"መደፈሬ ያመኛል፣ ከልጄ ፊት መሆኑ ደግሞ መቼም እንዳልረሳው ያደርገኛል"

የኢንዱስትሪ ከተማዋ ኮምቦልቻ በትግራይ አማፂያን እና በፌደራል መንግሥቱ ኃይሎች መካከል ውጊያ ከተካሄደባት ወራት ተቆጥረዋል።
በከተማዋ ሕይወት ወደ ነበረበት የተመለሰ ይመስላል። ጦርነቱ በብዙ ነዋሪዎቿ ላይ ጠባሳ ጥሎ አልፏል።
ጠባሳው በብርቱ ካረፈባቸው ነዋሪዎች መካከል ፋቲማ አህመድ አንዷ ነች።
የፋቲማ አህመድ ጦርነቱ ከትውልድ ከተማዋ ሐይቅ በቅርብ ርቀት እየተደረገ መሆኑን ስትሰማ የህወሓት ኃይሎች ወደ ሐይቅ ከተማ ዘልቀው እንደማይገቡ እርግጠኛ ነበረች።
የፋቲማ የወቅቱ ቀዳሚ እቅድ የተሻለ ሕይወት ለመምራት ሥራ መጀመር ነበር። በአባቷ ሞት ምክንያት ትምህርቷን ከሰባተኛ ክፍል በላይ አልገፋችም።
ለጊዜው የዕለት ጉርስ ይሸፍናል ያለችውን ሥራ በመሥራት የእራሷንም የእናቷንም ሕይወት መደጎም ነበረባት።
በሐይቅ ከተማ ሥራ ፈልጋ አላገኘችም።
ሥራ አገናኝ ደላላዎችን ስታናግር ለእርሷ የሚሆን ሥራ ኮምቦልቻ እንዳለ ነገሯት፤ መስተንግዶ። አላመነታችም።
ያስፈልገኛል ያለችውን ብቻ ይዛ ወደ ኮምቦልቻ አመራች። ኮምቦልቻ ውስጥ በአንድ መለስተኛ ሆቴል መስተንግዶ መስራት ጀመረች።
ከሳምንት በኋላ ሐይቅ በህወሓት እጅ ወደቀች። የስልክ ግንኙነት በመቋረጡ የእናቷን ደኅንነት ማረጋገጥ ሳትችል ቀረች።
ፋቲማ እናቷ ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅ እንደጓጓች የህወሓት ወታደሮች ኮምቦልቻ ደረሱ።
በጥቅምት ወር መጨረሻ የህወሓት ተዋጊዎች ኮምቦልቻ እንደ ደረሱ ቀድመው ከገቡባቸው ሆቴሎች መካከል አንዱ ፋቲማ የምትሰራበት ሆቴል መሆኑን ታስታውሳለች።
በወቅቱ የጠየቋትን ምግብ ሰጥታቸው ከሆቴሉ ወጥተው ሄዱ።
ይህ ለፋቲማ እና ሌሎች ሦስት የሥራ አጋሮቿ 'እፎይ' የሚያሰኝ ነበር። ታጣቂዎቹ ትንኮሳም ሆነ ጾታዊ ጥቃት ስላላደረሱባቸው ደስታ ተሰምቷቸዋል።
ከእዚህም ባለፈ 'ምንም አያደርጉንም' የሚል ስሜት አድሮባቸው ሥራቸውን ተረጋግተው ሲሰሩ ዋሉ። ይህ ግን የሆነው ለአንድ ሌሊት ብቻ ነበር።
"በማግስቱ በሩን ዘጋግተን ከተኛን በኋላ ሌሊት ላይ በሩን ክፈቱ አሉን" በማለት በሕይወቴ የማልረሳው መጥፎ ጠባሳ ደርሶብኛል የምትለውን ዕለት አጀማመር ታስረዳለች።
ሆቴሉ ውስጥ ከሚሰሩት አራቱም ሴቶች አንዳቸውም አልጎደሉም። 'ብዙ መሆናችን ጥቃትን ለመከላከል ያመቻል' የሚል እምነት ነበራቸው።
ፋቲማ እና ጓደኞቿ 'በር አንከፍትም' በማለታቸው ቢጸኑም ወታደሮቹ በሩን በኃይል ሰብረውት ገቡ።
"እንደገቡ ለምንድን ነው ያልከፈታችሁት ብለው ሁላችንንም በጥፊ እና በርግጫ መቱን" ትላለች።
