በአሜሪካ እና በፈረንሣይ ከፍተኛው ዕለታዊ በኮቪድ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ተመዘገበ

ጭምብል ያደረጉ ሁለት ሴቶች ፓሪስ ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኦሚክሮን ዝርያ መስፋፋቱን በቀጠለበት በዚህ ወቅት አሜሪካ እና ፈረንሳይ ወረርሽኙ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ዕለታዊ ከፍተኛ በኮቪድ የተያዙ ሰዎች ቁጥር መመዝገባቸውን አስታወቁ።

እንደ አሜሪካ የበሽታ መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) ከሆነ አገሪቱ ሰኞ ዕለት ብቻ ከ440,000 በላይ አዳዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን መዝግባለች።

ባለሥልጣናቱ በፈረንጆቹ የገና በዓል ምክንያት በተከሰቱ መዘግየቶች የተመዘገበው ቁጥር "ከልክ በላይ" ጨምሮ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።

ፈረንሳይ በበኩሏ በአውሮፓ ደረጃ ዕለታዊ ከፍተኛ በኮቪድ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር አስመዝግባለች። በዚህም ማክሰኞ ዕለት 179,807 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ታውቋል።

የፈረንሳዩ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ኦሊቪየር ቬራ ቀደም ብለው "ሁሉም ጠቋሚዎች እንደሚያሳዩት ፈረንሳይ በጥር ወር መጀመሪያ ላይ በየቀኑ እስከ 250,000 የሚደርሱ ሰዎች በቫይረሱ ሊያዙ እንደሚችሉ" አስጠንቅቀዋል።

የአሜሪካው የሲዲሲ ቃል አቀባይ ለፖሊቲኮ የዜና ድረ ገጽ በገና ወቅት በምርመራ መዘግየት እና በምርመራ ማዕከላት መዘጋት ምክንያት ቁጥሩ "ከልክ በላይ" ጨምሮ ሊሆን ይችላል ብለዋል።

በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን የሚገልጸው ቁጥር "[ከፈረንጆቹ] አዲሱ ዓመት በኋላ የበለጠ የተረጋጋ ይሆናል" ሲሉ ጨምረው ገልጸዋል።

ጣሊያን፣ ግሪክ፣ ፖርቱጋል እና እንግሊዝም ማክሰኞ ዕለት ክብረ ወሰን የሆነ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥርን አስመዝግበዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት በሳምንታዊ የኮቪድ መረጃው የኦሚክሮን ዝርያ የጋረጠው አደጋ "በጣም ከፍተኛ ነው" ሲል አስጠንቅቋል።

ማክሰኞ በወጣው መረጃ መሠረት ካለፈው ሳምንት ማብቂያ በፊት ከነበረው አንጻር በአውሮፓ በሁሉም የቫይረሱ ዝርያ ዓይነቶች የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በ57 በመቶ ጨምሯል። በአሜሪካ ደግሞ ቁጥሩ በ 30 በመቶ አድጓል።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት የኦሚክሮን ዝርያ ከዴልታ አንጻር መለስተኛ የሚባል ህመም የሚያስከትል ሲሆን ከ30 በመቶ እስከ 70 በመቶ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ወደ ሆስፒታል የመግባት ዕድላቸው ዝቅተኛ ነው። ነገር ግን በከፍተኛ ደረጃ ተላላፊ በመሆኑ ሆስፒታሎችን ሊያጨናነቅ ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።

የሲዲሰ መረጃ መከታተያ እንደሚያሳየው ሰኞ ዕለት ብቻ ቁጥሩ በ441,278 ከፍ ብሏል። ይህም እስካሁን በኤጀንሲው ከተዘገበው ከፍተኛው ዕለታዊ ቁጥር ሆኗል። የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት የቫይረሱ አማካይ የስርጭት መጠን ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የኤጀንሲው ባለሥልጣናት በአሜሪካ የኦሚክሮንንን የመከላከል ብቃት ቀደም ሲል እንደተዘገበው ከ73 በመቶው ይልቅ 59 በመቶ ነው ሲሉ ከልሰዋል።

የሕክምና ፖሊሲ ባለሙያ የሆኑት ስኮት ጎትሊብ አዲሱ መረጃ በአሜሪካ "ሆስፒታል ከያዙ ሰዎች ከፍተኛውን በመያዝ" የዴልታ ልዩነት እየመራ መሆኑን ሊጠቁም ይችላል ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፈረንሳይ ማክሰኞ ዕለት ከፍተኛ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን መመዝገቧን አስታውቃለች።

የፈረንሳይ ሆስፒታል ፌዴሬሽን "በጣም አስቸጋሪዎቹ ሳምንታት ገና ከፊታችን ናቸው" ብሏል።

አገሪቱ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ አዲስ ገደቦችን ጥላለች። ከእነዚህ ገደቦች መካከልም ከቤት መስራት የሚችሉ በሳምንት ቢያንስ ለሦስት ቀናት ከቤት እንዲሰሩ የሚያስገድድ ሕግን ያካተተ ነው።

የአገሪቱ ሦስተኛ ዙር የማጠናከሪያ ክትባት የጨመረች ሲሆን እስካሁን ከ23 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ይህንን ክትባት ወስደዋል።

ፓሪስ ፣ ለንደን እና በርሊንን ጨምሮ በርካታ ከተሞች ኦፊሴላዊ የአዲስ ዓመት በዓል ሥነ ሥርዓቶችን ሰርዘዋል። አንዳንድ አገራት በአገር አቀፍ ደረጃ ገደቦችን ለመጣል ብዙም ፍላጎት ያላቸው አይመስሉም።

በፈረንሳይ እና በእንግሊዝ ያሉ ሰዎች በራሳቸው እንዲወስኑ ሲጠየቁ የስፔን ርዕሰ መዲና ማድሪድ በፑየርታ ዴል ሶል አደባባይ የሚሰበሰቡ ሰዎችን ቁጥር በመቀነስ የበዓሉን ሥነ ሥርዓት እንደምታከናውን ገልጻለች።

ጣሊያን ደግሞ ከቤት ውጪ የሚደረጉ ዝግጅቶችን እና የምሽት ክለቦችን አግዳለች። በግል በሚደረጉ መሰባስቦች ላይ ግን ምንም እነት ገደቦች አልተቀመጡም።