የሴቶችና ሕጻናት ጥቃትን ለመከላከል የተቋቋመው የፖሊስ ግብረ ኃይል እንዴት ይሠራል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር በዓሥር ዓመት መሪ እቅዱ ካካተታቸው መካከል የጸረ ጥቃት ፖሊስ ግብረ ኃይል እንዲሁም ብሔራዊ የጥቃት አድራሾች መረጃ ሥርዓት ይገኙበታል።
ተቋሙ ከነዚህ በተጨማሪ የሕጻናት ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እና የሕጻናት ማኅበራዊ አገልግሎት ኤጀንሲ የመዘርጋት ሐሳብም እንዳለው አስታውቋል።
የአፍሪካ ሴቶች አመራር ማዕከል፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች ካውንስል እና የሴቶች የልማት ፈንድ ማቋቋምም ከእቅዶቹ መካከል ይገኙበታል።
በዋነኛነት ስለ ጸረ ጥቃት ፖሊስ ግብረ ኃይል እና ብሔራዊ የጥቃት አድራሾች መረጃ ሥርዓት ምንነት ከመሥሪያ ቤቱ ማብራሪያ ጠይቀናል።
የጸረ ጥቃት ፖሊስ ግብረ ኃይል
የሴቶች ሕጻናትና ወጣቶች ሚንስትር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አድነው አበራ እንደሚሉት፤ በዚህ ግብረ ኃይል ከፍትሕ፣ ከጤና እና ማኅበራዊ ጉዳይ የተውጣጡ አካላት ይካተቱበታል።
የፖሊስ ግብረ ኃይሉ ሕጻናት እና ሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን በሚመለከት ብቻ ይሠራል።
"ጥቃት ከመከሰቱ በፊት ይከላከላል። ጥቃት ሲከሰትም ጉዳዩን እስከ ፍርድ ቤት መረጃ በማጠናቀር ይሠራል" ብለዋል አቶ አድነው።
ግንዛቤ በመስጠትና በንቅናቄ ሥራዎች ብቻ ጥቃትን መከላከል ስለማይቻል ሥርዓቱ መዘርጋቱን አስረድተዋል።
"የተለያዩ ተቋሞች በቅንጅት ካልሠሩ አንድ ተቋም ብቻ በአሸናፊነት አይወጣውም" የሚሉት አቶ አድነው፤ አሁን ላይ ከጠቅላይ አቃቤ ሕግ እና ከፖሊስ ኮሚሽን ጋር እየተወያዩ እንደሆነና የመግባቢያ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት እቅዱ በአገር አቀፍ ደረጃ እንደሚተገበር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ብሔራዊ የጥቃት አድራሾች መረጃ ሥርዓት
ብሔራዊ የጥቃት አድራሾች መረጃ ሥርዓት ወይም ናሽናል ሴክስ ኦፌንደርስ ሬጅስትሬሽን ጥቃት አድራሽ ወንጀለኞች የሚመዘገቡበት ሥርዓት ነው።
"በሴቶችና ሕጻናት ላይ ጥቃት የሚያደርስ በሕግ ብቻ ተጠይቆ የሚወጣበት ሳይሆን፤ በሕይወቱ ባጠቃላይ ተጠያቂ የሚሆንበት፣ የሚሸማቀቅበት ሥርዓት ነው" ሲሉ የሕዝብ ግንኙነቱ ያስረዳሉ።
ሥርዓቱ፤ ወንጀለኞች ከእስር ከወጡ በኋላ የተለያዩ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን እንዳያገኙ ያግዳል።
አሠራሩ ወንጀለኞችን ለመቅጣት፣ ጥቃት አድራሾችን ለመግታት እንዲሁም ኢትዮጵያም የሴቶችና ሕጻናት ጥቃትን የምትጠየፍ አገር መሆኗን ለማሳየትም እንደሚያገለግል አቶ አድነው ገልጸዋል።
እንዴት ይሠራል?
