በአሜሪካ በአንድ ቀን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በኮቪድ መያዛቸው ተመዘገበ

የምትመረመር ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአሜሪካ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በኮቪድ መያዛቸው ተገለጸ። የአገሪቱ ባለሥልጣናት በፍጥነት እየተሰራጨ ያለው የኦሚክሮን ዝርያ የሥርጭቱ ጣሪያ ላይ አልደረሰም ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ሰኞ ዕለት 1,080,211 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ ይህም ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዝግቧል። እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ከሆነ ቁጥሩ በዓለም ላይ ከፍተኛው በአንድ ቀን ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች የተመዘገበበት ሆኗል።

ኦሚክሮን በአሜሪካ በስፋት እየተሰራጨ የሚገኘው የኮሮናቫይረስ ዝርያ ነው።

ለወረርሽኙ በሰጡት ምላሽ ትችት እየገጠማቸው የሚገኙት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ትምህርት ቤቶች ክፍት ሆነው እንዲቆዩ ጥሪ አቅርበዋል።

በቅርብ ሳምንታት በቫይረሱ ምከንያት በአሜሪካ የሞት እና ሆስፒታል የመግባት መጠን ከቀደሙት ጊዜያት አንጻር በጣም አነስተኛ ሆኗል። ሆስፒታል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው ተብሏል።

የአገሪቱ ከፍተኛ ወረርሽኝ አማካሪ የሆኑት አንቶኒ ፋውቺ የቫይረሱ ሥርጭት "ቀጥ ያለ ጭማሪ" እያሳየ ነው ብለዋል። ሥርጭቱ ጣራ ላይ ለመድረስ ምናልባትም ሳምንታት ሊቀሩ ይችላሉ ብለዋል።

ባይደን ማክሰኞ ዕለት እየጨመረ በመጣው ቫይረስ "አሳሳቢ እና ትልቅ ግራ መጋባት ፈጥሯል" ብለዋል። በአብዛኛው ሆስፒታል የሚገቡት እና በኮቪድ የሚሞቱት ሰዎች ያልተከተቡ መሆናቸውን አስታውቀው፤ ዩናይትድ ስቴትስ መስፈርቱን የሚያሟሉትን ሙሉ ለሙሉ ለመከተብ የሚያስችል በቂ ክትባቶች እንዳሏት በድጋሚ ተናግረዋል።

"ልጆች በትምህርት ቤት ደህንነታቸው የተጠበቀ ሊሆን እንደሚችል እናውቃለን። ለዚህም ነው ትምህርት ቤቶች ክፍት ሆነው መቆየት አለባቸው ብዬ የማምነው" ብለዋል።

በከፍተኛ ሥርጭት ወቅት ትምህርት ቤቶች መዝጋት

በኦሚክሮን በፍጥነት መሰራጨት እና በሰው ኃይል እጥረት ምክንያት የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ከገና እረፍት መልስ ተማሪዎችን የሚቀበሉበትን ጊዜ እንዲያራዝሙ አድርጓቸዋል። ለተማሪዎች እና ለመምህራን ፈጣን ምርመራ በማድረግ ላይም ስጋቶች አሉ።

ዲትሮይት ሚቺጋን ለምሳሌ ብንወስድ የሥርጭት መጠኑ የምንጊዜውም ከፍተኛ ሆኖ 36 በመቶ በመድረሱ የከተማው ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች እስከ ሐሙስ ድረስ ትምህርት ቤቶች ዝግ ሆነው እንደሚቆዩ አስታውቀዋል።

አትላንታ፣ ሚልዋኪ፣ ክሊቭላንድ እና ኒው ዮርክን ጨምሮ ሌሎች ዋና ዋና ግዛቶች ትምህርት የሚጀመርበትን ጊዜ አዘግይተዋል ወይንም ወደ በይነ መረብ ትምህርት መመለሳቸውን አስታውቀዋል።

