የቱኒዚያው ጤና ጥበቃ ሚኒስትር በ11 ህፃናት ሞት ምክንያት ስልጣን ለቀቁ

የቱኒዚያ ሰንደቅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የቱኒዚያ ህክምና አገልግሎት በሰሜን አፍሪካ አድናቆት የተቸረው ነበር

ጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ አብደራሁፍ ቸሪፍ ስልጣናቸውን የለቀቁት በአገሪቱ መዲና ቱኒዝ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ባለቀው ሳምንት በሁለት ቀናት ውስጥ ብቻ 11 ህፃናት ከኢንፌክሽን ጋር በተያያዘ ህይወታቸው ማለፉን ተከትሎ ነው።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ከተሾሙ ገና አራት ወራቸው ነበር።

ሁኔታውን ተከትሎ የቱኒዚያ ጠቅላይ ሚኒስትር የሱፍ ቻሂድ በአገሪቱ አጠቃላይ የመንግስት ጤና ተቋማት፣ የመድሃኒትና የህክምና መሳሪያዎች አቅርቦት ተቋማት ሰፊ ምርመራ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።

የቱኒዚያ የህፃናት ሃኪሞች ማህበር በፌስቡክ ገፁ እንዳስታወቀው ለ11ዱ ህፃናት ህልፈት ምክንያት የሆነው ኢንፌክሽን ደረጃውን ባልጠበቀ መድሃኒት የተከሰተ ሊሆን ይችላል።

ማህበሩ በአገሪቱ የጤና ባለሙያዎች አገልግሎት እየሰጡ ያለበት ሁኔታም አደገኛ መሆኑን ጠቁሟል።

ቀደም ባሉት ዓመታት የቱኒዚያ የህክምና አገልግሎት የተደነቀና በህክምና ቱሪዝምም ለአገሪቱ ጥሩ ገቢ ያስገኘ ነበር። ነገር ግን እንደ አውሮፓውያኑ በ2011 የፕሬዝዳንት ዜን ቢን አሊ ከስልጣ መውረድን ተከትሎ የአገሪቱ ጤና ዘርፍ በአመራር ጉድለትና በገንዘብ እጥረት ከባድ ችግር ውስጥ ወድቋል።