ኮቪድ-19 ፡ የቻይና ምጣኔ ሀብት እያደገ ነው

የቻይና ምጣኔ ሃብት እየጨመረ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የቻይና ምጣኔ ሀብት ባለፈው ዓመት ከአራት አስርት ዓመታት በላይ በዝቅተኛ ፍጥነት ማደጉን ይፋዊ አኃዞች ያሳዩ ሲሆን፤ በጎርጎሮሳዊያኑ 2020 ከባለ ትልልቅ የኢኮኖሚ ባለቤቶች ተርታ ብቸኛውን እድገት ያሳየ ለመሆን ተቃርቧል።

ምንም እንኳን በጎርጎሮሳዊያኑ 2020 መጀመሪያ ወራት የኮቪድ-19 እገዳዎች ምርት እንዲቀንስ ቢያደርጉም ምጣኔ ሀብቱ ባለፈው ዓመት 2.3% አድጓል፡፡

ጥብቅ የኮሮናቫይረስ መከላከያ እርምጃዎች እና ለንግድ ድርጅቶች አስቸኳይ እፎይታ መፈቀዱ ኢኮኖሚው እንዲነቃቃ አግዞታል፡፡

በዓመቱ የመጨረሻ ሦስት ወራት የዕድገት መጠኑ እስከ 6.5% ደርሷል፡፡

በኢኮኖሚስት ኢንተለጀንስ ዩኒት ዋና የምጣኔ ሀብት ምሁር የሆኑት ዩ ሱ "የአገር ውስጥ ምርት (GDP) መረጃ ኢኮኖሚው መደበኛ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑን ያሳያል ማለት ይቻላል፡፡ ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት በሰሜን ቻይና በሚገኙ ጥቂት አውራጃዎች የተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለጊዜው መለዋወጥ ቢያስከትልም ይህ ፍጥነት ይቀጥላል ማለት ይችላል" ብለዋል፡፡

የቻይና ዋና አክሲዮን ገበያዎች እና የሆንግ ኮንግ ሀንግ ሴንግ የቅርብ ጊዜ አሃዞች ላይ መጠነኛ ከፍታን ያሳዩ ሲሆን ይህም የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ከሚጠብቁት በላይ ሆኗል ሲል በሮይተርስ የተደረገ ጥናት አመልክቷል፡፡

አሁንም ግን በጎርጎሮሳዊያኑ 2020 የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የኢኮኖሚውን እድገት ሊያስተጓጉል ይችላል የሚል ስጋት አለ።

የቻይና የምርት ዘርፍ ወደ ዕድገቱ የተመለሰ ይመስላል። በሰኞ ዕለት መረጃ መሠረት የኢንዱስትሪ ምርት በ 7.3 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

ወደ ውጭ የሚላክ ምርትም ቀደሚነቱን ይዟል፡፡ በዓለም ዙሪያ የኮሮናቫይረስ ስርጭት የቻይና ምርትን ፍላጎት በመጨመሩ ባለፈው ታህሳስ የአገሪቱ የወጪ ንግድ ከተጠበቀው በላይ አድጓል።

ይህ የሆነው የን ጠንካራ ሆኖ የቻይና የውጭ ንግድ ለውጭ አገራት ገዢዎች የበለጠ ውድ ባደረገበት ወቅት ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜዎቹ ቁጥሮች አንጻር ግን መልካም ዜናዎች አይደሉም፡፡

በስታንዳርድ ቻርተርድ ባንክ ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ምሁር የሆኑት ሊ ዌ በበኩላቸው ከወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች እና በብድር የሚሸጡ መኪናዎች እና ቤቶች አብዛኛዎቹን ዕድገት ያስመዘገቡ ሲሆን የxር ውስጥ ፍላጎት ግን ወደ ኋላ ቀርቷል ብለዋል፡፡

ምሁሩ ለሮይተርስ እንደተናገሩት "የቤት ውስጥ የምግብ፣ የአልባሳት፣ የቤት ዕቃዎች እና የፍጆታ ቁሳቁሶች ፍላጎት ከቅድመ ወረርሽኝ መጠን በታች ሲሆኑ Yቱሪዝም እና የትራንስፖርት ዘርፎች የአቅም እና የጉዞ ገደቦችን መግጠማቸውን ቀጥለዋል፡፡"

የችርቻሮ ሽያጭ በ2020 አራተኛ ሩብ ዓመት በ 4.6 በመቶ ቢያድግም የዓመቱ ግን በ 3.9 በመቶ ቀንሷል፡፡

ብዙ ተንታኞች በጎርጎሮሳዊያኑ 2021 ዕድገቱ እንደሚፋጠን ግምታቸውን እየሰጡ ቢሆንም የቻይናው የስታቲስቲክስ ቢሮ "የወረርሽኙ ከፍተኛ ተጽዕኖ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ከባድና ውስብስብ ሊሆን ይችላል" ሲል አስጠንቅቋል፡፡

ቻይና አሁንም ከአሜሪካ ጋር የምታደርገውን የንግድ ውዝግብን ጨምሮ ብዙ ፈተናዎች ተጋርጠውባታል፡፡