ሩስያ፡ ከንቲባው የዱር እንስሳትን የሚያሳትፍ ሰርከስ ከለከሉ

የፎቶው ባለመብት, Alexander Demianchuk/TASS/Getty Images
በደቡባዊ ሩስያ የምትገኘው ሜጋስ ከተማ ከንቲባ የሆኑት ባስላን ሴቾይቭ የዱር እንስሳትን የሚያሳትፍ ሰርከስ ማገዳቸውን አስታውቀዋል።
ከንቲባው "የዱር እንስሳት ትርኢት ያለበት ሰርከስ እጅግ የከፋ የእንስሳት መብት ጥሰት ነው። እንስሳቱ እንዲኖሩ የሚደረጉት ባልተመቸ ቦታ ነው። ሜጋስ ውስጥ የዱር እንስሳ የሚጠቀም ማንም የሰርስ ባለሙያ ትርኢት እንዲያሳይ አይፈቀድለትም" ብለዋል።
ሩስያ ዘመናት ያስቆጠረ የሰርከስ ባህል ያላት ሀገር እንደመሆኗ የከንቲባው ውሳኔ የመገናኛ ብዙሀንን ትኩረት ለመሳብ ግዜ አልወሰደበትም።
ውሳኔያቸውን ተከትሎም በቅርቡ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረ የሰርከስ ትርዒት ተሰርዟል።
በተያያዥም የከተማው ካውንስል፤ ታዳጊዎች በምን መንገድ እንስሳትን መያዝ እንዳለባቸው የሚማሩበት ንቅናቄ እንደሚጀምርም ይፋ አድርጓል።
ከንቲባው፤ የዱር እንስሳትን በሰው ሰራሽ ማቆያ ውስጥ እያኖሩ ለሰረከስ ትርኢት መጠቀም "እንስሳቱን እንደ እስረኛ ማድረግ ነው" ብለዋል።
የ38 ዓመቱ ከንቲባ፤ ከተማዋን ለአራት ዓመታት ያስተዳደሩ ሲሆን፤ የእንስሳትን መብት ለማስጠበቅ በሚያደርጉት ጥረት ይታወቃሉ። አዘውትረውም አቋማቸውን በኢንስታግራም ገጻቸው ለሕዝብ ያጋራሉ።
ከዚህ ቀደም ሰው ሰራሽ የዶልፊኖች ማቆያ ይሠራ ሲባል አሻፈረኝ ብለው ነበር። "እነዚህ ተወዳጅ እንስሳት መኖር ያለባቸው በነጻነት በተፈጥሯዊ አካባቢያቸው ነው" ብለዋል።
መኖሪያ ለሌላቸው እንስሳት ማቆያ እንዲሠራ አድርገዋል። ድመቶችና ውሾች ሲበርዳቸው ቤታቸውን በማሞቅ፤ ሲሞቃቸው ደግሞ ሰውነታቸውን የሚያቀዘቅዙበት መዋኛ ገንዳ አሠርተዋል።
የዱር እንስሳትን የሚያሳትፍ ሰርከስ በበርካታ የአውሮፓ ሀገሮች ታግዷል። ከንቲባውም ከዓለም አቀፍ የእንስሳት መብት ተሟጋቾች ጋር የሚጣጣም ውሳኔ በማስተላለፍ ሩስያ ውስጥ የሚደርስባቸው የለም።












