የእግር ኳስ ኮከቡ ቦአቲንግ ፍቅረኛው ላይ ጥቃት በመፈጸም ጥፋተኛ ተባለ

ቦአቲንግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጀርመንናዊው የእግር ኳስ ኮከብ ዤሮም ቦአቲንግ የቀድሞ ፍቅርኛው ላይ ጥቃት በመፈጸም ጥፋተኛ ተባለ።

የቀድሞ ፍቅረኛውን በማጥቃት ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘው ጀርመናዊው እግር ኳስ ተጫዋች ዤሮም ቦአቲንግ 1.8 ሚሊዮን ዩሮ ቅጣት እንዲከፍል ተበይኖበታል።

ተጫዋቹ እአአ በ2018 በተፈጠረ አለመግባባት መንትያ ሴት ልጆቹን እናት ሼሪን ኤስን መጎዳቱን አስተባብሏል።

የቀድሞው የባየርን ሙኒክ ተከላካይ እና የ2014 የዓለም ዋንጫ አሸናፊው ከሳሽ ለፍርድ ቤቱ በቡጢ በከፍተኛ ሁኔታ እንደመታት እና ለአፍታ እስትንፋሷን አጥታ እንደነበር ተናግራለች።

በምስክርነቱ ወቅት ቦአቲንግ የተለየን የክስተቶች ሂደት ገልጿል።

በጀርመን የቤት ውስጥ ጥቃት ሕጎች መሠረት እስከ አምስት ዓመት ድረስ በእስር ሊቆይ ይችል ነበር።

ቦአቲንግ ጥቁር ሰማያዊ ሙሉ ልብስ ለብሶ በግል ጠባቂዎቹ እና በጠበቃው ካይ ዋልደን ተከቦ ነበር ፍርድ ቤት የደረሰው።

ከችሎቱ በፊት ዐቃቤ-ሕግ በቦአቲንግ በሐምሌ 2018 በካሪቢያን ደሴት እረፍት ላይ በነበሩበት ወቅት በቀድሞው ፍቅረኛውአነስተኛ የማቀዝቀዣ ሣጥን በመወርወር ሆን ብሎ አካላዊ ጉዳት አድርሷል ብሏል።

ቦአቲንግ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የቀድሞ ፍቅረኛው በፍርድ ቤት ምስክርነቷን ስትሰጥ በግጭቱ ወቅት ቦአቲንግ በቡጢ እንደመታት፣ ፀጉሯን መጎተቱን፣ ጭንቅላቷን መንከሱን እና እሷ እንደሰደበችው ተናግራለች።

ቦአቲንግ በሰጠው ቃል በካርድ ጨዋታ ወቅት ውጥረቱ መባባሱን አምኗል። ጠበኛ መሆኗን እና እንደሰደበችው፣ እንደመታችው እና ከንፈሩን እንደጎዳችው ተናግሯል። ከላዩ ላይ ሲገፈትራትም መውደቋን ተናግሯል።

ችሎቱ በታህሳስ ወር ሊካሄድ የነበረ ቢሆንም ምስክር ሊቀርብ ባለመቻሉ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል።

በእግር ኳስ ዓለም እና በማህበራዊ ሚዲያ ታዋቂ የሆነው ቦአቲንግ በክለብ እና በሀገር ደረጃ የተለያዩ ሽልማቶችን አንስቷል።

ሁለት የሻምፒዮንስ ሊግና ዘጠኝ የቡንደስሊጋን ዋንጫን ጨምሮ ከሙኒክ ጋር 22 ዋንጫዎችን አንስቷል። በሙኒክ የነበረው ኮንትራት መጠናቀቁን ተከትሎ ወደ ፈረንሳዩ ሊዮን በነጻ ዝውውር ተዛውሯል።

ሌላኛዋ የቦአቲንግ የቀድሞ ፍቅረኛ የ25 ዓመቷ ሞዴል ካሲያ ሌንሃርትት በየካቲት ወር በርሊን ውስጥ በሚገኝ አንድ አፓርታማ የራሷን ሕይወት አጥፍታለች።