ቻይና 'ወንጀለኞችን' በማሸማቀቅ በሕዝብ ፊት መቀጣጫ የምታደርግበትን ሥርዓት መለሰች

የተጠረጠሩት አራቱ ግለሰቦች

የፎቶው ባለመብት, Zhengguan video

ከወደ ደቡባዊ ቻይና ፖሊስ ጥፋት ፈጽመዋል ያላቸውን አራት ተጠርጣሪዎችን በሕዝብ መሀል ጥፋታቸው እየተነገረ እንዲሄዱ ሲያደርግ የሚያሳይ ምስል ወጥቷል።

አራቱ ወንዶች ሰዎችን ከቻይና ድንበሮች በኩል በሕገወጥ መንገድ በማዘዋወር የተከሰሱ ሲሆን ድንበሮች ደግሞ በአብዛኛው መልኩ በኮቪድ-19 ስርጭት ምክንያት ተዘግተዋል።

ሰዎቹ በደቡባዊ ቻይና ጊያንግዢ ግዛት ጂንግዢ ከተማ ውስጥ በሚገኙ ጎዳናዎች እንዲዘዋወሩ ተደርገዋል። ይህን ተከትሎም በማኅበራዊ ሚዲያና በመንግሥት በሚተዳደሩ መገናኛ ብዙኃንን ጨምሮ የተለያዩ ሐሳቦች እየተሰነዘሩ ነው።

ሁኔታውን የተከታተሉ ሰዎች ምስልና ተንቀሳቃሽ ምስል በመውሰድ በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ ሲሆን አራቱ ሰዎች በፖሊስ ታጅበው በከተማዋ ጎዳናዎች ሲመላለሱ ያሳያል። ይህ የሆነው ከሁለት ቀናት በፊት መሆኑም ተገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪም ግለሰቦቹ ፊታቸው የተሸፈነ ሲሆን፣ ነገር ግን ስማቸውና ምስላቸው ያለበት ወረቀት እላያቸው ላይ ተለጥፎ ነው እንዲዘዋወሩ የተደረጉት።

የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የሆነው 'ጊያንግዢ ዴይሊ' እንደዘገበው ሰዎቹ ከድንበር ጋር የተያያዙ ጥሰቶችን የፈጸሙ ሲሆን በተጨማሪነት ደግሞ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመቆታጠር የተቀመጡ መመሪያዎችንም ጥሰዋል።

የዜና ወኪሉ አክሎም በድንበር አካባቢ ያለው የኮሮናቫይረስ ስርጭት በጣም አሳሳቢና የተወሳሰበ እንደሆነ ዘግቧል።

ለመጀመሪያ ጊዜ የኮሮናቫይረስ የተገኘባት ቻይና እስካሁን በአጠቃላይ 114 ሺህ 365 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ያስታወቀች ሲሆን፣ 4 ሺህ 849 ሰዎች ደግሞ በዚሁ ቫይረስ ሳቢያ ሕይወታቸው ማለፉን ገልጻለች። ከትናንት በስቲያ ደግሞ ተጨማሪ 203 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተዘግቧል።

ቻይና በአሁኑ ወቅት ጠበቅ ያለና ኮቪድ ስርጭትን ዜሮ ለማድረግ የሚያግዝ መመሪያ አውጥታ በመስራት ላይ ትገኛለች። በዚህም በርካታ ሰዎችን በአንድ ጊዜ በመመርመር፣ በመከተብና እንቅቃሴ ገደቦችን ተግባራዊ በማድረግ ስርጭቱን ለመቆጣጠር እየጣረች ትገኛለች።

እስካሁንም ቻይና 85 በመቶ የሚሆነውን ሕዝቧን ሙሉ በሙሉ ከትባለች።

አራቱ ሰዎች በጎዳናዎች ላይ ከነስማቸውና ምስላቸው እንዲመላለሱ ከተደረጉ በኋላ የቻይና ማኅበራዊ ሚዲያ የሆነው ዌቦ ላይ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኗል።

አንዳንዶች የፖሊስ ውሳኔ ከበርካታ መቶ ዓመታት በፊት ነገሥታት ያደርጉት የነበረ የቅጣት አይነት እንደሆነ በመግለጽ የተቃወሙት ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት የሚደረጉ ውሳኔዎችን እንደሚቀበሉ ገልጸዋል።

ሌላኛው የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የሆነው ቤይጂንግ ኒውስ መሰል እርምጃዎች የሕግ የበላይነትን እንዲሁም የፖሊስ ኃላፊነትን ያልተከተለ እንደሆነ ዘግቧል።

የከተማዋ የሕዝብ ደኅንነት ቢሮ በበኩሉ የፖሊስን እርምጃ ደግፏል። አክሎም እርምጃው ወንጀል እና የሥነምግባር ጥሰት የፈጸሙ ሰዎችን በተገኙበት ቦታ የመቅጣትና የማስተማር ሂደት እንደሆነ ገልጿል።

በአውሮፓውያኑ 2007 የቻይና ባለሥልጣናት የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ሰዎች በተመሳሳይ በህዝብ መሀል በየጎዳናው እንዲመላለሱ የሚያደርገውን ሕግ መሻራቸው ይታወሳል።