ኮቪድ-19፡ የቻይናዋ የወደብ ከተማ በ48 ሰዓት ውስጥ 14 ሚሊየን ሰዎችን ልትመረምር ነው

በቲያንጂን በርካታ ሰዎች የኮቪድ ምርመራ ለማድረግ ረዣዥም ሰልፎች ታይተዋል።

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, በቲያንጂን በርካታ ሰዎች የኮቪድ ምርመራ ለማድረግ ረዣዥም ሰልፎች ታይተዋል

የቻይናዋ የወደብ ከተማ ቲያንጂን በ48 ሰዓታት ውስጥ ለ14 ሚሊየን ነዋሪዎቿ የኮቪድ-19 ምርመራ ልታደረግ መሆኑን አስታውቃ ክትባት እየሰጠች ነው።

ቲያንጂን ይህንን ለማድረግ ያቀደችው በከተማዋ በኮቪድ የተያዙ ሰዎች በመገኘታቸው ነው።

በዚህም መሠረት ነዋሪዎች እስከሚመረመሩ ድረስ በቤታቸው ውስጥ እንዲቆዩ የተነገራቸው ሲሆን፣ የሕዝብ መጓጓዣ ለመጠቀም የሚያስችላቸውን የጤና የይለፍ ወረቀት ለማግኘትም ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል ተብሏል።

በከተማዋ ውስጥ ቫይረሱ ከተገኘባቸው 20 ሰዎች መካከል ሁለቱ ግለሰቦች የተያዙት በፍጥነት በሚዛመተው የኦሚክሮን ዝርያ መሆኑም ተረጋግጧል።

ቻይና ወረርሽኙን ከማኅበረሰቡ ውስጥ ለማጥፋት ያለመ 'ዜሮ ኮቪድ' ፖሊሲ እየተከተለች ነው።

ከሌሎቹ የዓለም አገራት ጋር ሲነጻጸርም ቻይና ጥቂት ቁጥር ያላቸው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ብታገኝም፣ በስፋት ምርመራ በማካሄድ እና ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብ በመጣል ምላሽ ሰጥታለች።

በአገሪቷ በአውሮፓውያኑ የካቲት አንድ የሚከበረውና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚጓዙበት አዲስ ዓመት እንዲሁም ከጥቂት ቀናት በኋላ የሚጀመረው የክረምት ኦሊምፒክ በዜሮ ኮቪድ ፖሊሲዋ ላይ ጫና ይፈጥርበታል የሚል ስጋት አለ።

የክረምት ኦሊምፒክ አዘጋጅ ከተማዋ ቤይጂንግ ከወደብ ከተማዋ ቲያንጂን ከተማ የምትርቀው በ115 ኪሎ ሜትር ነው።

የኦሊምፒክ አዘጋጆች ቁጥጥር በተሞላበት ሁኔታ 'በዝግ' ጨዋታውን ለማካሄድ እየሰሩ ሲሆን፣ ተሳታፊዎች ከጨዋታ ስፍራዎች መውጣት የሚችሉት ለይቶ ማቆያ የሚገቡ አሊያም አገሪቷን ለቀው የሚወጡ ከሆነ ነው።

የቤይጂንግ ነዋሪዎችም የጨዋታው ተሳታፊዎችን ለማጓጓዝ የሚውሉ ተሽከርካሪዎችን ከመቅረብ እንዲቆጠቡ አዘጋጆቹ መምከራቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

በቲያንጂን በርካታ ሰዎች የኮቪድ ምርመራ ለማድረግ ረዣዥም ሰልፎች ታይተዋል።

በከተማዋ ለወረርሽኙ የተሰጠው አፋጣኝ ምላሽ በዢያን እና ዩዙሁ ከተሞች የተጣለውን ጥብቅ እርምጃዎች ያስቀራል ተብሏል። ሁለቱ ከተሞች የእንቅስቃሴ ገደብ ውስጥ ይገኛሉ።

ዢያን ከባለፈው ወር መጨረሻ ጀምሮ በእንቅስቃሴ ገደብ ውስጥ ስትሆን ነዋሪዎቿ በቤታቸው ውስጥ እንዲቆዩ ታዘዋል። በከተማዋ አስፈላጊ የሆኑ እቃዎችን ለመግዛት መውጣትም ተከልክሏል።

በዚህም ምክንያት ነዋሪዎች ምግብ እያለቀባቸው እንደሆነና አንዳንዶቹም ንብረቶቻቸውን በምግብ ለመቀየር እየተገደዱ መሆኑን በምሬት እየገለፁ ነው።