የሱዳን ተዋጊ ጀነራሎች ለዘላቂ ሰላም ድርድር የማድረግ ፍላጎት እንደሌላቸው ተነገረ

ለሥልጣን ሸሚያ እየተፋለሙ ያሉት ሁለቱ የሱዳን ጦር ጀነራሎች ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ድርድር የማድረግ ፍላጎት እንደሌላቸው ተገለጸ።
የተባበሩት መንግሥታት የሱዳን ልዩ መልዕክተኛ ቮልከር ፐርዝስ ለተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ሁለቱ ተዋጊ ኃይሎች በዘላቂነት ልዩነቶቻቸውን ለመፍታት ለድርድር የመቀመጥ ፍላጎት የላቸውም ሲሉ ተናግረዋል።
ልዩ መልዕክተኛው በአሜሪካ አደራዳሪነት የተደረሰው የ72 ሰዓታት የተኩስ አቁም ስምምነት በበርካታ የአገሪቱ ከፍሎች ተፈጻሚ እየሆነ እንደሆነም ተናግረዋል።
12ኛ ቀኑን ባስቆጠረው ግጭት በጀነራል አልብዱል ፋታህ አል ቡርሃን የሚመራው መደበኛው የአገሪቱ ጦር በጀነራል መሐመድ ዳጋሎ (ሄሜቲ) ከሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይል ጋር ሲዋጋ ቆይቷል።
በዚህ ግጭት ምክንያት ከ450 ያላነሱ ሰላማዊ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን የተፈጠረው ቀውስ የሱዳንን የወደፊት እጣ ፈንታ ጥያቄ ውስጥ የከተተ ሆኗል።
ጀነራል አል ቡርሃን እና ጀነራል ሄሜቲ ልዩነቶቻቸውን በንግግር እንዲፈቱ የቀጠናው አገራት፣ የአረብ እና ምዕራባውያን አገራት ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም ግጭቱ እንደቀጠለ ነው።
የተመድ የሱዳን ልዩ መልዕክተኛው አንዳቸው ሌላኛውን በጦር ማሸነፍ እንችላለን ብለው ስለሚያስቡ በዘላቂነት ልዩነትን ለመፍታት ለድርድር የመቀመጥ ፍላጎት እያሳዩ አይደለም ብለዋል።
በሱዳን የሚገኙት ቮልከር ፐርዝስ ሰኞ እኩለ ለሊት ጀምሮ ለ72 ሰዓታት ተግባራዊ ለማድረድ የተሞከረው የተኩስ አቁም ስምምነት ግጭት እንዲቀንስ ቢያደርግም በካርቱም እና ኦማዱሩማን የተኩስ እና የፍንዳታ ድምጽ ይሰማል ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ምዕራባውያን አገራት ዜጎቻቸውን ከሱዳን ማስወጣታቸውን ቀጥለዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም በሁለተኛው ዙር ከሱዳን በአየር ያስወጣቻቸው ዜጎቿ ሳይፕረስ ደርሰዋል።
በመርከብ አማካይነት ከሱዳን የተነሱ የበርካታ አገራት ዜጎች የሆኑ 1600 ሰዎች ደግሞ ሳዑዲ አረቢያ ደርሰዋል።
የአገሪቱ ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሉ ግጭት ውስጥ ከገቡ በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳንን ጥለው መሸሻቸውን የተገለጸ ሲሆን ተመድ አገራቸው ጥለው የሚሰደዱ ሱዳናውያን ቁጥር ሊጨምር ይችላል ሲል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።
በግጭቱ ምክንያት የጤና ተቋማት በወደሙባት እና በተጨናነቁባት ካርቱም በቀጣይ ሳምንታት ሊወልዱ የሚችሉ ወደ 24ሺህ የሚጠጉ ነፍሰ ጡሮች እጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል አሳሳቢ ሆኗል።












