በሊቢያ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ላይ በደረሰ ጥቃት በርካቶች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሊቢያዋ ዋና ከተማ ትሪፖሊ በሚገኝ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ላይ በደረሰ ጥቃት 28 ሰዎች ሲገደሉ በርካቶች መቁሰላቸውን የሊቢያ ባለሰልጣናት ተናገሩ።
ስለ ጥቃቱ ዝርዝር መረጃ ባይወጣም ለጄነራል ካሊፍ ኸፍታር ታማኝ በሆኑና በምስራቂያዊ ሊቢያ በመሸጉ አማፂያን የተፈፀመ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።
ከጥቃቱ በኋላ የተወሰደ ምስል እንደሚያሳው የሞቱ ሰዎች አካል በየስፍራው ወድቆ ይታይ ነበር።
የተባበሩት መንግሥታት የሚደገፈው የሊቢያ መንግሥት በጄነራል ኸፍተር የሚመራውን ሰርጎ ገብ እየተዋጋ ይገኛል።
"በትሪፖሊ በሚገኝ የወታደራዊ ትምህርት ቤት ላይ በደረሰ የአየር ጥቃት 28 ምልምል ወታደሮች ሲሞቱ በርካቶች ቆስለዋል" ሲሉ የተናገሩት የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ አሚን አል-ሀሼሚ ናቸው።
ሊቢያን ለረዥም ጊዜ ሲያስተዳድሯት የነበሩት ሙሐመድ ጋዳፊ እ.ኤ.አ. በ2011 ከስልጣን ከተወገዱና ከተገደሉ በኋላ ሀገሪቱ በግጭትና በክፍፍል እየታመሰች ትገኛለች።
ሀገሪቱን አንድ አድርጎ የሚያስተዳድር አካልም የለም።
ባለፈው ዓመት በሚያዚያ ወር ላይ ጄነራል ኸፍተር በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፈውን የትሪፖሊውን መንግሥት ከስልጣን ለማስወገድ ዘመቻ ከፍተው ነበር።













