የሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ተጠናቀቀ

የሕዳሴው ግድብ

የፎቶው ባለመብት, PM ABIY/FB

ከጥቂት ሳምንት በፊት የተጀመረው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግደብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቁ ተገለጸ።

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ያለችው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት መጠናቀቁን የውሃ፣ ኢነርጂ እና መስኖ ሚንስትሩ ዶ/ር ኢንጅ. ስለሺ በቀለ አስታውቀዋል።

"የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በመጠናቀቁ እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ" ያሉት ዶ/ር ኢንጅነር ስለሺ "ግድቡ በአሁኑ ወቅት መያዝ የሚያስፈልገውን ውሃ ይዟል" ብለዋል።

ከሱዳንንና ከግብጽ በኩል ከፍ ያለ ተቃውሞ እየተሰማ በነበረበት ጊዜ ከሁለት ሳምንት ሰኔ 28/2013 ዓ.ም ግድቡ የሁለተኛው ዙር ሙሌት በተጀመረበት ጊዜ ሙሌቱ በነሐሴ ወር አጋነማሽ ላይ እንደሚጠናቀቅ ተገልጾ የነበረ ቢሆንም በአገሪቱ ባለው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት በአጭር ጊዜ ተጠናቋል።

የግድቡ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጀመርን በተመለከተ ለግብጽ አቻቸው የኢትዮጵያው የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ በላኩት ደብዳቤ ላይ በሐምሌ ወር 6.9 ሚሊዮን ኪውቢክ ሜትር ውሃ እንዲሁ በነሐሴ ወር ተመሳሳይ መጠን ያለው ውሃ ለመሙላት መታቀዱን ገልጸው እንደነበር ይታወሳል።

በአሁኑ ወቅት በግድቡ ውስጥ ሁለት የኃይል ማመንጫ ተርባይኖችን ለማንቀሳቀስ የሚያስችል የውሃ መያዝ እንደተቻለ የውሃ፣ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት 10 ዓመታት የግድቡን ግንባታ በ5 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ ግንባታውን ስታከናውን ቆይታለች።

ግድቡ ሲጠናቀቅ ከፍተኛ ቁጥር ላለው ሕዝብ የኤሌክትሪክ ብርሃን ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ተገንብቶ ሲጠናቀቅ በግዝፈቱ ከአፍሪካ ቀዳሚ እንደሚሆን የተነገረው ግድቡ በአሁኑ ጊዜ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የግንባታ ሥራው መጠናቀቁ የተገለጸ ሲሆን የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሊት መጠናቀቅን ተከትሎ በከፊል የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።

ከአምስት ሺህ በላይ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያመነጭ የተነገረለት ይህ ግድብ ተጠናቆ ሥራ ሲጀምር ከግማሽ በላይ ለሚሆነው የአገሪቱ ሕዝብ፣ ለኢንዱስትሪዎችና ለጎረቤት አገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ያቀርባል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።

የሕዳሴውን ግድብ ግንባታ እና ውሃ ሙሊት የታችኛው የተፋሰስ አገራት ግብጽ እና ሱዳን ሲቃወሙት ቆይተዋል። በቅርቡም በሱዳን እና ግብጽ ግፊት በግድቡ ዙሪያ የተባባሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት መወያየቱ ይታወሳል።

በቀጥታ ስርጭት ላይ የሁለተኛውን ዙር ውሃ ሙሌት መጠናቀቅን በተመለከተ ከስፍራው የተሰራጩ ምስሎች ግድቡ በውሃ ሞልቶ ውሃው በግድቡ አናት ላይ ሲፈስ አሳይተዋል።

የሕዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ በበኩላቸው "የተለያዩ ወገኖች በግድቡ ዙሪያ ተቃውሞና ጫጫታ ቢያሰሙም ፕሮጀክቱ ይፈጸማል ከፍጻሜ ላይ ይደርሳል" ብለዋል።

ግብጽ እና ሱዳን ኢትዮጵያ እየገነባች ያለችው ግደብ ደኅንነት ያሳስበናል እንዲሁም የውሃ ድርሻችንን ይቀንስብናል ሲሉ ሲከራከሩ ከመቆየታቸው በተጨማሪ ሕጋዊ አሳሪ ስምምነት ሳይደረግ የውሃ ሙሌቱ እንዳይከናወን ሲወተውቱ ነበር።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ከሱዳን ድንበር አቅራቢያ እየተገነባ ያለ ግዙፍ ግድብ ሲሆን ግንባታው ከአስር ዓመት በፊት ነበር የተጀመረው።

