ከሥልጣን የሚለቁ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንቶች ምን ዓይነት መብት እና ጥቅሞች ይኖሯቸዋል?

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝደንቶች - ነጋሶ ጊዳዳ፣ ግርማ ወልደጊዮርጊስ፣ ሙላቱ ተሾመ እና የወቅቱ ፕሬዝደንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ

ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ዛሬ ሰኞ መስከረም 27/2017 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ ለስድስት ዓመት የቆዩበትን ሥልጣን ለአምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ አስረክበዋል። የመሰናበቻ ንግግር ያላደረጉት የቀድሞዋ ፕሬዝዳንት ከመንበራቸው የተሰናበቱበት ምክንያትን በተመለከተ የተባለ ነገር የለም።

ሳህለ ወርቅ ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት ከስድስት ዓመት በፊት ጥቅምት አጋማሽ 2011 ዓ.ም ነበር። የአገሪቱ ሕገ መንግሥት “የፕሬዝዳንቱ የሥራ ዘመን ስድስት ዓመት ይሆናል። አንድ ሰው ከሁለት ጊዜ በላይ ለፕሬዝዳንትነት ሊመረጥ አይችልም” ሲል ይደነግጋል።

ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በመንበራቸው ላይ እንደማይቀጥሉ ሲነገር የነበረ ሲሆን፣ የቅርብ ሰዎቻቸውም ፕሬዝዳንቷ ለሁለተኛ ዙር የሥልጣን ዘመን በኃላፊነታቸው ሊቀጥሉ እንደማይችሉ ለቢቢሲ ፍንጭ ሰጥተው ነበር።

ፕሬዝዳንቷ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በኤክስ ገጻቸው ያጋሩት መልዕክትም ብዙዎችን ግራ ያጋባ ነበር። የርዕሰ ብሔሯ መልዕክት መደምደሚያ “እንደከፋቸው” እና “መሄጃ መውጫ” እንደጠፋቸው፤ ለዚህም መልሳቸው “ዝምታ” መሆኑን ይጠቁማል። በአጭር ጽሁፋቸው ማጠቃለያ ላይም ይህንን የዝምታ አማራጭ “ለአንድ ዓመት” እንደሞከሩት ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቷ የሥራ ዘመናቸው ተጠናቆ ለሁለተኛ ጊዜ በፕሬዝዳንትነት የማይቀጥሉ ከሆነ ምን ዓይነት መብቶች እና ጥቅማጥቅሞች ይኖሯቸዋል?

ከ16 ዓመት በፊት ከኃላፊነት የተነሱ የአገር እና የመንግሥት መሪዎችን፣ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎችን የምክር ቤት አባላት እና ዳኞች የሚያገኟቸውን መብቶች እና ጥቅሞች ለመወሰን አዋጅ ወጥቷል።

“የአገር እና የመንግሥት መሪዎች፣ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የምክር ቤት አባላት እና ዳኞች ሕዝባዊ አደራ በመሸከም ለአገር እና ለሕዝብ ጥቅም የሚሰሩ በመሆናቸው ከኃላፊነት ሲነሱ ከጉስቁልና የራቀ ኑሮ እንዲኖሩ ማድረግ እና ለጥቃት ተጋላጭ እንዳይሆኑ ጥበቃ እና ከለላ መስጠት አስፈላጊ በመሆኑ” አዋጁ መውጣቱ በመግቢያው ላይ ሰፍሯል።

አዋጁ ከኃላፊነት የተነሱ ጠቅላይ ሚኒስትር እና ፕሬዝዳንትን የሚኖራቸውን መብት እና የሚያገኙትን ጥቅማጥቅም በዝርዝር ያትታል። ከኃላፊነት የተነሳ/ች ፕሬዝዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር በአዋጁ መሠረት ያላቸው ጥቅማ ጥቅም ተመሳሳይ ነው።

በአዋጁ መሠረት ከኃላፊነት የተነሳ/ች ፕሬዝዳንት በኃላፊነት ላይ በነበሩበት ጊዜ ይከፈላቸው የነበረው የወር ደመወዝ እና አበል ከኃላፊነት ከተነሱ በኋላም አይቋረጥም። ከዚህ በተጨማሪ በሥራ ላይ ላሉ ፕሬዝዳንት የደመወዝ እና የአበል ማስተካከያ ሲደረግ ከኃላፊነት የተነሱትም ፕሬዝዳንት የማስተካከያው ተጠቃሚ ይሆናሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይኸው አዋጅ ከኃላፊነቱ የሚነሳ/የምትነሳ ፕሬዝዳንት “ለራሳቸው እና ለቤተሰባቸው መኖሪያነት የሚያገለግል የሠራተኞችን ደመወዝን ጨምሮ በመንግሥት ወጪ የሚተዳደር ከአራት እስከ አምስት መኝታ ክፍሎች ያሉት መኖሪያ ቤቶች ይሰጣቸዋል” ይላል።

ከኃላፊነት የተነሱ ፕሬዝዳንት እና ቤተሰባቸው በመንግሥት ወጪ በአገር ውስጥ እንዲሁም በውጭ አገር የህክምና አገልግሎት ያገኛሉ። የህክምና አገልግሎቱ እንደ ሁኔታው በመንግሥት ወይም በግል የጤና ተቋም እንደሚሰጥ የሚጠቅሰው አዋጁ፤ “ባለመብቱ እና ቤተሰቡ በአገር ውስጥ የጤና ተቋም ተኝተው ሲታከሙ ሕክምና የሚሰጠው በአንደኛ ደረጃ ማዕረግ ይሆናል” ሲል ያትታል።

