ታሊባን የካቡል አየር ማረፊያ ፍንዳታን ያቀነባበረውን የአይኤስ መሪን ገደለ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የኢስላሚክ ስቴት ቡድን አመራር እና ከሁለት ኣመት በፊት በአፍጋን ዋና ከተማ ካቡል ውስጥ በሚገኘው አየር ማረፊያ ላይ የተፈጸመውን ፍንዳታ ያቀነባበረውን ግለሰብ መግደሉን ታሊባን ገለጸ።
አሜሪካም ይህ ግለሰብ በታሊባን መገደሉን አረጋግጫለሁ ብላለች።
በነሐሴ 2021 በደረሰው በዚህ የካቡል አየር ማረፊያ ፍንዳታ 170 ሰላማዊ ሰዎች ሲገደሉ፣ 13 የአሜሪካ ወታደሮችም ሞተዋል።
ይህ ጥቃት የተፈጸመው ታሊባን ወደ ካቡል ሲገባ እና አሜሪካውያን ከአፍጋኒስታን በጥድፊያ እየወጡ በነበረበት ወቅት ነው።
በወቅቱ በርካታ አፍጋኒስታናውያን አገር ለመልቀቅ በአየር ማረፊያው ተገኝተው ነበር።
ይህ የኢስላሚስ ስቴት (አይኤስ) ከፍተኛ አመራር የተገደለው ከሳምንት በፊት ቢሆንም መሞቱ በአሜሪካ የተረጋገጠው ግን ትናንት ማክሰኞ ነው ሲሉ ባለሥልጣናት ለቢቢሲ አጋር ሚዲያ ሲቢኤስ ተናግረዋል።
የዚህ ግለሰብ ስም ለጊዜው ይፋ አልሆነም።
ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው ደግሞ ይህ ግለሰብ መገደሉን አሜሪካ ያወቀችው በሚያዝያ ወር መጀመሪያ ላይ ቢሆንም ማን እንደገደለው፣ በምን ሁኔታ እንደተገደለ የጠራ መረጃ ለጊዜው አልተገኝም ወይም ይፋ አልሆነም።
ይሁንና ከትናንት በስቲያ ሰኞ የአሜሪካ ባለሥልጣናት በዚህ የካቡል ጥቃት ቤተሰቦቻቸው የተገደሉባቸውን አሜሪካውያንን ጥቃት አድራሹ መገደሉን አብስረዋቸዋል።
ይህ ጥቃት የተፈጸመው በርካታ የምዕራብ አገራት ዜጎቻቸው በፍጥነት ከካቡል አየር ማረፊያ እንዲርቁ፣ የተሸረበ የቦምብ ጥቃት ሊኖር እንደሚችል ባስጠነቀቁ በሰዓታት ውስጥ ነበር።
ለጥቃቱ ኃላፊነቱን የወሰደው ደግሞ አይኤስ-ኬ በሚል የእንግሊዝኛ ምህጻር ቃል የሚጠራው የኢስላሚክ ስቴት የካቡል ቅርንጫፍ ነበር።
ይህ ጥቃት በፈረንጆች ነሐሴ 26/2021 በአየር መንገዱ መግቢያ በር ላይ የተፈጸመ ሲሆን፣ በርካታ ቤተሰቦች ወደ አየር ማረፊያው ለመግባት በሚጠብቁበት የአቤይ በር ላይ ነበር አጥፍቶ ጠፊው ድንገት ዘው ብሎ በመግባት ራሱን እና በመቶ የሚቀጠሩ ሰዎችን ያጠፋው።
በወቅቱ አሜሪካ አፍጋኒስታንን እየለቀቀች ስለነበረ በርካታ አፍጋኒስታናውያን ከአገር ለመውጣት እዚያ የነበሩ አሜሪካውያንን በመማጸን ላይ ነበሩ።
አብሮ ለመውጣትም በርካታ ግፊያዎች መተረማመሶች ይታዩ ነበር።
ጥቃት ከደረሰባቸው የአገሬው ዜጎች ሌላ ሁለት የዩናይትድ ኪንግደም ዜግነት ያላቸው እና አንድ ሌላ ሕጻን ይገኝበታል።
አሜሪካ ይህን ጥቃት ተከትሎ ጥቃት አድራሹን አግኝቻለሁ በሚል የድሮን ጥቃት የፈጸመች ሲሆን፣ በኋላ ግን እንዳመነችው ዒላማ ያደረገችው ስህተት ሆኖ 10 የአንድ ቤተሰብ አባላትን መግደሏን ነው። ከእነዚህ ሟቾች ውስጥ ሰባቱ ሕጻናት ናቸው።
አሜሪካ ይህን አጥፍቶ ጠፊ ወይም የቡድኑን መሪ ሳኑላህ ጋፋሪን ለጠቆመኝ 10 ሚሊዮን ዶላር እሸልማለሁ ስትል ቃል ገብታ ነበር።
አሜሪካ ከአፍጋኒስታን የወጣችበት መንገድ እና አብረዋት ሲሠሩ የቆዩ አፍጋኒስታናውያንን ለአደጋ አጋልጣ አገር መልቀቋ በአያሌው ሲያስተቻት ነበር።
ጆ ባይደን በበኩላቸው ለዚህ ሁሉ ውርደት የዳረጉን የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ናቸው ሲሉ መናገራቸው አይዘነጋም።












