ለ100 ዓመታት 'ያልታየው' የቫን ጎህ ሥዕል 13 ሚሊዮን ዩሮ ተሸጠ

ለ100 ዓመታት ያልታየው የቫን ጎህ ሥዕል 13 ሚሊዮን ዩሮ ተሸጠ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ከ100 ዓመታት በላይ በአደባባይ ሳይታይ የቆየው የቪንሰንት ቫን ጎህ ሥዕል 13.9 ሚሊዮን ዩሮ (11.2 ሚሊዮን ፓውንድ) ተሸጠ።

የፓሪስ ጎዳናን የሚያሳየው ሥዕል እስካሁን ከተሸጡ የቫን ጎህ ሥዕሎች ከፍተኛ ገንዘብ የወጣበት ነው።

ሥዕሉ በጨረታ ይሸጣል ተብሎ የተገመተው በ6.9 ሚሊዮን ዩሮ ነበር።

ጨረታው በቀጥታ በበይነ መረብ የተላለፈው ከፓሪስ ነበር።

ሥዕሉ የተሠራው እአአ በ1887 ሲሆን፤ አንድ የፈረንሳይ ቤተሰብ ጋር ተቀምጦ ነበር።

A Street Scene In Montmartre የተባለውን ሥዕል ቫን ጎህ የሠራው እአአ ከ1886 እስከ 1887 ወንድሙ ጋር ፓሪስ ሳለ ነበር።

ያኔ መንደር በነበረው ሞንትማትሪ ውስጥ የሚገኝ ጎዳና እና የንፋስ ኃይል ማመንጫን ያሳያል።

ቫን ጎህ ፓሪስን ለቅቆ ወደ ደቡብ ፈረንሳይ ያቀናው በ188 ነበር።

በቫን ጎህ ሥዕሎች ላይ የሚመራመሩት ማርቲን ቤይሊ፤ ሥዕሉ ከተሠራበት ቀለም እና ቅርጽ በመነሳት "የቫን ጎህን የሽግግር ዘመን ያሳያል" ብለዋል።

ሥዕሉ ለዓመታት ተደብቆ መቆየቱም ምሁሩን አስገርሟቸዋል።

"የቤተሰቡ የግል ስብስብ ውስጥ ስለነበር ስለ ሥዕሉ የሚያውቀው ቤተሰቡና ጓደኞቻቸው ብቻ ነበሩ" ሲሉ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ቫን ጎህ ሥዕሉ ላይ ያሰፈረው ጎዳና ወንድሙ ይኖርበት የነበረው ቤት አቅራቢያ ያለ ነበር። ምናልባትም ቫን ጎህ ገንዘብ ሲያገኝ የሚጠጣበትና የሚዝናናበት አካባቢ ሊሆን እንደሚችል ያምናሉ።