ሰሜን ኮርያ ያስወነጨፈችው ሚሳዔል "አዲስ በታክቲክ የሚመራ" እንደሆነ ገለፀች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሰሜን ኮርያ ሐሙስ እለት ያስወነጨፈችውን ሚሳዔል በሚመለከት ባወጣችው መግለጫ "አዲስ በታክቲክ የሚመራ ተወንጫፊ" መሳሪያ መሆኑን ገለፀች።
ሰሜን ኮርያ ከዓመት ወዲህ ያስወነጨፈችው ይህ ባሌስቲክ ሚሳዔል፤ ጆ ባይደን ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ የተደረገ የመጀመሪያ ሙከራ ነው ተብሏል።
ይህንን ሙከራ አሜሪካ፣ ጃፓን፣ እና ደቡብ ኮርያ አውግዘዋል።
በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ስምምነት መሰረት ፒዮንግያንግ ባሌስቲክ ሚሳዔሎችን እንዳትሞክር ማዕቀብ ተጥሎባት ነበር።
የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ "ይህ ሙከራ የተባበሩት መንግሥታትን በርካታ ስምምነቶች የጣሰ፣ የቀጠናውን ሰላም እና ሰፊውን የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ አደጋ ላይ የጣለ ነው" ብለዋል።
ሰሜን ኮርያ አርብ እለት ባወጣችው መግለጫ ያስወነጨፈቻቸው ሁለት ሚሳዔሎች በ600 ኪሎ ሜትር ርቀት ከሰሜን ኮሪያ የባህር ዳርቻ ርቆ የሚገኝ ዒላማን ድባቅ የሚመቱ ናቸው ብላለች።
በርግጥ ጃፓን ይህንን የሰሜን ኮሪያ ምዘና በሚቃረን መልኩ ሚሳዔሎቹ 400 ኪሎ ሜትር ብቻ መወነጨፍ የሚችሉ ናቸው ብላለች።
የአገሪቱ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን የሆኑት እና ሙከራውን በቅርበት የተከታተሉት ሪ ፕዮንግ ቾል "የዚህ መሳሪያ ባለቤት መሆን ለአገሪቱ መከላከያ ኃይል ትልቅ አቅም እንዲሁም ሊቃጣ የሚችልን ማንኛውንም ወታደራዊ ጥቃት በብቃት ለመመከት ያስችላል" ማለታቸው በመግለጫው ላይ ተመልክቷል።
ኪም ጆንግ ኡን ግን በሙከራው ወቅት አልተገኙም።
እንደ ፒዮንግያንግ ከሆነ ይህ አዲሱ ሚሳዔል 2.5 ቶን የሚመዝን የኒውክለር ጫፍ ተሸክሞ መምዘግዘግ ይችላል።
ሰሜን ኮርያ ምን ዓይነት ሚሳዔል እንዳስወነጨፈች በትክክል ጥርት ያለ መረጃ ባይኖርም፤ አገሪቱ በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሥልጣን ዘመን ያሏትን የኒውክለር ጦር መሳሪያዎች እንድታወድም ንግግር ከጀመረች ወዲህ በዘርፉ እመርታ ማሳየቷን ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የአገሪቱን የሚሳዔል አቅም በቅርበት የሚከታተሉ ሰዎች እንደሚሉት ከሆነ አሁን ያስወነጨፈችው መሳሪያ በጥቅምት ወር በወታደራዊ ትርዒት ላይ ካሳየችው ጋር ተመሳሳይ ነው።
ይህ እውነት ከሆነ ከዚህ ቀደም የሞከረችው KN-23 ሚሳዔል ተሻሽሎ ግዙፍ አረር መሸከም እንዲችል ተደርጎ ተሰርቷል ማለት ነው ሲሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
ይህ ከባድ የሆነ አረር መሸከም የሚያስችለው ሚሳዔል ሰሜን ኮርያን በሮኬቶቿ ላይ ከባድ የሆኑ የኒውክሌር ጫፎችን በማድረግ ማስወንጨፍ እንደሚያስችላት በኤምአይቲ የደህንነት ጥናት ፕሮፌሰር የሆኑት ቪፒን ናራንግ በትዊትር ገጻቸው ላይ ገልፀዋል።
አነስ ያሉ የኒውክሌር አረርችን ማምረት ከባድ እንደሆነ ባለሙያዎች ቢናገሩም ሰሜን ኮርያ ግን ቀድሞውንም ይህ አቅሙ አላት።
ሰሜን ኮርያ ለመጨረሻ ጊዜ ባሌስቲክ ሚሳዔል ያስወነጨፈችው ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር በነበራት አለመግባበት ወቅት ከአንድ ከዓመት በፊት ነበር።
የባይደን አስተዳደር ከሰሜን ኮርያ ጋር ለመመስረት የሞከረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ፍሬ አልባ መሆኑን አስታውቋል።
ፒዮንግያንግ እስካሁን ድረስ የባይደንን ወደ ሥልጣን መምጣት በማስመልከት ያለችው ነገር የሌለ ሲሆን ሁለቱ አገራት አሁንም ሰሜን ኮርያ ባላት የኒውክሌር መሳሪያ ምክንያት አይንና ናጫ እንደሆኑ ናቸው።












