2013 በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ወሳኝ ክስተቶች የተስተናገዱበት ዓመት

ካርታ

በተጠናቀቀው 2013 ዓ.ም ግንባታው ከተጀመረ አስረኛ ዓመቱን ያስቆጠረው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ በዓመቱ ውስጥ ወሳኝ ክስተቶችን አስተናግዷል።

ተገንብቶ ሲያበቃ በአፍሪካ ቀዳሚው የሚሆነው ይህ ግዙፍ ግድብ በፍጥነት ወደ ማጠናቀቂያው እየተቃረበ ነው።

የግንባታው ሂደት ከ80 በመቶ በላይ የደረሰው ይህ ግድብ ከአምስት ሺህ ኪሎ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ለኢትዮጵያና ለአካባቢው አገራት እንደሚያቀረብ ይጠበቃል።

ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ እየተገነባ ያለው ይህ ግዙፍ ግድብ የመጀመሪያ ደረጃ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ሥራውን በአዲሱ የኢትዮጵያ ዓመት ውስጥ እንደሚጀምር ተነግሯል።

ካለፉት ዓመታት በተለየ 2013 ላይ ግድቡን በተመለከተ ጠንከር ያለ አለመግባባት የተከሰተ ሲሆን ጉዳዩም አስከ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ድረስ ቀርቦ ነበር።

በ2013 ዓ.ም በታላቁ የሕዳሴው ግድብ ዙሪያ የተከሰቱ ጉልህ ጉዳዮች የትኞቹ ነበሩ?

የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት

መስከረም 2013፡ የትራምፕ አስተዳደር ኢትዮጵያ ከግብጽና ከሱዳን ጋር ከስምምነት ሳትደረስ ግድቡን መሙላት በመጀመሯ ምክንያት ለአገሪቱ ከሚሰጠው እርዳታ ላይ ቅነሳ እንደሚያደርግ አስታወቀ።

ኢትዮጵያም በዚህ ውሳኔ ላይ አሜሪካ ማብራሪያ እንድትሰጥ የጠየቀች ሲሆን እርምጃው የአገራቱን ግንኙነት እንደማይጎዳው ገለጸች።

ጥቅምት 2013፡ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አዛዥ በሕዳሴው ግድብ ላይ ሊሰነዘር የሚችልን ማንኛውንም አይነት ጥቃት ሠራዊቱ መመከት የሚያስችል አቅም እንዳለው ከተናገሩ በኋላ፤ የግድቡ ደኅንነት ለመጠበቅ በአካባቢው የሚደረጉ ሁሉም በረራዎች መታገዳቸው ተገለጸ።

ጥቅምት 2013የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሱዳንና ከግብጽ መሪዎች ጋር በስልክ በተወያዩበት ጊዜ በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ የሚካሄደው ድርድር በኢትዮጵያ ምክንያት ውጤት አለማምጣቱን በመግለጽ ግብጽ "ግድቡን ልታፈነዳው ትችላለች" በሚል በሰነዘሩት አስተያየት ላይ ኢትዮጵያ ቁጣዋን ገለጸች።

በማስከተልም ኢትዮጵያ በአገሯ የሚገኙትን የአሜሪካ አምባሳደርን በመጥራት በፕሬዝደንቱ ንግግር ላይ "ማብራሪያ" ጠየቀች። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም የትረምፕን ንግግር በመቃወም የበይነ መረብ ዘመቻ አካሄዱ።

ኅዳር 2013፡ በሕዳሴው ግድበ ዙሪያ በሦስቱ አገራት መካከል ሲካሄድ የቆየውና የተራዘመው ድርድር በበይነ መረብ አማካይነት መካሄድ ጀምረ። በዚህም የውሃ ሚኒስትሮች፣ ባለሙያዎች እና ዓለም አቀፍ አደራዳሪዎች የተሳተፉ ሲሆን ከስምምነት ለመድረስ ሳይቻል ቀረ።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Water...

ኅዳር 2013በትግራይ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ ይገባኛል የምትለውን ግዛት በኃይል የያዘችው ሱዳን ግንኙነቷን ከግብጽ ጋር ማጠናከሯን ቀጠለች። ከሕዳሴው ግድብ አንጻር ተመሳሳይ አቋም በመያዝ አብረው ከመቆማቸው ባሻገር ሁለቱ አገራት ይፋዊ ወታደራዊ ልምምድ ማድረግ ጀመሩ።

ጥር 2013፡ በሦስቱ አገራት መካከል ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው ድርድር ሱዳን ባለመሳተፏ ሳይሳካ ቀረ። ሱዳን የተጀመረው የድርድር ሂደት ውጤት አያመጣም በማለት ከድርድሩ ስትቀር ለሁለተኛ ጊዜ ነበር።

ቢሆንም ግን ከሳምንት በኋላ የሁሉም አገራት የውጭ ጉዳይና የውሃ ሚኒስትሮች የተሳተፉበት የበይነ መረብ ስብሰባ ለማድረግ ቢቻልም ከስምምነት ሳይደረስ ተጠናቀቀ።

