በእንግሊዝ ተማሪዎች ቢያንስ አንድ ጊዜ እንዲከተቡ እና ጭንብል እንዲለብሱ ሊደረግ ነው

ማስክ ያደረጉ ተማሪዎች

የፎቶው ባለመብት, PA Media

እንግሊዝ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ከመመለሳቸው በፊት ቢያንስ አንድ ጊዜ የኮቪድ-19 ምርመራ እንደሚያደርጉ መንግሥት አስታወቀ።

ለትምህርት ቤቶች የምርመራ ቁሳቁሶች እንደ አስፈላጊነቱ እንደሚቀርቡ ባለሥልጣናት አረጋግጠው፣ ተማሪዎች በሳምንቱ ሁለት ጊዜ እንዲመረመሩ አሳስበዋል።

ከኮቪድ ጋር በተያያዘ በተገኘ መረጃ መሠረት ምንም አዲስ ገደቦች እንደማያስፈልጉ መንግሥት እሁድ ዕለት አጽንኦት ሰጥቶ ገልጿል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ናዲሂም ዛሃዊ እስከ ጥር 26 ድረስ በትምህርት ቤቶች የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል መልበስ ያስፈልጋል ብለዋል።

የኦሚክሮን ስርጭትን ለመቀነስ ነው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ክፍል ውስጥ እንዲለበስ የተወሰነው።

ጭንብሎቹን እንዲለበሱ በጊዜያዊነት የታሰበው በትምህርት ቤቶች ያለውን ስጋት ለመቅረፍ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ስድስት የትምህርት ቤት ሠራተኞች ማኅበራት የቫይረሱን ስርጭት ለመገደብ አስቸኳይ እርምጃዎች ይወሰዱ ሲሉ ጠይቀዋል።

ተጨማሪ እርምጃዎች ካልተወሰዱ ብሔራዊ ፈተናዎች ለአደጋ ሊጋለጡ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።

በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ያሉ ትምህርት ቤቶች ከገና እረፍት በኋላ በሚቀጥለው ሳምንት ይከፈታሉ። ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤታቸው ሲመለሱ የኮቪድ-19 ምርመራ እንዲያደርጉ ይጠየቃሉ።

ከአራቱ የዩኬ ግዛቶች ተማሪዎች ክፍል ውስጥ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንዲለብሱ ከማይመከርባት ብቸኛዋ እንግሊዝ ነበረች። በአዲሱ መመሪያ መሰረት መምህራን ጭንብል እንዲለብሱ አይጠበቅባቸውም።

በእንግሊዝ ያሉ አንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች እና የተለያዩ ግዛት ባለሥልጣናት በክፍል ውስጥ ጭንብል እንዲለበስ ጠይቀው ነበር።

ባለፈው ዓመት ከመጋቢት ጀምሮ ለሁለት ወራት ያክል የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ በእንግሊዝ ትምህርት ቤቶች እንዲለበስ ተደርጎ ነበር።

'ቀዳሚ ጉዳይ'

የትምህርት ሚኒስትር ናዲም ዛሃዊ እንዳሉት ጭምብሉ እስከ ጥር 26 ድረስ ይተገበራል ብለዋል።

ጥር 26 እየተተገበረ የሚገኘው ብሔራዊ የኮቪድ-19 እርምጃዎች ሁለተኛ እቅድ የሚጠናቀቅበት ነው።

ለእርሳቸው እና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ትምህርት "አንደኛና ቅድሚያ የሚሰጠው" መሆኑን ገልጸው ትምህርት እንዳይስተጓጎል "እኛ የቻልነውን ሁሉ" እናደርጋለን ብለዋል።

መንግሥት 7,000 የአየር ማጽጃ መሳሪያዎችን ለትምህርት ቤቶች እና ኮሌጆች ተደራሽ የሚያደርግ መሆኑን ገልጿል።

በእንግሊዝ ከ24,400 በላይ ትምህርት ቤቶች እንዳሉ የቅርብ ጊዜ የመንግሥት አሃዛዊ መረጃዎች ያመለክታሉ። የትምህርት ሚኒስቴር እንዳለው ከሆነ መሳሪያዎቹ በሮች እና መስኮቶችን ለመከፈት አስቸጋሪ ለሆኑባቸው አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ብቻ የሚሰጡ ናቸው።

የሠራተኞች መቅረት

በኦሚክሮን ፈጣን ስርጭት ምክንያት ሠራተኞች በመቅረታቸው እና ኮቪድ መስፋፋቱ ባለፈው ዓመት መገባደጃ ላይ በትምህርት ላይ ተጨማሪ መስተጓጎልን እንዳይኖር የሚል ስጋት አስከትሏል።

በትምህርት ዘርፍ ላይ የተሰማሪ ዋና ዋና ማኅበራት ትምህርት ቤቶችን ለመርዳት አስቸኳይ እርምጃዎች እንደዲወሰዱ የሚጠይቅ የጋራ መግለጫ አውጥተዋል።

ትምህርት ቤቶች ለሦስተኛ ተከታታይ ዓመት የፈተና መስተጓጎልን እንዲያስወግዱ ጠይቀዋል። በተማሪዎች እና በመምህራን ላይ የሚደርሰውን አለመተማመን እና ተጨማሪ የሥራ ጫና ማስወገድ አለባቸው ብለለዋል።

