መንግሥት ህወሓት ባለመተባበሩ እርዳታ በየብስ ማድረስ አለመቻሉን ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ሲባል ግጭት ማቆሙን ካሳወቀ በኋላ ከህወሓት በኩል አስፈላጊው ትብብር ባለመኖሩ በየብስ እርዳታ ትግራይ ማድረስ አልቻልኩም አለ።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ማክሰኞ መጋቢት 20/2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ክልል ላሉ ዜጎች በየብስ እርዳታው ለማቅረብ ጥረት ቢያደርግም ህወሓት ሊተባበር ባለመቻሉ የእርዳታ አቅርቦት ሥራው እክል ገጥሞታል ብሏል።
እንደ መግለጫው ከሆነ የእርዳታ አቅርቦት መተላለፊያ የሆነው የአብኣላ መንገድ በህወሓት ታጣቂዎች በመዘጋቱ የዓለም የምግብ ፕሮግራም እንዲያጓጉዝ የተዘጋጁት 43 የጭነት ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ መግባት አልቻሉም ብሏል፡፡
በሌላ በኩል ህወሓት የፌደራሉ መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ግጭት ለማቆም ወስኛለሁ ካለ አራት ቀናት ቢያልፉትም ትግራይ የደረሰ የሰብዓዊ እርዳታ የለም ብሏል።
ህወሓት ሰኞ መጋቢት 19/2014 ባወጣው መግለጫ፤ ግጭት ቆሞ የሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ የተደረሰው ስምምነት ተፈጻሚ ይሁን ሲል ጠይቋል።
"የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን በተመለከተ ሐሰተኛ ምክንያቶች ቆመው ያለአንደች መዘግየት በቂ የሰብዓዊ እርዳታ ትግራይ ይድረስ" ብሏል ህወሓት ያወጣው መግለጫ።
የፌደራሉ መንግሥት የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦትን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ላይ ደግሞ፤ ወደ ትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ግጭት ለማቆም መወሰኑን አስታውሶ፤ ሰብዓዊ እርዳታው እንዲደርስ የኢትዮጵያ መንግሥት በርካታ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል ብሏል፡፡
ከእነዚህ እርምጃዎች መካከል በሳምንት ሁለት ጊዜ ይደረግ የነበረውን የአየር በረራ በየቀኑ እንዲሆን ፍቃድ መሰጠቱን ገልጿል። በየብስም የሰብዓዊ እርዳታው በአብአላ በኩል እንዲቀርብ መፍቀዱን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ገልጧል።
አብኣላ በአፋር ክልል የምትገኝ የወረዳ ከተማ ስትሆን፤ ከሰመራ-መቀለ ዋነኛ መተላለፊያ ናት። አብአላ በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ከገባች ወራት አልፈዋል።
የፌደራሉ መንግሥት ወደ ትግራይ የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ቁርጠኛ ነኝ ያለ ሲሆን፤ የዓለም አቀፍ ተቋማት የትግራይ ኃይሎች ከያዟቸው የአማራ እና አፋር አካባቢዎች እንዲወጡ እና ግጭት ለማቆም የገቡትን ቃል እንዲያከብሩ ጫና እንዲያሳድሩ ጥሪውን አቅርቧል።
በተመሳሳይ ህወሓት ባወጣው መግለጫ ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭት ለማቆም መወሰኑን አስታውሶ፤ ዓለም አቀፉ ማኅብረሰብ ወደ ትግራይ ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እየቀረበ መሆኑን ያረጋግጥ ሲል ጥያቄ አቅርቧል።
አንድ ዓመት ተኩል የሆነው ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ የጦርነቱ ዋነኛ ማዕከል በሆነችው ትግራይ ውስጥ የሰብአዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች በየቀኑ 100 የጭነት ተሽከርካሪ እርዳታ ማቅረብ አስፈላጊ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ቢገልጽም የእርዳታ አቅርቦት ከተቋረጠ ወራት ተቆጥረዋል።
በዚህም ሳቢያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በከባድ ችግር ውስጥ መሆናቸው የተዘገበ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ መንግሥት እንዳለው በርካታ ሰዎች ድጋፍ ለማግኘት ከትግራይ ወደ አጎራባች ክልሎች እየተሰደዱ መሆኑን ገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት አመቺነት ግጭት የማቆም ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ ህወሓት ለዚሁ አርምጃ ተባባሪ መሆኑን እንደገለጸ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የአርዳታ አቅርቦቱ በየብስ ከሚቀርብበትና በህወሓት ከተያዘው የአፋር ክልል አካባቢ ኃይሎቹን እንዲያስወጣ የጠየቀ ሲሆን፣ አሁንም እርዳታው በአካባቢው የአማጺያኑ መኖር እክል ፈጥሯል ሲል ከሷል።

በ2013 ዓ. ም. ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች በተስፋፋው ጦርነት ምክንያት ከፍ ያለ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት መድረሱ የተነገረ ሲሆን፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለችግር ተዳርገዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ በሰሜን ኢትዮጵያ የሰብአዊ እርዳታ የሚያስፈልገው ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ገልጿል።
ጦርነቱ እስካሁን መቋጫ ስላላገኘ የተፈናቀሉትን ወደ ቀያቸው ለመመለስና እርዳታ ለማቅረብ አስቻጋሪ በመሆኑ በአስቸኳይ እርዳታ ማቅረብ ካልተቻለ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ እንደሚወድቅ የእርዳታ ድርጅቶች ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል።
ህወሓት የኢትዮጵያ መንግሥት እርዳታ ወደ ትግራይ ክልል እንዳይገባ እገዳ ጥሏል በማለት ሲከስ፣ መንግሥት ደግሞ በእርዳታ አቅርቦት መስመሮች ላይ ጥቃት በመክፈት የእርዳታ አቅርቦትን ያስተጓጎለው አማጺው ኃይል ነው ሲል መቆየቱ ይታወቃል።















