የኤሲ ሚላኑ ግብ ጠባቂ በደረሰበት የዘረኝነት ጥቃት ሜዳ ጥሎ ወጣ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በጣሊያን ሴሪ ኤ ኤሲ ሚላን ከዩዲኒዜ ያደረጉት ጨዋታ የሚላኑ በረኛ በደረሰበት ጥቃት ምክንያት ለጥቂት ደቂቃዎች ተቋርጧል።
የኤሲ ሚላኑ በረኛ ማይክ ማኞን ከዩዲኒዜ ደጋፊዎች ዘረኛ ጥቃት ደርሶብኛል ብሏል።
በረኛው ከእረፍት መልስ የዘረኝነት ጥቃት እየደረሰበት እንዳለ ለዳኛው ጠቁሞ ሜዳውን ለቆ ሲወጣ የቡድን አጋሮቹ ተከትለውታል።
የሚላኑ አማካይ ሩበን ሎፍተስ ቺክ የመጀመሪያዋን ጎል ካስቆጠረ ከደቂቃዎች በኋላ ነው ይህ የሆነው።
ጨዋታው ከተቋረጠ ከ10 ደቂቃ በኋላ ድጋሚ ተጀምሯል።
“እግር ኳስ እንደዚህ እየተጫወትን ልንቀጥል አንችልም። ይህ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም” ሲል ሚኞን ለስካይ ስፖርት ኢታሊያ አስተያየቱን ሰጥቷል።
ፈረንሳዊው በረኛ “ከባድ ቅጣት ሊጣል ይገባል። ምክንያቱም ማውራታችን ብቻ ምንም ፋይዳ እንደሌለው እያየን ነው” ብሏል።
ሚኞን “ገና ጨዋታው ሲጀመር የዝንጀሮ ድምፅ ከደጋፊዎች ሰማሁ፤ ነገር ግን ምንም አላልኩም” ሲል ስለሁኔታው ይናገራል።
“ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ኳሷ ስቀርብ ይህን ድምፅ ድጋሚ ሰማሁት። ይሄኔ ነው ለአራተኛው ዳኛ እና ለቡድን አጋሮቼ ሁኔታውን ያሳወቅሁት።”
ግብ ጠባቂው አክሎ “በጣም ተናድጄ ነበር። መጫወት አልፈግኩም ነበር። ነገር ግን ይህ ቤተሰቤ ነው። ቤተሰቤን ጥዬ መሄድ አልፈቀድኩም” ይላል።
ኤሲ ሚላን በቀድሞው ትዊተር በአሁኑ ኤክስ ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት “ዘረኝነት በእግር ኳስ ቦታ የለውም። እጅግ አዝነናል። ማይክ፤ እኛ ካንተ ጋር ነን” ብሏል።
ሊጉን እየመሩ ያሉት ኢንተር ሚላን ደሞግ “እኛ የዚህች ዓለም ወንድማማቾች ነን። ማንኛውንም ዓይነት መገለል እንቃወማለን። ከጎንህ ነን” የሚል መልዕክት አስፍረዋል።
ከጨዋታው በኋላ በርካታ የቀድሞ እና የአሁን ተጫዋቾች በማሕበራዊ ሚድያ ገፆቻቸው የተፈጠረውን ክስተት አውግዘዋል።
የቀድሞው የአርሰናል እና የእንግሊዝ አጥቂ ኢያን ራይት ፈረንሳዊው ግብ ጠባቂ ላይ የደረሰውን የዘረኝነት ጥቃት ካወገዙት መካከል ነው።
ሴሪ አውም እንዲሁ “ማንኛውንም ዓይነት ዘረኝነት እንቃወማለን” ብሏል።
የ28 ዓመቱ የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን እና የኤሲ ሚላን ግብ ጠባቂ “ሁሉም ደጋፊዎች ባይሆኑም ይህን ያደረጉ ሰዎች ትክክል አለመሆናቸው ሊነገራቸው ይገባል” ብሏል።
ኢንተር ሚላን ጨዋታው ድጋሚ ከተጀመረ በኋላ በተቆጠሩበት ሁለት ጎሎች ቢመራም የኋላ ኋላ ድል መጎናፀፍ ችሏል።
ተቀይሮ የገባው ሉካ ጆቪች እና ኖዋህ ኦካፎር ባስቆጠሯቸው ጎሎች ሚላን ጨዋታውን 3-2 አሸንፏል።
አሴ ሚላን በስድስት ነጥቦች ከመሪው ኢንተር ሚላን ርቆ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ጁቬንቱስ እና ኢንተር ቀሪ አንድ ጨዋታ አላቸው።












