ኮቪድ-19፡ ኮቪድ የተገኘበት ልጇን በመኪና ኮፈን ውስጥ የቆለፈችው የቴክሳስ መምህርት ታሰረች

በመንገድ ላይ የኮቪድ ምርመራ ሲደረግ የሚያሳይ ምሥል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በመንገድ ላይ የኮቪድ ምርመራ ሲደረግ የሚያሳይ ምሥል

አንዲት አሜሪካዊት መምህርት ራሷን ከቫይረሱ ለመጠበቅ ስትል ኮሮናቫይረስ የተገኘበት ልጇን መኪናዋ እቃ መጫኛ ውስጥ ቆልፋበታለች በሚል በቁጥጥር ሥር መዋሏን ተዘገበ።

ሳራህ ቤም የተባለችው የ41 ዓመቷ መምህርት ልጇን ለአደጋ በማጋለጥ ክስ ቀርቦባታል።

እንደ ክሊክቱሆስተን ድረ ገጽ ከሆነ ሳራህ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋለችው ባለፈው ሰኞ በቴክሳስ፣ ሃሪስ ካውንቲ ውስጥ ከግለሰቧ መኪና የኋላ እቃ መጫኛ ክፍል ውስጥ አንድ ግለሰብ ድምጽ ሰምቶ ለፖሊስ በመደወሉ ነበር።

መምህርቷ ሳራህ ቤም የ13 ዓመቱ ልጇ ኮቪድ-19 እንደተገኘበትና ውጤቱን ለማረጋገጥ ለሌላ ምርመራ ወደ ፕሪጂን ስታዲየም አካባቢ እየሄደች እንደነበር መግልጿን መገናኛ ብዙኃኑ ዘግቧል።

ልጇን በመኪናው እቃ መጫኛ ውስጥ እንዲተኛ ያደረገችውም በቫይረሱ እንዳትያዝ ራሷን ለመጠበቅ እንደነበር አስረድታለች።

የኤቢሲ ተባባሪ የሆነው ኬቲአርኬ ቲቪ እንደዘገበው አንድ የጤና ባለሙያ ልጁ የኋላ መቀመጫ ላይ እንዲቀመጥ እስካልተፈቀደለት ድረስ ምንም ዓይነት የኮሮናቫይረስ ምርመራ እንደማይደረግለት ነግረዋታል።

ሳራህ እአአ ከ2011 ጀምሮ ሳይፕረስ ፎልስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመምህርነት ስትሰራ የቆየች ሲሆን አሁን ላይ ፈቃድ ላይ መሆኗን መገናኛ ብዙኃኑ ዘግቧል።

ሳይ ፌር አይኤስዲ ፖሊስ መሥሪያ ቤት "ፖሊስ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ከኮቪድ የምርመራ ጣቢያ የተነሳ መኪና የእቃ መጫኛ ክፍል ውስጥ ህጻን ልጅ እንዳለ ተነግሮታል" ብሏል።

በዚህም መሠረት የሕግ አስከባሪ አካላት ሙሉ ምርመራ በማካሄድ መምህርቷን በቁጥጥር ሥር ለመዋል የእስር ማዘዣ እንደተሰጣቸው ፖሊስ ገልጿል።

ፖሊስ እንዳለው በህጻኑ ላይ የደረሰ ጉዳት የለም።

የቴክሳስ የሕዝብ ደኅንነት ባልደረባ ሪቻርድ ስታንዲፈር በበኩላቸው ተሽከርካሪው ግጭት ቢያጋጥመው ኖሮ ግን ልጁ በጣም ሊጎዳ ይችል ነበር ብለዋል።

ሪቻርድ አክለውም "አንድ ሰው ምንም ዓይነት ቫይረስ ስለተገኘበት በመኪና እቃ መጫኛ ክፍል ውስጥ ሲቆለፍበት ሰምቼም፤ አይቼም አላውቅም " ብለዋል።