ሰሜን ኮሪያ አዲስና የረቀቀ የጦር መሳሪያ ሞከረች

የፎቶው ባለመብት, AFP
የሰሜን ኮሪያው ፕሬዝዳንት ኪም ጆንግ ኡን በአገሪቱ ብሄራዊ የመከላከያ ሳይንስ ተቋም ተገኝተው በቴክኖሎጂ የረቀቀ የተባለለትን መሳሪያ ሙከራ ላይ ክትትል ማድረጋቸውን የአገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።
እንደ ዘገባው ሙከራውም ውጤታማ ሆኗል።
የመሳሪያው ሙከራ ስኬታማ በመሆኑ ደስተኛ እንደሆኑና ይህ መሳሪያ ደግሞ የአገሪቱን መከላከያ ሃይል አቅም ከመገንባት አንፃር ትልቅ እርምጃ እንደሆነ ኪም መግለፃቸውን ዘገባው አመልክቷል።
የዜና ወኪሉ ምንም እንኳ ዝርዝሩን ባይገልፅም መሳሪያውን ለመስራት ረዥም ጊዜ እንደወሰደ ጠቁሟል።
ይህ እንደ አውሮፓውያኑ በ2018 የመጀመሪያው የጦር መሳሪያ ሙከራ እንደሆነም ገልጿል።
ምንም እንኳ እንዴት ተግባራዊ ይሆናል የሚለውን በሚመለከት ዝርዝር ባይወጣም ከጥቂት ወራት በፊት ኪም ጆንግ ኡንና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሰሜን ኮሪያ ኒኩሌር የማበልፀግ ፕሮጀክቷን እንድትገታው ከስምምነት ላይ መድረሳቸው የሚታወስ ነው።
ደቡብ ኮሪያ ጎረቤቷ ሰሜን ኮሪያ ምን አይነት መሳሪያ እንደሰራች ጥናት እየሰራች መሆኑ ተገልጿል። ብዙዎች ሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል ጣቢያዎችዋን ለመዝጋትም ሆነ የጦር መሳሪያ ፕሮጀክቶቿን ለመግታት ምንም አይነት ቁርጠኝነት እንደሌላት እየገለፁ ነው።
ሰሜን ኮሪያ ረቂቅ የተባለውን የጦር መሳሪያ የመሞከሯ ዜና መሰማቱን ተከትሎ የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት በፕሬዝዳንት ኪምና በፕሬዝዳንት ትራምፕ መካከል የተደረገው ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንደሚሆን ፅኑ እምነት እንዳለ አስታውቋል።












