አንድ የደቡብ ኮሪያ ዜጋ ባልተመደ ሁኔታ ወደ ሰሜን ኮሪያ መክዳቱ ተዘገበ

የደቡብ ኮሪያ ወታደሮች ግሰቡን ለማግኘት ፍለጋ ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የደቡብ ኮሪያ ወታደሮች ግሰቡን ለማግኘት ፍለጋ ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም

አንድ የደቡብ ኮሪያ ዜጋ ባልተመደ ሁኔታ በጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበትን ወታደራዊ ቀጠና አልፎ ወደ ጎረቤት ሰሜን ኮሪያ ግዛት ከድቶ መግባቱ ተነገረ።

ብዙውን ጊዜ ከሰሜን ኮሪያ ወደ ደቡብ ኮሪያ ከድተው የሚገቡ ዜጎች ይኖራሉ እንጂ በተቃራኒው የመሆን አጋጣሚ እምብዛም ነበር።

ይህ ስሙ ያልተገለጸ ደቡብ ኮሪያዊው ዜጋ ግን እጅግ ጥብቅ የሆነውንና ከወታደራዊ ቀጠና ነጻ ተብሎ የሚታወቀውን የፈንጂ ወረዳ ድንበር ማቋረጡን የደቡብ ኮሪያ ባለሥልጣናት አረጋግጠዋል።

ግለሰቡን ለመያዝ ለሰዓታት በድንበር አካባቢ ከፍተኛ አሰሳ ተደርጎ ቢፈለግም ባልተጠበቀ መልኩ ሾልኮ ወደ ሰሜን ኮሪያ መግባቱ ተነግሯል።

አንድ የደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ባለሥልጣን እንደተናገሩት ዜጋቸው በእርግጥ አሁን በሕይወት ይኑር ወይም ይገደል እርግጠኛ እንዳለሆኑ፣ ነገር ግን ለሰሜን ኮሪያ ባላንጣዎቻቸው ስለ ጉዳዩ እንዳሳወቁ አብራርተዋል።

ሰሜን ኮሪያ በተለይ ኮቪድ-19ን ተከትሎ በድንበር ሊከዱ ያሰበ ማንኛውንም ሰው በጥይት ተኩሶ የመግደል ፖሊሲን ትከተላለች።

መግደል ብቻም ሳይሆን ሬሳቸውን ታቃጥላለች።

ይህ ግለሰብ ለመጨረሻ ጊዜ ከታደራዊ ቀጠና ነጻ ወረዳ (DMZ) ውስጥ የታየው ቅዳሜ ዕለት በምሥራቅ ድንበር በአገሬው አቆጣጠር ምሽት 3፡20 ላይ ነበር።

ከዚያ በኋላ ግን ከፍተኛ አሰሳ በአካባቢው ቢደረግም ደቡብ ኮሪያዊው እምጥ ይግባ ስምጥ ሊገኝ አልቻለም።

በመስከረም 2020 እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች አንድን ድንበር ላይ ያገኙትን ደቡብ ኮሪያዊ ዓሣ አጥማጅ ወዲያውኑ ተኩሰው ገድለውት ነበር።

ተኩሶ መግደላቸው ሳይበቃ ግለሰቡን ከገደሉት በኋላም አስከሬኑ ላይ ቤንዚል አርከፍክፈው አቃጥለውት ነበር።

በወቅቱ ይህ ክስተት በደቡብ ኮሪያዊያን ዘንድ ብስጭትን ፈጥሮ ነበር።

ነገር ግን ፒዮንግያንግ ዜጋችሁን ወዲያው እንዲገደልና ሬሳውም እንዲቃጠል የወሰንኩት ኮሮናቫይረስ ሊኖርበት ይችላል ብዬ ነው ብላ ባላንጣዋን ደቡብ ኮሪያን ይቅርታ ጠይቃ ነበር።

ሰሜን ኮሪያ በርካታ ዜጎቿ ድንበር እያቋረጡ ለደቡብ ኮሪያ እጅ ስለሚሰጡ በድንበር የሚሾልኩ ሰዎችን ለመግደል ሁለት ጊዜ አስባ አታውቅም።

የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ ማወጃቸው አይዘነጋም።

ይህን ያደረጉትም አንድ ደቡብ ኮሪያዊ ወደ ሰሜን ኮሪያ ቫይረስ ይዞ ዘልቆ ገብቷል በማለት ነበር።

በደቡብና ሰሜን ኮሪያ ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ ቀጠና የሚባለው አካባቢ በዓለም ላይ በከባድ ሁኔታ የሚጠበቅ አስፈሪ ሥፍራ ሲሆን መሬቱ በተቀበሩ ፈንጂዎች ከመሞላቱም በላይ አካባቢው በሞላ በአደገኛ የኤሌክትሪክ አጥር የተከለለ ሆኖ 24 ሰዓት በካሜራ የሚጠበቅ ነው።