የስፓይደር-ማን ተከታይ ፊልም በኮሮና ዘመን ብዙ ዶላር በማጋበስ ክብረ ወሰን ሰበረ

ስፓይደር ማን

የፎቶው ባለመብት, Sony Pictures

የስፓይደር ማን ተከታታይ ፊልም አካል የሆነው 'ኖ ዌይ ሆም' የተሰኘው ፊልም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዘመን ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያጋበሰ የመጀመሪያው ፊልም ሆኗል።

ስፓይደር-ማን፡ ኖ ዌይ ሆም እየተገባደደ ባለው የፈረንጆቹ ዓመት ከፍተኛ ገቢ ያስገኘ ፊልምም ሆኗል።

ቻይና ውስጥ የተሠራው የኮሪያ ጦርነትን የሚተርከው 'ዘ ባትል ኦፍ ሌክ ቻንግጂን' የተሰኘው ፊልም 905 ሚሊዮን ዶላር ቢያስገባም ስፓይደር ማንን በገቢ ሊረታ አልቻለም።

ኮምስኮር የተባለው የፊልም ገቢ አሰባሳቢ ድርጅት እንደሚለው ከዚህ በፊት ከሲኒማ 1 ቢሊዮን ዶላር መዛቅ የቻለው 'ስታር ዋርስ፡ ዘ ባትል ኦፍ ስካይዎከር' የተሰኘው ፊልም ነበር።

ነገር ግን ይህ ፊልም ከወጣበት 2019 (እአአ) ጀምሮ ባለፉት ሁለት የወረርሽኝ ዓመታት የትኛውም ፊልም ይህን ያህል ገቢ አላስገባም።

የምዕራባዊያኑ ገና በተከበረበት ባለፈው ቅዳሜ ስፓይደር ማን የተሰኘው ፊልም ከሲኒማ ብቻ 1.05 ቢሊዮን ዶላር ማጋበሱ ተሰምቷል።

ሶኒ እና ዲዝኒ የተሰኙት ፊልም አምራቾች በትብብር የሠሩት ይህ ፊልም በተለቀቀ በሁለት ሳምንታት ውስጥ ነው ክብረ ወሰን የሰበረው።

ምንም እንኳ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ኦሚክሮን የተሰኘው የኮቪድ-19 ዝርያ በዓለም ዙሪያ ቢሰራጭም የፊልም ወዳጆችን ሲኒማ ከመግባት አላገዳቸውም።

ይህ ፊልም በአሁኑ ወቅት የዓለማችን ግዙፏ የፊልም ገበያ በሆነችው ቻይና ገና አልተለቀቀም።

'ስፓይደር-ማን፡ ኖ ዌይ ሆም' በተሰኘው ፊልም ላይ ቶም ሆላንድ እንደ ፒተር ፓርከር፤ ዘንደያ እንደ ኤምጄ ሆነው ይተውናሉ። በተጨማሪም ቤኔዲክት ከምበርባች ዶክተር ስትሬንጅን ሆኖ ይጫወታል።

2019 የተለቀቀው ስፓይደር ማን፡ ፋር ፍሮም ሆም በተመሳሳይ ርዕስ ከወጡ ፊልሞች ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ በማስገባት የመጀመሪያው ነበር። አልፎም ይህ ፊልም በጠቅላላው ከሲኒማ በተገኘ ገቢ 1.132 ቢሊዮን ዶላር በማስገኘት ብዙ ዶላር ያስገባ ፊልም ሆኖ ይመራል።

ዲዝኒ፣ ማርቭል ስቱዲዮስና ሶኒ የተሰኙት ግዙፍ ፊልም አምራች ኩባንያዎች ይህን ታዋቂ የፈንጠዝያ ዓለም ፊልም በጋራ ለማምረት የተስማሙት በ2015 ነበር።

ስፓይደር ማን ክብረ ወሰኑን ከመበጣጠሱ በፊት ጄምስ ቦንድ 'ኖ ታይም ቱ ዳይ' የተሰኘው ፊልም 774 ሚሊዮን ዶላር በመሰብሰብ ድኅረ-ኮቪድ ያለውን የሲኒማ መንደር ገቢ ይመራ ነበር።