"ሁሉም መሳሪያ ይዘው ነበር" የምትለው ፋቲማ "የተወሰኑት ነጣ ያለ ዩኒፎርም ለብሰው ነበር፣ አሁን ተቀራራቢ የወታደር ልብስ ባየሁ ቁጥር እነሱ እየመሰሉኝ እደነግጣለሁ" ትላለች።
የሆቴሉን በር ገንጥለው የገቡት ወታደሮች ስምንት እንደነበሩ ታስታውሳለች።
ሁለቱ መሣሪያ ደግነው እርሷን ከጓደኞቿ ነጥለው እንደወሰዷት የምታስረዳው ፋቲማ፣ "ግደሉኝ እንጂ አልሄድም ስላቸው ሁለቱም በጥፊ እና በእርግጫ መትተው እየጎተቱ ወደ አልጋ ቤት ወሰዱኝ።"
"አልጋ ቤት ካስገቡኝ በኋላ እየተፈራረቁ እንደፈለጉት አደረጉኝ" በማለት የደረሰባትን ጥቃት ለቢቢሲ ተናግራለች።
ሌሎቹ ጓደኞቿ ምን እንደገጠማቸው በወቅቱ ፋቲማ የምታውቀው ነገር አልነበረም።
"ሌሊቱ እንደዚያን ዕለት ረዝሞብኝ አያውቅም" ያለችው ፋቲማ በማግስቱ ከጓደኞቿ ጋር ተገናኘች።
በደረሰባት መደፈር ብትጎዳም ሕመሟን ለጓደኞቿ አለማጋራት ግን አልፈለገችም። ፋቲማ የጓደኞቿን ሁኔታ ስላላወቀች የመደፈር ጥቃት የደረሰባት እርሷ ብቻ እንደሆነች ታስብ ነበር። የደረሰባትን ስታጋራቸው ግን፣ በእርሷ የደረሰው ጥቃት በእነርሱም ላይ መድረሱን ተረዳች።
የህወሓት ወታደሮች ኮምቦልቻን እንደተቆጣጠሩ መብራት እና የስልክ ኔትወርክ ተቋርጧል።
ከወዳጅ ዘመድ ጋር ለመደዋወል፣ በምሽት በመብራት ታግዞ ለመንቀሳቀስ የማይታሰቡ ነገሮች ናቸው።
ፋቲማ እና ጓደኞቿ በእዚህ ምክንያት በሰላሙ ቀን ሰርተው ለመለወጥ መስተንግዶ የጀመሩበትን እና ከአንድ ቀን በፊት ደግሞ መጥፎ ጠባሳ ያስተናገዱበትን ሆቴል ጥለው መሄድ አልፈለጉም፤ ቢፈልጉም መሄጃ የላቸውም። እዚያው ዋሉ።
ማታ የተገነጠለውን በር ጠጋግነው ለመተኛት ጥረት አደረጉ።
ሰባራው በር ዳግም ተንኳኳ። ተመሳሳይ ሰዎች ናቸው። እነፋቲማ "አንከፍትም" አሉ።
ወታደሮቹ ግን እንደተለመደው በሩን በርግደውት ገቡ።
እነፋቲማ የባለፈውን ሌሊት ሕመም በማንሳት ርህራሄ እንዲያደርጉላቸው ተማጸኑ። ተማጽኖው አልተሳካም።
እንዲያውም "ከትናንቱ የባሰ ገጠመኝ" ትላለች ፋቲማ።
በቀደመው ሌሊት ሁለት የነበሩት ወታደሮች አሁን አንድ ጓደኛቸውን ጨምረው ነው የመጡት።
ከዚህ በኋላ ግን እዚያ መቆየት የበለጠ አደጋ መጋበዝ መሆኑን ተረዱ። አቤት ይሉበት የሕግ አካል፣ ይሸሸጉበት ከለላ የላቸውም።
ስለዚህ ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመመለስ ወሰኑ።
ሌሎች ጓደኞቿ ወደ የአካባቢያቸው ሲሄዱ ፋቲማም ወደ ሐይቅ ጉዞ ጀመረች።
ከኮምቦልቻ - ደሴ ከእዚያም ሐይቅ ሁለት ቀን በእግር ተጉዛ ከእናቷ ቤት ደረሰች።
ቤት ውስጥ እናቷ፣ እህትና ወንድሞቿ የሉም። ሌላ የራስ ምታት። ጎረቤት ስትጠይቅ ወደ ገጠር ሸሽተው እንደሄዱ ተነገራት። አይታ ማመን ስለነበረባት እርሷም ወደ ገጠር ተጓዘች. . .