የካቲት 2013፡ ሱዳን በአፍሪካ ሕብረት የሚመራና አሜሪካ፣ የአውሮፓ ሕብረት እና የተባበሩት መንግሥታት በአደራዳሪነት የሚሳተፉበት ሂደት እንዲጀመር ሐሳብ አቀረበች። ግብጽም የሱዳንን ሐሳብ ደግፋ ብትቆምም በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ፥።

የካቲት 2013ኢትዮጵያ ከሱዳንና ከግብጽ ጋር ከስምምነት ተደረሰም አልተደረሰ ሁለተኛውን ዙር የግድቡን የውሃ ሙሌት በያዘችው ዕቅድ መሠረት እንደምታከናውን አሳወቀች። ለዚህም እንዲሆን የደን ምንጣሮ ለማካሄድ የሚውል ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ መድባ ነበር።

ሚያዝያ 2013፡ በአፍሪካ ሕብርት አማካይነት ዲሞክራቲክ ኮንጎ ዋና ከተማ ኪንሻሳ ውስጥ የተካሄደው የሦስቱ አገራት የሕዳሴ ግድብ ድርድር ያለ ውጤት ማብቃቱን ግብጽ አሳወቀች።

ለዚህም የግብጽ የመስኖ ሚኒስትር ለድርድሩ አለመሳካት ኢትዮጵያን ተጠያቂ ያደረጉ ሲሆን ሱዳን ደግሞ ኢትዮጵያ "ተቀባይነት የሌለው ግትርነት" አሳይታለች ስትል ከሰሰች።

ግንቦት 2013፡ ባልተለመደ ሁኔታ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሁለተኛው ዙር የግድቡ ሙሌት የግብጽን ብሔራዊ ጥቅም የሚጎዳ አይሆንም ብለዋል። ነገር ግን የአገራቸው የውሃ ደኅንነት አደጋ ላይ የሚወድቅ ከሆነ እርምጃ ትወስዳለች ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Water...

ግንቦት 2013 ግብጽ በአፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ ውስት በግድቡ ዙሪያ ድጋፍን ለማሰባሰብ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በምታደርግት ጊዜ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን ግብጽ፣ ኢትዮጵያንና ሱዳንን ጎበኙ።

ግንቦት 2013ለኢትዮጵያ መልዕክት ለማስተላለፍ በሚመስል ሁኔታ ሱዳንና ግብጽ "የአባይ ጠባቂዎች" በሚል ስያሜ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ አደረጉ። ይህም በአገራቱ ጥቅምና ደኅንነት ዙሪያ ሊያጋጥሙ በሚችሉ ስጋቶች ዙሪያ በጋራ ለመሰለፍ የታለመ መሆኑም ተገልጿል።

ሰኔ 2013የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በግድቡ ምክንያት ከገባችበት ውዝግብ አንጻር ድጋፍ እንዲሰጧቸው ለአረብ አገራት ጥያቄ አቀረቡ።

የአረብ ሊግም በግድቡ ዙሪያ አገራቱ ውጤታማ የሆነ ድርድር እንዲጀምሩ ለማስቻል የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ እንዲያደርግ ጥሪ አቀረበ።

ሰኔ 2013፡ ሱዳንና ግብጽ ከስምምነት ሳይደረስ ሁለተኛው ዙር የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት እንዳይካሄድ ቢወተውቱም ኢትዮጵያ በያዘችው መርሃ ግብር መሠረት ውሃ መሙላቷን ጀመረች። የውሃ ሙሌቱ በሐምሌና በነሐሴ ከገፋም አስከ መስከረም ድረስ ሊቆይ ይችላል ተብሎ ነበር።

ሐምሌ 2013፡ በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብጽ መካከል በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ለተከሰተው አለመግባባት ከዚህ በፊት ባልታየ ሁኔታ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ተሰብስቦ የአገራቱን አቤቱታ ሰምቷል። በመደምደሚያውም ጉዳዩ ቀደም ሲል በተያዘበት በአፍሪካ ሕብረት በኩል መቋጫ እንዲያገኝ ውሳኔ ሰጠ።

ሐምሌ 2013፡ ለጥቂት ወራት ይቆያል የተባለው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በሳምንታት ውስጥ ተከናውኖ መጠናቀቁን ኢትዮጵያ አሳወቀች።

በ2013 የታላቁ ሕዳሴ ጉዳይ በተለይ በግብጽና በሱዳን ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት በርካታ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ወታደራዊ ሥራዎች ሲከናወንበት ቆይቷል።

የግድቡ ጉዳይ በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት የውይይት ርዕስ ከሆነ በኋላ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር ግድቡን የውሃ ሙሌት ማጠናቀቋን ካሳወቀች በኋላ ከግብጽና ከሱዳን በኩል በግድቡ ዙሪያ የነበረው የተካረረ ውዝግብ ጋብ ያለ ይመስላል።

የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት