ፊንላንድ እና ሰዊድን ታሪካዊ በተባለ ውሳኔ በይፋ ኔቶን እንቀላቀላለን አሉ

የስዊድን ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የስዊድን ወታደሮች

ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ ስዊድንና ፊልናድ ታሪካዊ በተባለው ውሳኔያቸው የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) ለመቀላቀል መወሰናቸውን ይፋ አድርገዋል።

ሞስኮ በኪዬቭ ላይ ያደረገችው ወረራ ሁለቱ አገራት ኔቶን የመቀላቀል ሃሳብ እንዲኖራቸው ምክንያት መሆኑ በስፋት ሲዘገብ ቆይቷል።

ስዊድን ውስጥ በስልጣን ላይ የሚገኘው የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ የኔቶን ጥምረት የመቀላቀል ሀሳብ እንደሚደግፈው በመግለጽ አገሪቱ በፍጥነት ማመልከቻዋን እንድታስገባ ተገቢውን እርምጃ እንደሚወስድ ገልጿል።

የስዊድን ውሳኔ የተሰማው የሩሲያ ጎረቤት የሆነችው ፊንላንድ ኔቶን ለመቀላቀል ይፋዊ ጥያቄዋን እንደምታቀርብ ካስታወቀች በኋላ ነው።

ሩሲያ በበኩሏ ኔቶ በድንበሯ አካባቢ የሚገኙ አገራትን በአባልነት የሚመዘግብ ከሆነ የደህንነት ስጋት እንደሚፈጠርባትና ብዙ መዘዞችን እንደሚያስከትል ስታስጠነቅቅ ቆይታለች።

ስዊድን ለበርካታ ዓመታት ከማንኛውም አይነት ወታደራዊ ጥምረት ውስጥ ሳትገባ ገለልተኛ ሆና ቆይታለች።

ፊንላንድ ደግሞ 1300 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ድንበሯን ከሩሲያ ጋር የምትዋሰን ሲሆን አገሪቱ የኔቶ አባል አገር ሳትሆን የቆየችውም ጎረቤት ሩሲያን ላለማስቆጣት ነው።

ፕሬዝዳንት ፑቲን የፊንላንድ ኔቶን የመቀላቀል እርምጃ ትልቅ ምላሽ የሚያስከትልና ስህተት የሆነ ነው ቢሉም በትክክል ግን ምን አይነት እርምጃ እንደሚወስዱ አልገለጹም።

ነገር ግን የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ሩሲያ ምላሽ እንደምትሰጥ አስታውቋል።

የስዊድኑ ገዢ ፓርቲ ባወጣው መግለጫ የኔቶ አባል መሆን የሚለውን ሀሳብ አብዛኛው ዜጋ እንዲሁም ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ጭምር የሚደግፉት እንደሆነ ገልጿል። በቅርብ ቀናት ውስጥ ደግሞ ሰዊድን ኔቶን ለመቀላቀል ይፋዊ ጥያቄዋን እንደምታቀርብ ይጠበቃል።

የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ማግዳሌና አንደርሰን በበኩላቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ''ጥምረቱ ለስዊድንም ሆነ ለህዝቦቿ ደህንነት የሚፈጥር ነው'' ሲሉ ተደምጠዋል።

''ከዚህ በፊት በነበሩት ጊዜያት ምንም አይነት ወታደራዊ ጥምረት ውስጥ አለመግባታችን በጣም ጠቅሞናል። ወደፊት ግን በዚሁ መቀጠል የምንችል አይመስለኝም። በክልሉ የኔቶ አባል አለመሆናችን ተጋላጭ ያደርገናል'' ሲሉ አክለዋል።

የፊንላንዱ ፕሬዝዳንት ሳኡሊ ኒኒስቶ ደግሞ አገራቸው ለኔቶ አባልነት ጥያቄዋን እንደምታቀርብና ይህም ቀን ታሪካዊ እንደሆነ አስታውቀዋል።

ፊንላንድ የኔቶ አባል ስለመሆን ካሰበች ወዲህ ሩሲያ ለአገሪቱ ታቀርበው የነበረውን የኤልክትሪክ ኃይል ማቋረጧ የሚታወስ ነው። የሩሲያው የኃይል አቅራቢ 'ራኦ ኖርዲክ' እንዳለው አቅርቦቱ የተቋረጠው ከክፍያ ጋር በተያያዘ ነው።

ፊንላንድ ግን የኃይል አቅርቦቱ መቋረጥ እዚህ ግባ የሚባል ችግር እንዳላስከተለባት ገልጻለች። የአገሪቱ ብሄራዊ የኃይል ኃላፊው ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ''ሩሲያ ኃይል ማቋረጧ ምንም አይነት ችግር አልፈጠረብንም'' ብለዋል።

ኃላፊው አክለውም ከሩሲያ የሚገባው የኃይል አቅርቦት ከአገሪቱ ፍላጎት 10 በመቶ የሚሆነውን ብቻ እንደሚሽፍንና በሌሎች አማራጮች ሊተካ እንደሚችል ገልጸዋል።

የሩሲያና የፊንላንድ መሪዎች ቅዳሜ ዕለት በስልክ ውይይት አድርገው ነበር። ከውይይታቸው በኋላም ክሬምሊን ባወጣው መገልጫ ፊንላንድ ከዚህ በፊት ትከተለው የነበረው ገለልተኛ አቋሟን ለመቀየር ማሰቧ ትልቅ ስህተት እንደሆነና ለደህንነቷም የሚያሰጋት እንደሆነ የሩሲያው መሪ ማሳሰባቸውን ገልጿል።

የፊንላንዱ ፕሬዝዳንት በበኩላቸው ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ የአገራቸው ደህንነት አደጋ ላይ መውደቁንና ይህ ደግሞ እንደሚያሰጋቸው ለሩሲያው ፕሬዝዳንት አስረድተዋል።

አክለውም ''ያደረግነው ንግግር ቀጥተኛና በትክከል ጉዳዩን ስለመፍታት ነበር። የተፈጠሩ ውጥረቶችን ማርገብ ደግሞ ወሳኝ እንደሆነ ተግባብተናል'' ብለዋል።