የካቢኔ ጽህፈት ቤቱ ሚኒስትር ስቲቭ ባርክሌይ እንደተናገሩት ትምህርት ቤቶች በታቀደው ጊዜ መከፈታቸውን ለማረጋገጥ ምርመራ እንዲያደርጉ ቅድሚያ ይሰጣቸዋል።

ሚኒስትሮች የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል "ብዙ ልጆች ሊለብሱት የማይፈልጉት ነገር" እንደሆነ ይገነዘባሉ ያሉ ሲሆን ይህ የተደረገው ትምህርትን ገጽ ለገጽ መሰጠቱን ለማረጋገጥ ነው ብለዋል።

የሌበር ፓርቲው ዌስ ስትሪትንግ በበኩላቸው በትምህርት ቤቶች ጭምብሎች መለበሱል ማንም "ለመፈንደቅ" ብሎ ባያደርገውም ልጆች ትምህርት ከሚያጡ ይሻላል በሚል መሆኑን ገልጸዋል።

ስትሪትዲንግ ለምርመራ የሚያስፈለጉ ግብዓቶች እጥረት እየተፈጠረ መሆኑን ገልጸው መንግሥት ምርመራ ላይ "እንዲበረታ" ጠይቀዋል።

የኮንሰርቫቲቭ ፓርቲው የፓርላማ ተወካይ እና የትምህርት ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ሮበርት ሃልፎን በጭንብል ፖሊሲው ላይ ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል።

የሕጻናት ሚኒስትሩ ለኮሚቴያቸው "ጭንብል የመልበስ ውጤታማነት ላይ ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም" ማለታቸውን ሃልፎን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ከፖሊሲው ጀርባ ያሉትን ማስረጃዎች እና ይህም በልጆች አዕምሮአዊ ጤንነት፣ ደኅንነት፣ ጭንቀት እና ትምህርት ላይ ያለውን ተጽእኖ ለመገምገም መንግሥት ምን እየሠራ እንደሆነ እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል።

36,000 ህጻናትን የሚያስተምረውን የሃሪስ ፌዴሬሽንን የሚመሩት ሰር ዳንኤል ሞይኒሃን በበኩላቸው ከሃልፎን ጋር በጭንብል ዙሪያ እንደማይስማሙ ተናግረዋል። በጉዳዩ ላይ ትምህርት ቤቶቻቸው ከሚገኙ የተማሪዎች ኮሚቴ ጋር ሊወያዩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

"በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ አንድ ሺህ ልጆች ካሉን እና ሲተነፍሱ አንዳቸው ለሌላቸው በማስተላለፍ እነሱም ሆነ ሠራተኞቻቸው ሊታመሙ ከመቻላቸው ባለፈ በአእምሯዊ ጤንነታቸውም ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል" ብለዋል።

በዎርዚንግ በሚገኘው በሎሬልስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ረዳት ርዕሰ መምህር የሆኑት ቤዝ ኮሊንስ "የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በድጋሚ እንደተረሱ" ይሰማቸዋል። የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች ያልተከተቡ በመሆናቸው "ለሁሉም ዓይነት አደጋዎች ክፍት አድርጎናል" ብለዋል።

የአየር ማናፈሻ ማሰሪያዎች

ትምህርት ቤቶች አዲሱን የአየር ማጽጃ መሳሪያ ማግኘት ስለሚችሉበት ሂደት የትምህርት ቢሮው በቅርቡ መመሪያ ያወጣል።

ስትሪትንግ እንደተናገሩት የመንግሥት ውሳኔ በበቂ ሁኔታ አልተተገበረም። በእንግሊዝ ከሚገኙት አራት ትምህርት ቤቶች ውስጥ አንዱ እንዲያገኝ 7,000 የሚሆኑት በቂ መሆናቸውን ጠቅሰው "ትምህርት ከመጀመሩ በፊት በጣም የሚጨናነቅ ይመስላል" ብለዋል።

በምሥራቅ ሰሴክስ የምትኖረው የፒያኖ እና የድምጽ መምህርት የሆነችው ሜጋን ስኪነር ከስድስት ዓመት በፊት በሳምባዋ ላይ በተፈጠረው የደም መርጋት ልትሞት ተቃረባ ነበር።

ሐኪሟ በኮቪድ ከተያዘች የሳምባ ህመሙ በድጋሚ ሊያገረሽ እንደሚችል ስለነገራት "ወደ ትምህርት ቤት ስለመመለስ ሳስብ በጣም ፍርሃት አለብኝ" ስትል ገልጻለች።

ለአንዳንድ ክፍሎቿ በቂ አየር ማናፈሻ አለመኖሩ እንዳስጨነቃት ተናግራለች። "ብዙ መምህራን ከሚያገኙት የተማሪዎች ቁጥር አምስት እጥፍ ይደርሰኛኛል። ይህም እና በእኔ ላይ ካለው በኮሮናቫይረስ የመያዝ ስጋት በተጨማሪ ብዙ ተማሪዎች ላይ የማስተላለፍ ዕድልም ሊኖረኝ ይችላል" ብላለች።