የኮቪድ ወረርሽኝ ትልቅ አደጋ ነው - ኪም ጆንግ ኡን

የፎቶው ባለመብት, EPA
በሰሜን ኮሪያ በፍጥነት እየተዛመተ ያለው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለሀገሪቱ "ትልቅ አደጋ" ነው ሲሉ መሪዋ ኪም ጆንግ ኡን መናገራቸውን የመንግሥት ሚዲያዎች ዘግበዋል።
ለመጀመሪያ ጊዜ በኮሮናቫይረስ ሞት መመዝገቡን ያስታወቀችው ሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም በያዝነው ሳምንት ቅዳሜ ዕለት ባደረጉት አስቸኳይ ስብሰባ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ሁለንተናዊ ትግል እንዲደረግ ጠይቀዋል።
ባለስልጣናቱ በያዝነው ሳምንት ሃሙስ ለመጀመሪያ ጊዜ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች መገኘታቸው መረጋገጡን አስታውቀዋል። ባለሙያዎች በበኩላቸው አሁን ተያዙ የተባሉት የመጀመሪያ እንዳልሆኑና ለተወሰነ ጊዜ እየተዛመተ ነበር ይላሉ።
በሰሜን ኮሪያ ወረርሽኙ ከፍኛ ሊሆን እንደሚችልና አስከፊ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋትም ጭሯል።
25 ሚሊዮን ነዋሪዎቿ በክትባት መርሃ ግብር እጥረት እና በደካማ የጤና አጠባበቅ ስርአት ምክንያት ለአደጋ የተጋለጡ መሆናቸውም ተገልጿል።
ባለፉት ሳምንታት ውስጥ ግማሽ ሚሊዮን ህዝብ በማይታወቅ ትኩሳት እንደተጠቁ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ቅዳሜ እለት ዘግበዋል።
የሃገሪቱ የመመርመር አቅምም የተገደበ በመሆኑ በኮቪድ-19 ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ አልተረጋገጠም።
ይህ አኃዝ አርብ እና ሐሙስ ከፍተኛ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን ይህም ሁኔታ በሰሜን ኮሪያ እየተከሰተ ስላለው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ አንዳንድ ፍንጮችን ይሰጣል ተብሏል።
"የከፋው ወረርሽኝ በአገራችን ላይ የወደቀ ትልቅ አደጋ ነው" በማለት መሪው መናገራቸውን የኬ ሲ ኤንኤ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ኪም ለዚህ ችግር መንስኤ ያሉትን የቢሮክራሲ ቀውስ እና የህክምና ብቃት ማነስ እንደሆነ ጠቁመው እንደ ጎረቤት ቻይና ካሉ ሀገራት ምላሽ መማር እንደሚቻልም ጠቁመዋል።
ከሚያዝያ ወር ጀምሮ 27 ሰዎች ትኩሳት ካጋጠማቸው በኋላ መሞታቸውን የመንግስት ሚዲያዎች ዘግበዋል።
በዋና ከተማዋ ፒዮንግያንግ በኦሚክሮን ልውጥ ከሞተው አንድ ሰው በስተቀር እነዚህ ግለሰቦች ኮቪድ- 19 ተይዘው ነበር ወይ ስለሚለው ጉዳይ ሪፖርቶቹ ያሉት ነገር የለም።