ኢትዮጵያ ሕዝቧን በማስተባበር ከአምስት ቢሊየን ዶላር በላይ በሚሆን ገንዘብ እያከናወነችው ያለውን የግድቡን ግንባታ ከሚያከናውኑ ሥራ ተቋራጮች መካከል የጣሊያኑ ሳሊኒ ኢምፕሬጂሎ በዋነኝነት ይጠቀሳል።

የዋናው ግድብ ከፍታ 145 ሜትር ሲሆን፤ ርዝመቱ 1 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ነው።

ግድቡ የሚይዘው የውሃ መጠን 74 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ሲሆን፤ ግድቡ የሚሸፍነው የቦታ ስፋት ደግሞ 1 ሺህ 680 ስኩዌር ኪሎ ሜትር መሆኑ ተነግሯል።

ሱዳንና ግብጽ የውሃ ሙሌቱ ከመከናወኑ በፊት ከስምምነት መደረስ አለበት ቢሉም ኢትዮጵያ ግንባታውም ሆነ ውሃ መሙላት ሥራው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ እየተከናወነ ድርድሩን ማድረግ እንደሚቻል በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች።

ለረጅም ጊዜ ሲካሄድ የቆውና ከውጤት ላይ ሳይደረስ በእንጥልጥል ላይ ያለው የአገራቱ ድርድር በቅርቡ መልሶ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል።

ማን ምን አለ?

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ መገለጹን ተከትሎ በተለያየ ኃላፊነት ላይ የሚገኙ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ሌሎችም ኢትዮጵያውያን ደስታቸውን በማኅበራዊ ገጾቻቸው እየገለጹ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ግድቡን የሚያሳዩ ፎቶግራፎችና "ሁለተኛው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሙሌት በመጠናቀቁ እንኳን ደስ ያለን!" የሚል መልዕክት አስፍረዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን የግድቡ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በመጠናቀቁ ሕዝቡን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

አቶ ደመቀ "የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መርሃ ግብር በተሳካ ሁኔታ በመከናወኑ እንኳን አስ አላችሁ። እንኳን አብሮ ደስ አለን" ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ ስሜታቸውን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤም በተመሳሳይ ሁኔታ ደስታቸውን ገልጸዋል።

ወ/ሮ አዳነች "መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ መላው ከተማችን ነዋሪዎች እንዲሁም በመላው ዓለም የምትገኙ የአገሬ ልጆች እንኳን ደስ አላችሁ። ኢትዮጵያ በትንሳኤ ጉዞ ላይ ናት" ሲሉ ትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

የገንዘብ ሚንስትር ሚኒስቴር ዲኤታ ዶ/ር እዮብ ተካልኝ "ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ተጠናቋል። ይህ ትልቅ ነው። ኢትዮጵያ ብዙ መሰናክሎች ቢገጥሟትም ወደፊት መገስገሷን ቀጥላለች" ብለዋል በትዊተር ገጻቸው።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ "ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ኩራታችን ነው" በማለት ትዊት አድርገዋል።

በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ በማስመልከት ዜጎች፣ የማኅበረሰብ አንቂዎችም ደስታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።

ታዋቂው የንግድ እና ኢንቨስትመንት ባለሙያ አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ የውሃ፣ ኢነርጂ እና መስኖ ሚንስትር ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ ስለ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ በትዊተር ገጻቸው የጻፉትን አጣቅሰው "ሁላችንንም አኩርቶናል። እንኳን አስ አለን። ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድቡን ከማጠናቀቅ የሚያግዳት የለም" ብለዋል።

የተለያዩ የኢትዮጵያ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶችም በይፋዊ ማኅበራዊ ድረ ገጾቻቸው የእንኳን ደስ አለን መልዕክት እያስተላለፉ ነው።

ኢትዮ-ቴሌኮም ከእነዚህ ድርጅቶች አንዱ ሲሆን "እንኳን ደስ አላችሁ። እንኳን ደስ አለን" የሚል ጽሑፍ በገጹ አስፍሯል።

ከዛሬ ንጋት አንስቶ ማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ የግድቡን የሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ የሚያሳዩ ፎቶዎችን በብዙዎች ሲጋሩ ነበር።