ከትግራይ የተለቀቁት የጦር ምርኮኞች እንዳልሆኑ መንግሥት አስታወቀ

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በምርኮ የተያዙ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ሰኔ መጨረሻ 2013 ዓ.ም. በትግራይ መዲና መቀለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በምርኮ የተያዙ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ሰኔ መጨረሻ 2013 ዓ.ም. በትግራይ መዲና መቀለ

በትግራይ አመራሮች ምህረት ተደርጎላቸው ተለቀዋል ከተባሉት የጦር ምርኮኞች መካከል አብዛኛዎቹ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ "ሰራዊቱ ትግራይን ለቆ በወጣበት ወቅት ታግተው የቀሩ የሰራዊቱ የቤተሰብ አባላት" እንደሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ገለጸ።

የፌደራል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የተለቀቁት ግለሰቦች የጦር ምርኮኞች አለመሆናቸውን ባስታወቀበት በዛሬ ግንቦት 14 ፣ 2014 ዓ.ም መግለጫው "በሃሰተኛ መረጃና ፕሮፓጋንዳ የአለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማደናገር የተደረገ ሙከራ ነው" ብሏል።

የትግራይ አመራሮች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተማረኩ 4 ሺህ 208 የመከላከያ ሰራዊት አባላት የጦር ምርኮኞች ግንቦት 12፣ 2014 ዓ.ም መለቀቃቸውን አስታውቀዋል።

የምርኮኞቹ መለቀቀቅ የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይና የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ የ18 ወራቱ የእርስ በርስ ጦርነት በሰላም እንዲቋጭ ያደረጉት ጥረት አካል መሆኑንም የትግራይ አመራሮች ባወጡት መግለጫ ጠቅሰዋል።

መግለጫው በተጨማሪም ህወሃት ከተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ለስራ ትግራይ ክልል ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሲቪል ነዋሪዎችን በማገት "የፖለቲካ ትርፍ አገኝበታለሁ ባለው የፕሮፖጋንዳ ድራማ የመከላከያንና የተለያዩ ጸጥታ ሃይሎችን መለዮ በማልበስ በምርኮኛ ስም አሰልፏቸዋል" ብሏል።

በተጨማሪም በአማራና አፋር ክልሎች በግዳጅ ወስዷቸዋል ያላቸውንም ግለሰቦችንም ምርኮኛ በማለት " የሃገር ውስጥም ሆነ አለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማጭበርበር እየሞከረ ነው " ብሏል።

የተለቀቁት አብዛኛው የጦር ምርኮኞች ከትግራይ ውጪ በተካሄዱ ዓውደ ውጊያዎች የተማረኩ እና በቅርብ የተመለመሉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት መሆናቸውን የትግራይ አመራሮች ማስታወቃቸው ይታወሳል።

የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማህበር በበኩሉ የጦር ምርኮኞቹ ይለቀቃሉ በተባለው ሂደት ምንም አይነት ተሳትፎ እንደሌለው ለቢቢሲ ተናግሯል።

የኮሙኒኬሽን መግለጫ በተጨማሪ ከሰሞኑ ህወሃት ለጦርነት በይፋ እየተዘጋጀ እንደሆነና የአሁኑም ድርጊቱ የዚህ ማሳያ እንደሆነም አስፍሯል።

በኢትዮጵያ መንግሥትና በትግራይ ኃይሎች የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መደረሱን ተከትሎ ለአስራ ስምንት ወራት የዘለቀው ጦርነት መቋጫ ሊሆን ይችላል የሚል ተስፋን ዘርቶ የነበረ ቢሆንም ከሰሞኑ ዳግም ጦርነት ይከሰት ይሆን የሚሉ ፍንጮች ጥያቄ ፈጥረዋል።

ለዚህም እንደ ማሳያ የሚሆኑት ከትግራይ፣ ከኤርትራና ከአማራ ክልሎች የተሰሙ መግለጫዎች እንዲሁም በድንበሮች አካባቢ አልፎ አልፎ ተከስተዋል የተባሉ ግጭቶች ናቸው።

ከሰሞኑ የኤርትራ መንግሥት በማስታወቂያ ሚኒስቴሩ በኩል ባሰፈረው መልዕክት ህወሓት በኤርትራ ድንበር በኩል እና በምዕራብ ትግራይ አቅጣጫ በሁለት ግንባሮች ጦርነት ለመክፈት እየተዘጋጀ ነው ብሎ ነበር።

ለዚህም ከትግራይ አመራሮች በኩል በተሰጠው ምላሽ ኤርትራ በጦርነቱ በርካታ ጥሰቶችን እንደፈጸመችና እንዲሁም የትግራይን ግዛቶች ተቆጣጥራ እንደምትገኝ ጠቅሰው በሰላምም ይሁን በሌላ መንገድ ከእነዚህ ግዛቶች ነጻ ይወጣሉ ብለዋል።

ከቀናት በፊት ደግሞ የአማራ ክልል ከህወሓት በኩል ሊሰነዘር ይችላል ላለው ሌላ ዙር ወረራ የክልሉ የፀጥታ መዋቅር ዝግጁ እንዲሆን ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በበኩሉ በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ኃይሎች እና በፌደራል መንግሥት ኃይሎች መካከል ውጥረት እየጨመረ መምጣቱ እንዲሁም አልፎ አልፎም ግጭቶች ሪፖርት መደረጋቸው እንዳሳሰበው ገልጾ ነበር።