ሰሜን ኮሪያ 'ምንነቱ ያልተለየ' የተወንጫፊ ሚሳኤል ሙከራ ማድረጓ ተነገረ

የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን

የፎቶው ባለመብት, KCNA via Reuters

የምስሉ መግለጫ, የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን

ሰሜን ኮሪያ አንድ ምንነቱ ለጊዜው በውል ያልታወቀ ተወንጫፊ ሚሳኤል ወደ ባሕር ሳትተኩስ እንዳልቀረች የደቡብ ኮሪያ መከላከያ ሚኒስቴር ይፋ አደረገ።

ጉዳዩን ይፋ ለማድረግ የመጀመሪያ የሆኑት የጃፓን የባሕር ጠረፍ ጠባቂዎች እንደሚጠረጥሩት ይህ ምንነቱ ያልታወቀ ሙከራ ተወንጫፊ ሚሳኤል እንደሆነ ጠርጥረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ሰሜን ኮሪያን የተወንጫፊ ሚሳኤሎችና የኒኩሊየር መሣሪያ ሙከራዎች እንዳታደርግ እገዳ እንደጣለባት ይታወቃል።

ይህ የአሁኑ የሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል ሙከራ ጥርጣሬ እውነት ከሆነ ክስተቱ በዚህ በአዲሱ የፈረንጆች ዓመት ፒዮንግያንግ ያደረገችው የመጀመሪያ የሚሳኤል ሙከራ ሆኖ ይመዘገባል።

ጉዳዩን አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ በቅርብ እየተከታተሉት ነው ተብሏል።

የጃፓኑ መከላከያ ሚኒስትር ናቡ ኪሺ እንደሚሉት ይህ ተምዘግዛጊ ሚሳኤል በሰዓት እስከ 300 ማይል ወይም 500 ኪሎ ሜትር የሚከንፍ ነው።

ይህ ሙከራ የሰሜን ኮሪያው ፍጹማዊ መሪ ኪም ጆንግ ኡን አገራቸው ሰሜን ኮሪያ "መከላከያ ኃይሏን ማጠናከሯን ትቀጥላለች፣ ምክንያቱም በአካባቢው ጠብ አጫሪ እንቅስቃሴዎች በመበራከታቸው" ሲሉ በተናገሩ ማግስት መሆኑ ነው።

ኪም ይህንን ንግግር ያደረጉት በሰሜን ኮሪያ ኮሚኒስት ፓርቲ ያለፈው የፈረንጆች ዓመት የመዝጊያ ስብሰባ ላይ ነበር።

የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳ ይህን ጥቃት 'መደረግ የሌለበት' ሲሉ ተቃውመውታል።

በተጠናቀቀው 2021 የጎርጎሮሲያዊያኑ ዓመት ሰሜን ኮሪያ የጦር መሣሪያዎቿን ማዘመንን ቀጥላበት ነው የቆየችው።

የአገሬው ሚዲያ እንደሚለው ከሆነ ሰሜን ኮሪያ ከድምጽ ፍጥነት ጋር የሚስተካከሉ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎችን እና አዲስ የረዥም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤሎችን ሙከራ አድርጋለች።

ሰሜን ኮሪያ ይህን ሙከራ እያደረገች ያለችው ሕዝቧ በምግብ እጥረት ክፉኛ እየተሰቃየ ነው በሚባልበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ነው።

በዚህ ኪም ንግግር ባደረገበት የፓርቲው ስብሰባ ሰሜን ኮሪያ የሞት ሸረት ፈተና ውስጥ ገብታለች፣ የዜጎች ኑሮ ተጎሳቅሏል ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ባልተለመደ ሁኔታ የአገሪቱን ወቅታዊ ችግር አምነው ተናግረው ነበር።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, ሰሜን ኮሪያ ለምን ኑክሊዬርን መረጠች?

የተባበሩት መንግሥታት በሰሜን ኮሪያ ውስጥ ሕጻናትና አረጋዊያን በረሀብ ምክንያት እየሞቱ እንደሆነ ይገምታል።