችን ስም ይፋ አድርጓል።
ይህንን ተከትሎም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ሰኞ ምሽት ላይ ባወጣው መግለጫ የደብረ ጽዮን ቡድን ባወጣው መግለጫ ያሳወቀው ሹም ሽር “ይፋዊ የመንግሥት ግልበጣ” ነው በማለት ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል።
“የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲህ ያለውን ድርጊት አይቀበለውም ያለው” መግለጫው በዚህም ሳቢያ አስተዳደሩ “የጥፋት ኃይሎች” ባላቸው የቡድኑ መሪዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ገልጿል።
“በዚህም ሳቢያም በሂደቱ ለሚከሰት ለማንኛውም ዓይነት ጉዳት በዋናነት ይህ ቡድን እና አመራሩ ተጠያቂ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለመላው ሕዝብ ልናሳውቅ እንወዳለን” ብሏል በመግለጫው።
ነገር ግን ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ከአቶ ጌታቸው ረዳ ጽህፈት ቤት የወጣው መግለጫ ይወሰዳል የተባለው እርምጃ ምን ሊሆን እንደሚችል ያለው ነገር የለም።
በሁለቱ ወገኖች መካከል የተከሰተው አለመግባባት ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ በትግራይ ክልል ብቸኛው የፖለቲካ ኃይል ሆኖ በቆየው ህወሓት ውስጥ ከፍፍል ፈጥሯል።
ለሁለት ዓመታት የተካሄደውን ደም አፋሳሽ ጦርነትን ተከትሎ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በመስማማት የተቋቋመው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ሳይጠናከር ነው በህወሓት ውስጥ አለመግባባት የተፈጠው።
በህወሓት ውስጥ የተፈጠረው ውዝግብ በሁለት ጎራ የተቧደኑ አመራሮቹን በተለይም በፓርቲው 14ኛ ጉባኤ መካሄድ ዙሪያ እንዳይስማሙ አድርጓቸዋል። በቀውስ መካከል የተካሄደው የድርጅቱ ጉባኤ በፓርቲው ላይ ብቻ ሳይሆን በጊዜያዊ አስተዳደሩ ላይም ጫና አሳድሯል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጉባኤው ተቀባይነት የለውም ከማለቱ በተጨማሪ በአቶ ጌታቸው ወገን ያሉት የህወሓት አመራሮች እና አባላት ሳይቀሩ ጉባኤውን ሕገወጥ ቢሉትም አቶ ጌታቸውን ከምክትል ሊቀመንበርነት አንስቷቸው ደብረ ጽዮንን በሊቀመንበርነት እንዲቀጥሉ አድርጓል።
የደብረ ጽዮን ቡድን የጊዜያዊ አስተዳደሩን ባለሥልጣናት ከቦታቸው መነሳታቸውን ገልጾ የሚተኳቸውን ግለሰቦች የሰየመ ሲሆን፣ በአቶ ጌታቸው ቦታ ተተኪ ለማስቀመጥ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በመነጋገር ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል። ይህንን በሚመለከት ግን ከፌደራል መንግሥቱ በኩል እስካሁን የተባለ ነገር የለም።