የትግራይ ኃይሎች ከወልድያ አልፈው ወደ ደሴ ሲገሰግሱ ዘምዘም በኮንስትራክሽን ሥራ ላይ ከተሰማራው የትዳር አጋሯ ጋር ከደሴ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቃ በምትገኝ አነስተኛ ከተማ ትኖር ነበር።
አማፂያኑ ወደ ከተማዋ በገቡበት ወቅት ባለቤቷ እና ልጇ ፊት በሁለት ወታደሮች መደብደቧን ታስታውሳለች።
ባለቤቷ እርሷን ለማስጣል ሲሞክር ደግሞ በጥይት ተመትቶ ተገደለ።
በደረሰባት ድብደባ ዘጠኝ ጥርሷ መርገፉን የምትናገረው ዘምዘም በእግሯ ላይም ከፍ ያለ ጉዳት ማስተናገዷን ትገልጻለች።
ዘምዘም በአማፂያኑ ወታደሮች መደፈሯን ለቢቢሲ ስታስረዳ "ወደ ቤት እንድገባ ጠየቁኝ። ገባሁ። በሩን ከኋላዬ ዘጉት። አንዱ ጥርሴን ሲመታኝ ወዲያውኑ ረገፈ። በድጋሚ በሌላኛው ጎኔ ደገመኝ፤ እርሱም ረገፈ። አፌ በደም ተሞላ። ሊደፍረኝ ሲሞክር ስታገለው ጩቤ አውጥቶ እጄን ወጋኝ። ከዚያም ልብሴን ቀዳደደ እና ደፈረኝ" ብላለች።
ዘምዘም የደረሰባትን ጾታዊ ጥቃት ማስታወስ ለበለጠ ሕመም እንደሚዳርጋት ትናገራለች።
ሰውነቷ በደም ተነክሮ፣ መንቀሳቀስ ተስኗት እንደነበር ገልጻ፣ ማልቀስ እንኳ እንዳልችል እንባዬ ደረቀ ትላለች።

"መደፈሬ ያመኛል፣ ከልጄ ፊት መሆኑ ደግሞ መቸም እንዳልረሳው ያደርገኛል" የምትለው ደግሞ ሜላት አበራ ናት።
እንደ ፋቲማ ሁሉ ሜላትም ከተመሳሳይ ከተማ ወደ ኮምቦልቻ የመጣች እና በሆቴል መስተንግዶ ሥራ የተሰማራች ነች።
ሁልጊዜም ከእግሯ ሥር የማትጠፋ ታዳጊ ልጅ አለቻት።
ከባለቤቷ ጋር ሲለያዩ "ልጄ ሊጎድልባት አይገባም" ብላ ከሰው ቤት ተቀጥራ ልጇን ማሳደግ መጀመሯን ትናገራለች።
ሜላት እና ፋቲማ የተለያየ ሆቴል ነው የሚሰሩት። ሜላት የምትሰራበት ቤት ተወካይ ነበረች።
የህወሓት ወታደሮች አንድ ቀን ሜላት ወደ ምትሰራበት ሆቴል አመሩ። ሆቴሉ ዝግ አልነበረም። ገብተው ቢራ መጠጣት ጀመሩ።
"ቢራ የለም ማለትም አንችልም፣ ምክንያቱም ይመቱናል" የምትለው ሜላት ቢራው ሲያልቅ ግን የፈራችውን ነገር ማምለጥ እንዳልቻለች ታስታውሳለች።
"ሁለቱ ወታደሮች 'ነይ አንቺ ከእኛ ጋር ትሄጃለሽ' አሉኝ" የምትለው ሜላት፣ "እምቢ ስላቸው አንደኛው መሣሪያውን አቀባብሎ 'እደፋሻለሁ' አለኝ" በማለት ሁኔታውን ትገልጻለች።
ከእዚያም "ለልጄ መኖር እንዳለብኝ ወስኜ የፈለጉትን አደረጉኝ" በማለት በህወሓት ታጣቂዎች የደረሰባትን ትናገራለች።
ሜላት እንደምትለው ይህ ጥቃት የተፈጸመባት ልጇ ከተኛችበት አልጋ ላይ ነው።
ልጇ ከእንቅልፏ የነቃችው የሚደርስባትን ድብደባ መቋቋም አቅቷት ስታለቅስ ነው።
"ለሁለት እየተፈራረቁ ሲያሰቃዩኝ አለቀስኩ፣ ያኔ ልጄ ተነሳች" የምትለው ሜላት አሁን አዕምሮዋን እረፍት ከሚነሷት ጉዳዮች አንዱ "ያኔ በቡድን ስደፈር ልጄ አይታኝ ይሆን?" የሚለው እንደሆነ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ባደረገችበት ወቅት ተናግራለች።
ግን ደግሞ "አይታ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ትጠይቀኝ ነበር" የሚለው ያጽናናታል።
ሜላት ምንም እንኳ ሆቴሉን በውክልና የምታስተዳድር ቢሆንም ተጨማሪ ሌሊት በእዚያ ሆቴል ማሳለፍ አልፈለገችም።
ልጇን ይዛ ወደ ጓደኛዋ ቤት አመራች። ጓደኛዋ ጋር ቤት ዘግተው መዋል ጀመሩ።
ለተወሰነ ጊዜ በዚያ ሰፈር የህወሓት ወታደሮች አይመጡም ነበር።
ከጊዜ በኋላ ግን መንደር ለመንደር መዘዋወር ጀመሩ።
"ቀን ሴት ያለበትን ቤት አጥንተው ማታ ይመጣሉ" የምትለው ሜላት፣ የደረሰባት ጥቃት እንዳይደገም በመስጋት ከጓደኛዋ ጋር መፍትሔ ያሉትን ሃሳብ ዘየዱ።
ቀን ቤት ዘግተው ከዋሉ በኋላ ማታ ላይ ከከተማው ወጣ ብሎ የሚገኝ ወዳጃቸው ጋር እየሄዱ ማደር ጀመሩ።
አንድ ወር ለሚጠጋ ጊዜ በእዚህ ሁኔታ ከቆዩ በኋላ የመከላከያ ሠራዊት ድጋሚ ኮምቦልቻን ተቆጣጠረ. . .

