ህወሃት በታሪኩ የመጀመሪያ የሆነውን አስቸኳይ ጉባዔ እያካሄደ ነው

የህወሃት መለያ አርማ

የፎቶው ባለመብት, TPLF FB

ህውሃት ከዛሬ ታህሳስ 25/2012 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆይ አስቸኳይ ድርጅታዊ ጉባኤ በመቀሌ ከተማ ሰማዕታት ሐውልት አዳራሽ እያካሄደ ነው።

እስካሁን 13 ድርጅታዊ ጉባዔዎችን ያካሄደው ህወሃት አስቸኳይ ጉባዔ ሲጠራ ይህ የመጀመሪያው ነው።

በጉባዔው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የህወሃት ሊቀመንበር ደብረፂዎን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር)፤ ጉባዔውን "ቀጣይ የህወሃትን ህልውና የሚወስን ልዩና ታሪካዊ ጉባዔ ነው" ብለውታል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም፤ ጉባኤው በህወሃት ፍላጎት የተጠራ ሳይሆን፤ በአገሪቷ ያለው ሁኔታ አስገድዶ የተጠራ አስቸኳይ ጉባዔ መሆኑንም ተናግረዋል።

የፓርቲው ጽ/ቤት ኃላፊና ከጉባዔው አስተባባሪ ኮሚቴዎች አንዱ የሆኑት አቶ አለም ገ/ዋህድ የጉባዔውን ሦስት አጀንዳዎች አስተዋውቀዋል።

ከኢህአዴ መፍረስና እና ከአዲሱ ብልፅግና ፓርቲ መመስረት ጋር በተያያዘ የማዕከላዊ ኮሚቴውን በጥልቀት መገምገም፣ በምርጫ አዋጅ መሠረት የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና ሥነ ምግባር ጋር እንዲሁም ከኢህአዴግ ጋር ስላላቸው ግንኙነት የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በፓርቲው የመተዳደሪያ ደንብ ላይ ለውጥ ለማድረግ እና የፓርቲው ፕሮግራም ከኢህአዴግ ጋር ከነበረው ግንኙነት እና ከወቅቱ ጋር የሚሄዱ ጉዳዮችን ለማሻሻል እንደሆነ አስረድተዋል።

በጉባዔው ላይ ከፓርቲው አባላት ውጭ እስከ 150 የሚሆኑ ምሁራን፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የተለያዩ ብሔረሰብ ተወካዮች እና ሌሎች እንግዶች በመክፈቻውና እና በመዝጊያው ላይ ብቻ እንዲሳተፉ መፈቀዱም ታውቋል።

ዛሬ ጠዋት የተጀመረው ጉባኤ በአጀንዳዎቹ ላይ ውሳኔ በማሳለፍ ነገ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

Presentational grey line

በተመሳሳይ የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የመጀመሪያውን ስብሰባ ትናንት ማካሄዱ ይታወሳል።

ፓርቲው ከግንባር ወደ ውህደት ከተሸጋገረ በኋላ የመጀመሪያውን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ነበር ያካሄደው።

በስብሰባው ላይ ውይይት ከተደረገባቸው አጀንዳዎች መካከል ምርጫ 2012 አንዱ መሆኑ ተነግሯል።