መንግሥት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾቹ ሪፖርት ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነው አለ

ኮሚኒኬሽን አገልግሎት

የፎቶው ባለመብት, FDRE Gov't Comm Service

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዎች በምዕራብ ትግራይ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል ደርሷል የሚል ሪፖርት በትናንትናው ዕለት መጋቢት 28/2014 ዓ.ም ማውጣታቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ምላሽ ሰጥቷል።

የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ትናንት ማምሻውን በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ ሪፖርቱ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነው ብሏል።

የፌደራሉ መንግሥት ሁለቱ ተቋማት ጉዳዩን ለመመርመር የተጠቀሟቸውን ፖለቲካዊ ጉዳዮች ትክክለኛነት ላይ ጥያቄ አቅርቧል።

የውስጥ ወሰን ጉዳዮች ሊታዩ የሚገባቸዉ ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን ባላቸው አካላት ነው ያለው መንግሥት፤ "እንዲህ አይነቱ ሪፖርታቸው ለፖለቲካ ፍጆታ እንደሚውልም የታወቀ ነው። ይህ አመለካከት ምርመራው በተገቢው ጥንቃቄ አለመፈፀሙን ከማሳየቱም በላይ በፍፁም ተቀባይነት የሌለው ነው።" ብሏል።

በመጀመሪያ የጠቀሰው የአገሪቱ የውስጥ ወሰን ጉዳዮች ሲሆን እነዚህ ወሰኖች ሊታዪ የሚገባቸው ህገ መንግሥታዊ ስልጣን ባላቸው አካላት መሆኑን ጠቅሶ አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂውማን ራይትስ ዎች "በእንደዚህ አይነት ጉዳዮች ላይ ፍርድ መስጠት ብልህነት የጎደለው ነው" ብሎታል።

ሪፖርቱ ብሄር ተኮር ይዘት አለው ያለው ይህ መግለጫ ይህም ሁኔታ መንግሥትን እንደሚያሳስበው አስፍሯል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዋች ባወጡት 207 ገጽ የጋራ ምርመራ ሪፖርት በምዕራብ ትግራይ ያሉ ጊዜያዊ አስተዳደሮች፣ የክልል ባለስልጣናት እንዲሁም የአማራ ክልል የጸጥታ ኃይሎች በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እና እንደ ጦር ወንጀሎች ሊቆጠር የሚችል የዘር ማፅዳት ዘመቻ በትግራይ ተወላጆች ላይ ከጦርነቱ መባቻ ጀምሮ ፈፅመዋል ብለዋል።

በተጨማሪም የትግራይ ታጣቂዎች ማይካድራ ላይ በአማራ ተወላጆች እና ሰራተኞች ላይ በፈጸሙት ጭፍጨፋ የጦር ወንጀል መፈጸማቸውን አመላክቷል።

ድርጅቶቹ እነዚህ ጥቃቶች በሰብአዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች እና የጦር ወንጀሎች መሆናቸውን ማረጋገጣቸውንም አስፍሯል።

ይህንንም አስመልክቶ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን በሰጠው ምላሽ "አንዱን ወገን ለማስደሰት በሚሞክርበት ጊዜ ውንጀላውን ተመጣጣኝ ባልሆነ መንገድ የሚከፋፍል ይመስላል። ይህ ምልከታ ጥላቻን በማቀጣጠል ጠንካራ ሃገርን ለመገንባት በፅኑ የሚያስፈልገውን እርቅ የበለጠ ያርቀዋል።" ብሏል።

ሪፖርቱ "ስሜት ቀስቃሽ ተደርጎ እንደቀረበና የሚዲያ ዘገባ አቀራረብን የተከተለ" በሚል የተቸው ሲሆን "የግኝቶቹንም ይዘትና ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባም ነው።" በማለት ጠቅሷል።

በሌላ በኩል አንድን ቡድን ብቻ ወቅሷል ያለው ይህ ሪፖርት ይህም ሁኔታ " ለሰብአዊ መብት መከበርና ለሰላም መስፈን አይበጅም።" ብሏል።

በተጨማሪም "በሪፖርቱ ውስጥ ያሉ "ሌሎች ድክመቶችም በግልፅ የሚታዩ ናቸው።" ሲልም ጠቅሷል።

ከነዚህም መካከል ሪፖርቱ የተመሰረተዉ በአብዛኛው" ለአንዱ ቡድን ቀረቤታ ባለቸዉ እማኞች ወይም ምስክሮች ላይ መሆኑም ሚዛናዊነቱን አስቶታል' በማለት ሚዛን እንደጎደለውም አስፍሯል።