በአብዛኛው ጾታዊ ጥቃት የሚደርሰው በቤተሰብ፣ በዘመድ፣ በጎረቤት ወይም በሌላ የቅርብ ሰው እንደመሆኑ ጥቃት የደረሰባቸውን ሕጻናት እንዴት ትለያላችሁ? በሚል ለአቶ አድነው ጥያቄ አቅርበን ነበር።
እሳቸው እንደሚሉት፤ ሰፈር ውስጥ ወይም በትምህርት ቤቶች ከመምህራን መረጃ በመሰብሰብ ይሠራሉ።
"ተማሪዎች የሚያሳዩትን ባህሪ መምህራን ያውቁታል። ትካዜ፣ ትምህርት በቀላሉ መቀበል አለመቻል ወዘተ. . . ይጠቀሳሉ" ብለው ግብረ ኃይሉ ከተቋቋመ በኋላ ሌሎች ዝርዝር የአሠራር መንገዶች እንደሚወጡ አክለዋል።
ሌላው የሕጻናት ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት (ዩኒቨርሳል ቻይልድ ቤነፊት) ነው። ጥቃት፣ ያለ እድሜ ጋብቻና ድህነት በሰፋበት አካባቢ ከ0 እስከ 2 ወይም እስከ 5 ዓመት ልጆች እናቶች የገንዘብ ድጋፍ የማድረግ ፕሮጀክት ነው።
"ጥቃትን ለመከላከል ቀጥተኛ ያልሆነ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። እናትን በኢኮኖሚ ለማሳደግና አመጋገብ፣ ጤናና የአእምሮ እድገትን ጨምሮ ለሕጻናት ሁለተንተናዊ እድገት ድጋፍ ለማድረግ ይውላል" ይላሉ።
በሌላ በኩል ከዚህ ቀደም የነበረው ጥቃት የደረሰባቸው እንዲያገግሙ የመደገፍ (ሪሀብሊቴሽን) ሂደት እንደሚቀጥል አቶ አድነው ተናግረዋል።
አዳማ እና አዲስ አበባ ላይ ፍቃድ እንዳገኙና የነበሩትን ማዕከላት ከማጠናከር ጎን ለጎን፤ አዲስና ደረጃቸውን የጠበቁ ማዕከላት ለመገንባት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አክለዋል።
አያይዘውም፤ "ማንኛውም ችግር ሲከሰት በቅድሚያ የሚጎዱት ከተጠቃሚነትም ወደ ኋላ የቀሩት ሴቶችና ሕጻናት ናቸው። ይህን ለመፍታት ቋሚ አሠራር እንጂ ጊዜያዊው አይረዳም። ተደራርበው የሚመጡ ማኅበራዊ ቀውሶች በዘላቂ ሥርዓት እየተቀረፉ እንደሚሄዱ እናምናለን" ብለዋል።
የሴቶች መብት ተሟጋቾች ምን ይላሉ?
የጸረ ጥቃት ፖሊስ ግብረ ኃይል እና ብሔራዊ የጥቃት አድራሾች መረጃ ሥርዓትን በተመለከተ በተለያዩ የጾታ እኩልነት ላይ የሚሠሩ ማኅበሮች አባላት ምን አስተያየት እንዳላቸው ጠይቀናል።
የ 'የሎ ሙቭመንት' አባል የሆነችው ሩት ይትባረክ፤ ግብረ ኃይሎቹ መቋቋማቸው መልካም ቢሆንም፤ ተቋቁመዋል ለሚል ፍጆታ ከመዋል ባሻገር ተግባራዊ ለውጥ ማምጣት እንዳለባቸው ትናገራለች።
ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ወደ ፍትሕ እንዳይሄዱ ከሚያደርጋቸው አንዱ ከፍትሕ አካላት አዎንታዊ መልስ አለማግኘት መሆኑን በመጥቀስ፤ "በጥቃት ላይ ጥቃት የሚያደርሰው አንዱ የፍትሕ አካሉ ነው። ስለዚህ የፍትሕ አካሉ መፈተሽ፣ መሻሻል፣ ለጾታ ጉዳዮች ስሱ መሆን እና ለእውነተኛ ፍትሕ የቆመ መሆን አለበት" ትላለች።
ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችን አላስፈላጊ ጥያቄ የሚጠይቁ የፍትሕ አካላት ታርመው ጥቃት የደረሰባትን ሴት በምን መንገድ ማስተናገድ እንዳለባቸው መገንዘብ እንዳለባቸው ታሳስባለች።
"ዳይሬክቶሬት ማቋቋም ብቻ ሳይሆን እውነተኛ ሥራ ያስፈልጋል። ታች ካለ ፖሊስ እስከ መጨረሻ የፍትሕ አካላት ድረስ ጥቃት የደረሰባትን ሴት እንዴት እንደሚያስተናግዱ መገንዘብ አለባቸው" ትላለች።
ከጾታዊ ጥቃት ጋር በተያያዘ የመረጃ ክፍተት እንዳለ የምትገልጸው ሩት፤ ስንት ሴቶች ላይ ጥቃት ይደርሳል? የሚለውን ጨምሮ ሌሎችም ተያያዥ መረጃዎች ተቀናጅተው ቢገኙ ጥሩ እንደሆነ ታክላለች።
"ይህ የተዳፈኑ ጉዳዮችን ለመያዝ፣ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠትም በጣም ጥሩ ነው። ብዙ ጊዜ የሴቶች መብት ተሟጋቾች እስኪጮሁ ድረስ ምንም አይሠራም። ፍርድ ይጓተታል። ተዳፍኖ ይቀራል። መደራደር ይባላል። ይህንን የሚከታተል መቋቋሙ ጥሩ ነው።"
ጾታዊ ጥቃት ሲደርስ ከደፋሪው በበለጠ ተጎጂዋ እንድትሸማቀቅ እንደሚደረግ በመጥቀስ፤ ብሔራዊ የጥቃት አድራሾች መረጃ ሥርዓት መጀመሩን በበጎ ታየዋለች።
አሠራሩ፤ ተጎጂዎች እንዲሸማቀቁ የሚያደርገው ማኅበረሰባዊ ትርክት እንዲቀየር እንደሚረዳ ታምናለች።
"እከሌ እንዲህ አድርጓል መባል አለበት። መታወቅ አለባቸው። ማኅበረሰቡ ጣቱን ከተበዳይ ወደ በዳይ መቀሰር እስኪጀምር መቀጠል አለበት" ብላለች።
የ'ዝም አልልም' ንቅናቄ መሪዎች አንዷ የሆነችው ድምፃዊት ፀደንያ ገብረማርቆስም የሩትን አስተያየት ትጋራለች።
"ወሲባዊ ጥቃት ላይ ብቻ አተኩሮ የሚሠራ ግብረ ኃይል መቋቋሙ ትልቅ ነገር ነው" ትላለች።
መደፈርና ሌሎችም ወሲባዊ ጥቃቶች ከሌሎች ወንጀሎች በተለየ መንገድ መታየት እንዳለባቸው አለመረዳት በአጠቃላይ የፍትሕ ሥርዓቱ እንደሚስተዋል በማጣቀስ፤ የግብረ ኃይሉ መኖር የለውጥ ጅማሮ እንደሚሆን ተስፋ ታደርጋለች።
"በፊት በአፈጻጸም፣ በሕጉና የአቅምም ውስንነት ነበረ። ወሲባዊ ጥቃትን ላይ [በመግታት ረገድ] እስካሁን ለውጥ ያላየነውም ለዚሁ ነው። ከዚህ በኋላ በተወሰነ ደረጃ ለውጥ ይመጣል ብዬ አስባለሁ" ስትል ፀደንያ ታስረዳለች።
ብሔራዊ የጥቃት አድራሾች መረጃ ሥርዓት፤ ጥቃት ፈጻሚዎችን ወደ አደባባይ በማውጣት፤ እንዲሸማቀቁ፣ ማኅበረሰቡን እንዲያፍሩም እንደሚያደርግ ትገልጻለች።
"እስከዛሬ ጥቃት የደረሰበትን እንጂ ጥቃት አድራሽን አናውቀውም ነበር። ፍርዳቸው የት እንደደረሰ እንኳን አጣርተን አናውቅም። የሰረቀ፣ የገደለና ሌላም ወንጀል የሠራ በአደባባይ ይታያል። ጥቃት አድራሾችስ ለምን አደባባይ አይታዩም? ወጥተው በአደባባይ መታየት አለባቸው።"
ማኅበረሰቡ ወሲባዊ ጥቃትን እንደ ወንጀል ገና እንዳልተረዳው የምትናገረው ፀደንያ፤ ጥቃት መፈጸም ከፍተኛ ወንጀል እንደሆነ ግንዛቤ መፍጠር ከሚቻልባቸው መንገዶች አንዱ የጥቃት አድራሾችን ማንነት በማጋለጥ ማሸማቀቅ እንደሆነ ትናገራለች።

















