ኮሮናቫይረስ፡ በአሜሪካ የ17 ዓመቱን ተማሪ የከተበችው የሳይንስ መምህር በቁጥጥር ሥር ዋለች

ላውራ ሩሶ የተባለችው መምህርት

የፎቶው ባለመብት, CBS

በአሜሪካ ኒው ዮርክ ግዛት የሚገኝ ትምህርት ቤት መምህርት ምንም ዓይነት የሕክምና እውቀት ሳይኖራት ለተማሪዋ የኮቪድ-19 ክትባት ሰጥታለች በሚል በቁጥጥር ሥር ዋለች።

ፖሊስ እንዳለው ላውራ ሩሶ የተባለችው መምህርት ክትባቱን ለመስጠት ምንም ዓይት ሕጋዊም ሆነ ከተማሪው ወላጆች ፈቃድ ባይኖራትም ቤቷ ውስጥ ክትባቱን ሰጥተዋለች ተብሏል።

የሥነ ሕይወት ትምህርት መምህርት የሆነችው የ54 ዓመቷ መምህርት ሩሶ በአዲሱ የፈረንጆች ዓመት ዋዜማ ላይ በቁጥጥር ሥር የዋለች ሲሆን፤ እስከ አራት ዓመት እስር ሊጠብቃት ይችላል።

በእርግጥ የ17 ዓመቱ ተማሪም ክትባቱን መውሰድ ፈልጎ እንደነበር ተዘግቧል።

ባለሙያዎች እንደሚሉት ክትባት በተገቢው መንገድ ካልተሰጠ አደገኛ ነው። ሐኪሞችና ፈቃድ ያላቸው የሕክምና ባለሙያዎች ክትባት ከመስጠታቸው በፊት ሐሰተኛ አሊያም ጊዜው ያለፈበት አለመሆኑን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል።

ክትባቱን የሚወስደው ሰውም ስለጤንነቱ ሁኔታና የጤንነት ታሪኩ መጠየቅ አለበት። ከዚህም ባሻገር ክትባቱን ከወሰዱ በኋላም ያሳየው የጤንነት ሁኔታን ወይም የክትባቱን ምላሽ መከታተል የግድ ይላል።

ፖሊስ መምህርት ሩሶ ለተማሪዋ የሰጠችው ክትባትን እንዴት ልታገኘው እንደቻለችና የትኛው ክትባት እንደሆነ ግልጽ አይደለም ብሏል።

አሁን ላይ ከ18 ዓመት በታች ለሆኑ ልጆች ክትባት ለመስጠት በአሜሪካ ፈቃድ ያገኘው የፋይዘር ባዮንቴክ ክትባት ነው።

ከአሜሪካዋ ግዛት ኒው ዮርክ ደቡብ ምሥራቅ ላይ በምትገኘው ሎንግ ደሴት የተከሰተውን ይህንን አጋጣሚ የሚያሳየው ቪዲዮ መምህርት ሩሶ ተማሪዋን "ደህና እንደምትሆን ተስፋ አደርጋለሁ" ስትለው ያሳያል።

እርሱም በምላሹ "የቤት ውስጥ ክትባት . . . ይኸው!" ሲል ተደምጧል።

ተማሪው ወደ ቤቱ ተመልሶ መምህሩ ክትባቱን እንደሰጠችው ለወላጆቹ ከነገራቸው በኋላ ወደ ናሶ ፖሊስ በመደወል ሪፖርት አድርገዋል።

የናሶ ፖሊስ ኮሚሽነር ፓትሪክ ራይደር መምህርቷ "ክትባቱን አግኝታዋለች። እንዴት እንዳገኘችው እየተጣራ ነው" ብለዋል።

መምህርት ሩሶ የምትሰራበት ሄሪክስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በሰጠው መግለጫ መምህርቷ ከሥራዋ መታገዷን ገልጾ፣ የምርመራ ውጤቱን በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች ማለቱን በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ዘግቧል።

መምህርቷ ባለተፈቀደ የሙያ ተግባር ክስ የቀረበባት ሲሆን በአውሮፓውያኑ ጥር ወር መጨረሻ አካባቢ ፍርድ ቤት እንድትቀርብ ቀጠሮ ተይዟል።