ይህንን ሪፖርት ለመስራት ተቋማቱ የመደቧቸው ተመራማሪዎች ከጥቃቱ የተረፉ የአካባቢው ነዋሪዎችን፣ ቤተሰቦቻቸውንና የዓይን እማኞችን በአጠቃላይ በከተሞቹ እና መንደሮቹ የደረሰውን ጥቃት ለማወቅ ከ400 በላይ ግለሰቦችን ማናገራቸውንና ጦርነቱ ከመፈጠሩ በፊት ከዚህ ቀደም ምዕራብ ትግራይ ላይ በአምነስቲ ተመዝግበው የቀረቡ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ማካተታቸውን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በሱዳን በአምስት መጠለያ ካምፖች ከሚገኙ የትግራይ ስደተኞች ጋር በአካል ሰፋ ያለ ቃለ ምልልስ እንዲሁም ከምዕራብ ትግራይ የተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጆች፣ የአማራ ተወላጆች፣ የወልቃይት ነዋሪዎችና ከአማራ ክልል የመጡ ነዋሪዎች ማናገራቸውን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም የህክምና እና የፎረንሲክ ሪፖርቶች፣ የሳተላይት ምስሎችን እና መገኘት የቻሉትን ጥቂት ቪዲዮዎች እና ፎቶግራፎችን ማካተታቸውን ገልጸዋል። የግዛቱን ታሪክ እና ሁኔታ የበለጠ ለመረዳት ትምህርታዊ ጽሁፎችን፣ የታሪክ መዛግብትን፣ መጻህፍትን የመንግሥት ውሳኔዎችን እና ሪፖርቶችን ተመልክተናል ብለዋል።

ሁለቱም ድርጅቶች ወደ ትግራይ ገብተው ጥናታቸውን እንዲያከናውኑ ለኢትዮጵያ መንግሥት ጥያቄ ቢያቀርቡም ደብዳቤዎቻቸው ምላሽ እንዳላገኙም ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም መግለጫው "በሀገር መከላከያ ሰራዊትና በአማራ ልዩ ሃይል ላይ ፍትሃዊ ያልሆነ ዉንጀላ" ሪፖርቱ ሰንዝሯል ብሏል።

መግለጫው ሪፖርቱ ያተኮረው ወልቃይት ላይ እንደሆነና በሃገሪቱ ውስጥ የተከሰቱትንና በጥንቃቄ መታየት የሚገባቸውን የፖለቲካ ለውጦች፣ ሰላምና ደህንነት፣ የውስጥ ወሰን ጉዳዮችን ጨምሮ የዘር ማፅዳት፣ የጦር ወንጀል እና በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችንም ማካተቱን የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን መግለጫ ጠቅሷል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ አካላትን ተጠያቂ የማድረግ ቁርጠኝነት እንዳለው ያሰፈረው ይህ መግለጫ ለዚህም አንዱ ማሳያ የተባበሩት መንሥታት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነርና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የጋራ ምርመራን ተከትሎም የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል ማቋቋሙን ነው።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነርና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የጋራ ምርመራ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ችግር አጠቃላይ ምርመራ እንዳልሆነ ሪፖርቱ ማመኑን አምነስቲና ሂውማን ራይትስ ዎች አመልክተዋል።

ለዚህም የተመድ ሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነርና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መርማሪዎቻቸው በጸጥታ፣ የአሰራር እና የአስተዳደር ችግሮች ምክንያት ወደ ትግራይ አንዳንድ አካባቢዎች መሄድ አለመቻላቸውን ጠቅሰው የምርመራ ቡድኑ ሪፖርታቸውን ዳንሻ፣ ማይ ካድራ እና ሁመራ ከተሞችን ከጎበኙ በኋላ ያጠናቀሩት ሲሆን ከምዕራብ ትግራይ ተፈናቅለው በሽረ እንዲሁም በሱዳን ያሉ የትግራይ ተወላጆችን አለማካተቱን እነ አምነስቲ ገልጸዋል።

ሁለቱ ተቋማት አሁን ባወጡት ሪፖርትና በተመድ የተባባሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነርና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የጋራ ምርመራ ግኝት በርካታ ቁልፍ ልዩነቶች እንዳሉ ጠቅሰው ከዚህም አንዱ የአማራ ባለስልጣናት እና የጸጥታ ኃይሎቹ በትግራይ ተወላጆች ላይ ስለፈጸሙት ጥሰቶች እና የማሸበር ስልቶች ብዙም አለመጥቀሱን ነው።

የተመድና የኢሰመኮ ሪፖርት የአማራ የጸጥታ ኃይሎች በምዕራብ ትግራይ በሚገኙ ሴቶች እና ታዳጊዎች ላይ የፈጸሙትን የቡድን ደፈራ፣ የወሲብ ባርነት እና ሌሎች ጾታዊ ጥቃቶችን አላካተተም ብለዋል እነ አምነስቲ።

ሪፖርቱ ያስቀመጣቸው ምክረ ኃሳቦችም ለየትኛውም የሰላም ጥረት የማይጠቅሙ ናቸው ያለው መግለጫው መንግሥት ሁሉንም የሰብዓዊ መብት ጥሰት ክሶችን በጥልቀት መርምሮ ለህዝብ ይፋ ያደርጋል ብሏል።

ተቋማቱ እንደ ፋኖ ያሉ ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶችና ሚሊሻዎች ትጥቅ እንዲፈቱና ከደረሱት ጥሰቶች ጋር ግንኙነት ያላቸው ባለስልጣናት ታግደው በአፍሪካ ህብረት የሚመራ አለም አቀፍ ሰላም አስከባሪ ሃይል በምዕራብ ትግራይ እንዲሰማራ ጠይቀዋል።