የአንጎላ መንግሥት የቀድሞ ፕሬዝደንት ልጅ ዶስ ሳንቶስ ንብረት በቁጥጥር ሥር እንዲውል አዘዘ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአንጎላ ፍርድ ቤት የቀድሞ የሃገሪቱ ፕሬዝደንት ሴት ልጅ ቢሊየነሯ ኢሳቤል ዶስ ሳንቶስ ንብረት እና ባንክ ያላቸው ገንዘብ በቁጥጥር ሥር እንዲውል አዟል።
ነዳጅ ጠገቧ ሃገር አንጎላ የሙስናን አከርካሪ እሰብራለሁ ብላ ቆርጣ ከተነሳች ሰንበትበት ብላለች።
የፕሬዝደንት ጃዎ ሎሬንሶ መንግሥት በኢሳቤል ዶስ ሳንቶስ እጅ ውስጥ ያለ 1 ቢሊየን ዶላር አስመልሳለሁ እያለ ነው።
ኢሳቤል ዶስ ሳንቶስ እኔ በአባቴ ዘመን የፈፀምኩት በደል የለም ንበረቴም በቁጥጥር ሥር ሊውል አይገባም ስትል ስሞታ አሰምታለች።
ኢሳቤል በአፍሪካ ሃብታሟ ሴት የሚል ስያሜ የተሰጣት ግለሰብ ናት። ፎርብስ የተሰኘው የቱጃሮች ገንዘብ ቆጣሪ መፅሔት ኢሳቤል 2.2 ቢሊዮን ረብጣ ዶላር አላት ሲል የሃብት መጠኗን ይተነብያል።
የ46 ዓመቷ ኢሳቤል ዶስ ሳንቶስ ሕይወቴ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ በመስጋቴ ነው በሚል ምክንያት ኑሮዋን ከአንጎላ ውጭ አድርጋለች።
ታላላቅ ኩባንያዎችን በማስተዳደር የምትታወቀው ኢሳቤል አንጎላ እና ፖርቹጋል ውስጥ ትልቅ ድርሻ ያላቸው ድርጅቶች አሏት።
የአንጎላ መንግሥት ግለሰቧ አንጎላ ውስጥ በሚገኙ ትላልቅ ድርጅቶች ውስጥ ያላት የአክስዮን ድርሻ እና የባንክ ደብተሯ ነው በቁጥጥር ሥር እንዲውል ያዘዘው።
ኢሳቤል፤ ድርጊቱ በፖለቲካ የተሟሸ ነው ስትል ንብረቷ በቁጥጥር ሥር እንዲውል መድረጉን በክፉ አውግዛለች።
ዶስ ሳንቶስ በግሪጎሪ አቆጣጠር 2016 ላይ አባቷ የአንጎላ ነዳጅ አውጭ ኩባንያ ኃላፊ አደርገው ሲሾሟት ነበር ወደ እውቅና ጣራ የተመነጠቀችው።
በቀጣዩ ዓመት ግን አባቷን ተክተው ወደ ሥልጣን በመጡት ፕሬዝደንት ጆሴ ፊሎሜኖ ዶስ ሳንቶስ ተባረረች።