ዳያና እንደ እነ ሜላትና ፋቲማ ዓይነት ተጎጂዎችን የሥነ ልቦና ድጋፍ ለመስጠት በኮምቦልቻ ከተማ ከተመደቡ ክሊኒካል ሳይኮሎጂስቶች መካከል አንዷ ነች።
ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች ማከም ቀዳሚ ሥራዋ ነው።
እስካሁን በኮምቦልቻ ከተማ ብቻ 35 ሴቶች የመደፈር ጥቃት ተፈጽሞባቸው ማከማቸውን ነግራናለች።
በባሎቻቸው ፊት የተደፈሩ የአባውራ ሚስቶች፣ ህጻናት እና ታዳጊዎች ለሕክምና ከመጡት መካከል መሆናቸውን ዳያና ትናገራለች።
እርሷ የሥነ ልቦና ሕክምና ካደረገችላቸው ተጎጂዎች መካከል የ16 ዓመት ታዳጊ እንዳጋጠማት የነገረችን ዳያና፣ መገለልን በመፍራት ሪፖርት ያላደረጉ በርካቶች እንደሚኖሩ ታምናለች።
ፋቲማ ገጠር የሄዱትን ቤተሰቦቿን አግኝታ ከአንድ ወር በላይ አብራ አሳልፋለች።
አሁን ወደ ኮምቦልቻ ተመልሳ የቀድሞ አሰሪዎቿ ጋር ሥራ ጀምራለች። ሜላት አሁንም ከጓደኛዋ ጋር አብራ እየኖረች ነው።
ሜላት የደረሰባትን ለመርሳት ከኮምቦልቻ መልቀቅ ትፈልጋለች።
ነገር ግን ደግሞ "ልጄ ከለመደችው ቦታ ውጪ ብወስዳት ትታመምብኛለች" በማለት እዚሁ ለመኖር መወሰኗን ነግራናለች።
ፋቲማ እና ሜላት የሕክምና ድጋፍ ያገኙ ሲሆን ባደረጉት ምርመራም ከእርግዝና፣ ከኤችአይቪ እና ከአባላዘር በሽታዎች ነጻ መሆናቸውን አውቀዋል።
ድጋሚ ምርመራ ለማድረግ ሦስተኛ ወር እየጠበቁ ናቸው።
ቢቢሲ እነዚህን ሁኔታዎች በተመለከተ ለትግራይ ኃይሎች ጥያቄ ያቀረበ ቢሆንም ምላሽ አላገኘም።
ከዚህ ቀደም አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተሰኘው ሰብዓዊ መብት ተሟጋች በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት ጾታዊ ጥቃት እንደ መሳሪያ ማገልገሉን በመግለጽ ሪፖርት አውጥቶ ነበር።
ይኸው ድርጅት በታኅሣሥ ወር የህወሓት ተዋጊዎች በአማራ ክልል የአስገድዶ መድፈር ወንጀል መፈጸማቸውን በመጥቀስ በድጋሚ ሪፖርት አውጥቷል።
ህወሓት በበኩሉ ለሪፖርቶቹ በሰጠው ምላሽ የሠራዊቱ አባላት ሥነ ምግባር ያላቸው መሆናቸውን በመግለጽ ገለልተኛ መርማሪ አካል እንዲያጣራ ጠይቆ ነበር።
* መገለል እንዳይደርስባቸው በሚል የባለታሪኮቹ ስም ተቀይሯል።
















