በአውስትራሊያ በምርመራ ማዕከል ስህተት ብዙዎች ኮሮናቫይረስ እንደሌለባቸው ተነገራቸው

ቤተ ሙከራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአውስትራሊያ ሲድኒ ውስጥ በሚገኝ የምርመራ ማዕከል በተፈጠረ ስህተት ምክንያት ኮሮናቫይረስ ያለባቸው ሰዎች ከቫይረሱ ነጻ ናችሁ ተባሉ።

በሲድኒ በርካቶች በወረርሽኙ እየተያዙ ቢሆንም በምርመራ ማዕከሉ ስህተት ሳቢያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቫይረሱ እንደሌለባቸው ተነግሯቸዋል።

ስህተቱ የተፈጠረው በፈረንጆች ገና ሰሞን ነው። ምርመራ የተደረገላቸው ሰዎች ናሙና ሲፈተሽ በተፈጠረ የመረጃ ስህተት ሳቢያ ውጤቱ የተሳሳተ መሆኑም ተገልጿል።

አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ኦሚክሮን መስፋፋት ከጀመረ ወዲህ በአውስትራሊያ በወረርሽኙ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።

ብዙ ሰዎች ምርመራ እያደረጉ መሆኑ የመረጃ መጨናነቅ መፍጠሩም ተጠቁሟል።

ቫይረሱ እያለባቸው የለባችሁም የተባሉት ሰዎች በዓመት በዓል ሰሞን ቫይረሱን ወደ ወዳጅ ዘመዶቻቸው አስተላልፈው ሊሆን እንደሚችል ተሰግቷል።

ሲድፓዝ የተባለው የምርመራ ማዕከል ለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ ጠይቋል።

ወደ 886 ሰዎች የምርመራ ውጤታቸው የተሳሳተ የሆነው ባልተጠበቀ ሁኔታ ምርመራ ያደረጉ ሰዎች ቁጥር በመጨመሩ መሆኑን ቤተ ሙከራው ገልጿል።

400 ሰዎች የገና ዕለት ቫይረሱ እንደሌለባቸው ቢነገራቸውም በነጋታው ግን ትክክለኛ ውጤታቸው ተገልጾላቸዋል።

ከእነዚህ ሰዎች በኋላ ተጨማሪ 486 ሰዎች ቫይረሱ ቢኖርባቸውም በስህተት የለባችሁም መባላቸውን ምርመራ ማዕከሉ ይፋ አድርጓል።

የሰዎች ናሙና በዲጂታል መንገድ ይመረመር እንደነበረና ከሰሞኑ ግን በሰው ኃይል ምርመራ መደረግ በመጀመሩ የተፈጠረ ክፍተት እንደሆነ ተገልጿል።

ከዚህ በኋላ ወደ ዲጂታል ምርመራ እንደሚመለሱም አክለዋል።

ስታፋኒ ኮሎና የተባለች የሲድኒ ነዋሪ ቫይረሱ እያለባት የለብሽም ከተባለች በኋላ ከቤተሰቦቿ ጋር እንደተገናኘችና ቫይረሱን አስተላልፋባቸው ሊሆን እንደሚችል ተናግራለች።

የጤና ሚኒስትሩ ብራድ ሀዛርድ ስህተቱ የተፈጠረው ምርመራ የሚያደርጉ ሰዎች ቁጥር በጣም በመጨመሩ ነው ብለዋል።

የቫይረሱ ስርጭት ከጨመረ ወዲህ በየቀኑ ምርመራ የሚደረግላቸው ሰዎች ቁጥር ከ117,000 ወደ 145,000 አድጓል።