በአሜሪካ ትልቁ የትምህርት ግዛት በሆነው ኒው ዮርክ ትምህርት ቤቶች ክፍት ሆነው እየሠሩ ነው። የከተማዋ ከንቲባ ኤሪክ አዳምስ ትምህርት ቤት "ለልጆቻችን ደህነታቸው የሚጠበቅበት ቦታ" ነው ብለዋል።

ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው ከሆነ ግን ሲሶ የሚሆኑት ወላጆች በኮቪድ-19 ፍራቻ ልጆቻቸውን በቤታቸው ማቆየትን መርጠዋል።

ዘ ታይምስ ደግሞ በመላ አገሪቱ ከ450,000 የሚበልጡ ተማሪዎች ባለፈው ሳምንት በጊዜያዊነት ወደ ርቀት ትምህርት መመለሳቸውን ዘግቧል።

የሆስፒታል የመሚገቡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው

ሥልጣኑን ሲረከቡ "ቫይረሱን ለመግታት" ቃል የገቡት ባይደን በቫይረሱ ከፍተኛ ሥርጭት ምክንያት ትችት አይሎባቸዋል። ክትባትን፣ የጭንብል አጠቃቀምን እና አካለዊ ርቀት እርምጃዎችን በማበረታታት የክልል አስተዳዳሪዎች ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ በቅርቡ ኃላፊነታቸውን ወደ ሌላ የማዞር የሚመስል አስተያየት ሰጥተዋል።

ማክሰኞ ባደረጉት ንግግር ደግሞ የኮቪድ ህመምን ለማከም የሚውለውን የፋይዘር ክኒኖች ለመግዛት አሜሪካ ያቀረበቸውን ጥያቄ በእጥፍ በማሳደግ 20 ሚሊዮን መታዘዙን አስታውቀዋል።

ክኒኖቹን ለማምረት ወራትን ስለሚወስድ አሜሪካ ተጨማሪ የጠየቀችውን ትዕዛዝ ቢያንስ እስከ ስድስት ወር ድረስ አታገኝም ሲሉ በዱክ ዩኒቨርሲቲ የጤና ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ክሪሽና ኡዳያኩማር አስጠንቅቀዋል።

"ምርመራ ላይ ልናተኩር ይገባል። በቂ እና ወቅቱን የጠበቀ ምርመራ እንደማናደርግ እናውቃለን" ሲሉ አዎንታዊ ውጤትን ለማግኘት ህክምና ቀደም ብሎ መጀመር እንዳለበት ዶ/ር ኡዳያኩማር ለቢቢሲ ወርልድ ኒውስ አሜሪካ ተናግረዋል።

"እንደ ክትባቶች፣ መመርመሪያዎች እና ህክምናዎች ያሉ አንዳንድ ቴክኒካል መሳሪያዎች ቢኖሩንም ሁሉንም በየቦታው ለማስቀመጥ የሚያስችል ጠንካራ ሥርዓት አልገነባንም" ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዶ/ር ፋውቺ ሰኞ ዕለት ለኤቢሲ እንደተናገሩት ካልተከተቡት በአስር ሚሊዮን የሚቆጠሩ አሜሪካውያን "የተወሰኑት" ከባድ በሽታ አጋጥሟቸዋል።

እንደ ጆን ሆፕኪንስ ዘገባ ከሆነ ባለፈው ሳምንት 8,652 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ህይወታቸው አልፏል።

ቀደም ሲል የነበረው በአሜሪካ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ዕለታዊ ቁጥር 590,000 ነበር።

ከአሜሪካ ውጭ ከፍተኛው ቁጥር የተመዘገበው በግንቦት 2021 ሲሆን ከ 414,188 በላይ ሰዎች በህንድ የዴልታ ስርጭት በቫይረሱ በተያዙበት ወቅት ነው።

ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ኦሚክሮን ቀደም ሲል ከነበረው የዴልታ ዝርያ አንጻር መለስተኛ ህመም ቢኖረውም በከፍተኛ ደረጃ ተላላፊ በመሆኑ ሆስፒታሎች ላይ ጫና ሊያሳድር ይችላል የሚል ስጋት አለ።