በከፊል አንድ አይነት ስለሆኑ መንትያዎች ሰምተው ያውቃሉ?

የፎቶው ባለመብት, QUEENSLAND UNIVERSITY OF TECHNOLOGY
በከፊል አንድ አይነት የሆኑ መንትያዎች ለሁለተኛ ጊዜ ተወልደዋል። የህክምና ባለሙያዎች እንዳረጋገጡት ይህ ክስተት ከዚህ በፊት የተፈጠረው አንዴ ብቻ ነው።
አንዲት እናት በአውስትራሊያ፣ ብሪዝቤን ውስጥ የጸነሰቻቸው ልጆች በከፊል አንድ አይነት የሆኑ መንትዮች ናቸው።
ልጆቹ ወንድና ሴት ሲሆኑ በእናታቸዉ በኩል ተመሳሳይ ናቸው። ከአባታቸው የዘር ቅንጣት (ዲኤንኤ) ግን የተለየየ የዘር ፍሬ በመዉሰዳቸዉ አይመሳሰሉም።
ባለሙያዎች እንደሚሉት እንደዚህ አይነት አጋጣሚዎች በጣም ዉስን ከመሆናቸዉም በላይ ቢከሰት እንኳ ጽንሱ የማደግ እድል የለውም።
የህክምና ሂደቱን የተከታተሉት ፕሮፌሰር ኒኮላስ ፊስክ እንደገለጹት በስድሰተኛዉ ሳምንት በተደረገ ምርመራ ጽንሱ ተመሳሳይ መንትያዎች እንዳሉት የሚያሳይ ግኝት ነበረዉ። ነገር ግን 14ኛው ሳምንት ላይ የተደረገዉ ምርመራ ጽንሱ በከፊል አንድ አይነት መንትያዎችን መያዙ ተረጋግጧል።
በከፊል ተመሳሳይ ጽንስ እንዴት ተፈጠረ?
አንድ የወንድ ዘር በተመሳሳይ ጊዜ የአንዲትን የሴት እንቁላል ብቻ ሰብሮ እንዲበለጽግ ካደረገና ለሁለት ከተከፈለ ተመሳሳይ መንትያ ይፈጠራል። በዚህ መልኩ የሚፈጠሩ ልጆች ተመሳሳይ ጾታ ሲኖራቸዉ ተመሳሳይ አካላዊ ቅርጽና ባህሪ ይኖራቸዋል።
የተለያዩ መንትያዎች የሚፈጠሩት ሁለት የሴት እንቁላሎች ለየብቻቸዉ በሁለት የተለያየ የወንድ ዘር ሲበለጽጉ ነው። እነዚህ ልጆች በጾታ ተመሳሳይ ሊሆኑም ላይሆኑም ይችላሉ።
አንድ ላይ ከመወለዳቸው በስተቀር ምንም የጋራ ነገር አይኖራቸውም። ልክ እንደማንኛዉም ወንድምና እህት የመልክ መቀራረብ ካልሆነ መንታ በመሆናቸዉ የሚጋሩት ነገር አይኖርም።
አሁን መነጋገሪያ የሆነው በከፊል አንድ አይነት የሆኑ መንትያዎች ጉዳይ ነው። ክስተቱ የሚፈጠረዉ የአንድ ሴት እንቁላል በሁለት የወንድ ዘር ሲበለጽግ ነው።
በሳይንሱ መሰረት አንድ እንቁላል በሁለት የወንድ ዘር ከበለጸገ እንቁላሉ ሲከፈል ሶስት ክሮሞዞም ይኖረዋል። ነገር ግን ብዙ ጊዜ የተለመደው ሁለት ነው (ይህ ማለት አንድ ከእናት አንድ ከአባት)።
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በዚህ መልኩ የሚፈጠር ክሮሞዞም ህይወት የመሆን እድል የለውም። ምክንያቱም ሁለት ከአባት ስለሆነ በሁለት የወንድ ዘር አንድ እንቁላል ሊበለጽግ አይችልም።
ነገር ግን በአውስትራሊያ፣ ብሪዝቤን ይህ ክስተት ባልተለመደ መልኩ ህይወት ያላቸዉ ልጆችን ፈጥሯል። ካሁን በፊት ተመሳሳይ ክስተት እንደ አውሮፓውያኑ በ2007 በአሜሪካ ውስጥ ተከስቶ ነበር።