ከዚህ በተጨማሪ ከኃላፊነት የሚነሱ ፕሬዝዳንት የራሳቸውን እና የቤተሰባቸውን የግል ደኅንነት የሚጠብቁ ጠባቂዎች ይመደቡላቸዋል። የሚመደበው የጥበቃ ኃይል ዓይነት እና መጠን ጥበቃውን በሚያካሂደው አካል እንደሚወሰን አዋጁ ላይ ሰፍሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የተቋቋመው የሪፐብሊካን ጋርድ ከኃላፊነት ለተነሱ ፕሬዝዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጥበቃ የማድረግ ኃላፊነት በማቋቋሚያ ደንቡ ተሰጥቶታል።

ከፕሮቶኮል ጋር በተያያዘ ኃላፊነት የተነሱ ፕሬዝዳንት የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት፣ የቪ.አይ.ፒ አገልግሎት እና ቀድሞ የነበራቸውን ኃላፊነት የሚመጥን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር ሙሉ የፕሮቶኮል አገልግሎት እንደሚያገኙ አዋጁ ይደነግጋል።

በአዋጁ መሠረት የቀድሞው ፕሬዝዳንት “ደረጃቸውን የጠበቁ ሦስት ለመጓጓዣ የሚያገለግሉ የመንግሥት” ተሽከርካሪዎች ይመደቡላቸዋል። የአሽከርካሪ ደመወዝ፣ የነዳጅ እና የጥገና ወጪዎች በመንግሥት እንደሚሸፈን አዋጁ ያስቀምጣል።

ከኃላፊነት የተነሱት ፕሬዝዳንት ወጪው በመንግሥት የሚሸፈን ሁለት መደበኛ ስልኮች በመኖሪያ ቤት ውስጥ እና አንድ ተንቀሳቃሽ ስልክ ይኖራቸዋል። ፕሬዝዳንቱ/ቷ ከኃላፊነት ከተነሱ በኋላ በሕዝባዊ አገልግሎቶች ላይ የሚሰማሩ ከሆነ የመኖሪያ ቤታቸው በሚገኝበት ከተማ የቢሮ አገልግሎት እንደሚሰጣቸው አዋጁ ላይ ሰፍሯል።

ከዚህ በተጨማሪም ራሳቸው የሚመርጧቸው እና መንግሥት ደመወዛቸውን የሚከፍላቸው አንድ ፀሐፊ እና አንድ ባለሙያ ይኖራቸዋል። በአዋጁ መሠረት ለቢሮው የሚያስፈልጉ ኮምፒውተር፣ ስልክ፣ ኢንተርኔት፣ ፖስታ እና የመሳሰሉትን መንግሥት ያሟላል።

ተሰናባቹ/ቿ ፕሬዝዳንት ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ፤ “በሞት መለየታቸውን በመገናኛ ብዙኃን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይነገራል” እንዲሁም “በመላው አገሪቱ የአንድ ቀን ብሔራዊ የሐዘን ቀን ይታወጃል” ሲል አዋጁ ያትታል።

የዚህ መብት ተጠቃሚ የሆነ/ች ፕሬዝዳንት ከዚህ ዓለም በሞት መለየት፤ “ለቤተሰባቸው የሚሰጡትን የመኖሪያ ቤት፣ የሕክምና እና የግል ደኅንነት ጥበቃ አገልግሎቶች አያቋርጥም” ሲል አዋጁ ደንግጓል።

የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት የነበሩት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ሥልጣን ከለቀቁ በኋላ የሚገባቸውን ጥቅማጥቅሞች ያገኙት ለአራት ዓመታት ብቻ ነበር። በግል ተወዳድረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ከሆኑ በኋላ ጥቅማ ጥቅማቸው ተቋርጦ ነበር።

ከስድስት ዓመታት በፊት የቀድሞው የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን እንዲያገኙ ወስኖ እንደነበር ይታወሳል። ዶክተር ነጋሶ ለዓመታት ይተዳደሩበት የነበረው የጡረታ ደመወዝ በወር 2295 ነው።

ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ ለሰባት ዓመታት ፕሬዝዳንት ሆነው ያገለገሉት ዶ/ር ነጋሶ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት በ2011 ዓ.ም ወርሃ ሚያዚያ ላይ ነበር።

ከእሳቸው በመከተል ደግሞ መቶ አለቃ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ በፕሬዝዳንትነት ለሁለት የሥልጣን ዘመን ያገለገሉ ሲሆን፣ ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ደግሞ ሦስተኛው የሪፐብሊኩ ፕሬዝዳንት እንደነበሩ ይታወሳል።

በመጀመሪያው ዙር የሥልጣን ዘመናቸው ማብቂያ ላይ ቅሬታቸውን የገለጹት እና በፕሬዝዳንትነት እንደማይቀጥሉ የተነገረላቸው ሳህለ ወርቅ ዘውዴ እንደተባለው ከመንበራቸው የሚለቁ ከሆነ ከላይ ለአገለግሎታቸው የተጠቀሱት ጥቅማጥቆሞች ይከበሩላቸዋል።