ለገና በዓል የሚኖረው እንቅስቃሴ የአዲሱን የኦሚክሮን ቫይረስ መስፋፋት ሊያባብሰው ይችላል ተባለ

ዶ/ር ፋውቺ ከፕረዝዳንት ባይደን ጋር

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ዶ/ር ፋውቺ ከፕሬዝዳንት ባይደን ጋር

የገና በዓልን ተከትሎ ከቦታ ቦታ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ለአዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ኦሚክሮን መስፋፋት ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ የአሜሪካ የተላላፊ በሽታዎች ባለሙያዎች አስታወቁ። ይህ ደግሞ ሁለት ዙር የተከተቡ ሰዎችንም ጭምር እንደሚያካትት አሳስበዋል።

ዶክተር አንቶኒ ፋውቺ ከኤንቢሲ ጋር ቆይታ ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት "ጥርጥር የለውም፤ ኦሚክሮን በሚያስገርም ፍጥነት መስፋፋት ይችላል" በማለት አስጠንቅቀዋል።

ዶክተር ፋውቺ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ አሜሪካ መንግሥትን የሚያማክሩ ሲሆን አዲሱ ኦሚክሮን በመላው ዓለም በሚያስፈራ ፍጥነት እየተስፋፋ መሆኑን ጠቁመዋል።

እራሱን ለውጦ የመጣው ኦሚክሮን በአጭር ጊዜ ውስጥ በፍጥነት መሰራጨቱ አገራት ጠበቅ ያሉ እርምጃዎችን እንዲወስዱ አስገድዷቸዋል።

አውሮፓ ውስጥ ፈረንሳይ እና ጀርመን የጉዞ እገዳዎችን በፍጥነት ተግባራዊ ያደረጉ ሲሆን፣ ኔዘርላንድስ ደግሞ የገና በዓልን ተከትሎ ስርጭቱን ለመቆጣጠር በማሰብ ጠበቅ ያለ የእንቅስቃሴ ገደብ አስቀምጣለቸ።

በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥታት ተጨማሪ የመከላከል ኃይል የሚሰጡ ሦስተኛ ዙር የማጠናከሪያ ክትባት ዘመቻዎችን እያካሄዱ ሲሆን፣ የዘርፉ ተመራማሪዎችም ቢሆኑ አገራት ይህን መሰል እርምጃ እንዲወስዱ ከጅምሩ ሲወተውቱ ነበር።

እሁድ ዕለት ዶክተር ፋውቺ እንዳሉት በሚያስፈራ ፍጥነት እየተሰራጨ የሚገኘው ኦሚክሮን አሜሪካ ውስጥ በርካቶችን ሊጎዳ እና የአገሪቱን የጤና ሥርዓት ሊፈትን የሚችል ነው።

"ነገሮች አሁን እየሄዱ ባሉበት የሚቀጥሉ ከሆነ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ሆስፒታሎቻችን በጣም ሊጨናነቁ የሚችሉበት እድል አለ'' ብለዋል።

የጤና አማካሪው አክለውም ዜጎች የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማስኮችን በትክክል በመጠቀምና አካላዊ ርቀታቸውን በመጠበቅ የቫይረሱን ስርጭትን በእጅጉ መቀነስ እንደሚችሉ ገልጸዋል። አክለውም አሜሪካውያን በፍጥነት ክትባቱን እንዱወስዱ አሳስበዋል።

"ቫይረሱ ከሚያስከትለው ህመም አንጻር ሁለት ዙር ክትባቱን የወሰዱ ሰዎች እና ተጨማሪ ሦስተኛ ዙር ክትባቱን ያገኙ ሰዎች መካከል ከፍተኛ ልዩነት አለ። ያልተከተቡ ሰዎች ላይ ደግሞ ጉዳቱ በእጅጉ ይጨምራል'' ብለዋል።

አርብ ዕለት በዋይት ሐውስ በነበረው መግለጫ ላይ ደግሞ ዶክተር ፋውቺ ያልተከተቡ ሰዎች በኦሚክሮን የመያዛቸው ዕድል ከፍተኛ መሆኑንና ሆስፒታል እስከመግባት ሊደርሱ እንደሚችሉም አስጠንቅቀዋል።

"የቫይረሱ በከፍተኛ ፍጥነት መሰራጨት በጣም አሳስቦናል። ሙሉ በሙሉ ክትባቱን የወሰዱ ሰዎች በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው የሚገኙት" ብለዋል።

ከአሜሪካ ዜጎች 73 በመቶ የሚሆኑት ቢያንስ አንድ ጊዜ ክትባቱን የወሰዱ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ደግሞ 30 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው ሦስተኛ ዙር የማጠናከሪያ ክትባት የወሰዱት።

እስካሁን አሜሪካ ውስጥ በኮሮናቫይረስ ከተያዙ ሰዎች መካከል 3 በመቶ የሚሆኑት በኦሚክሮን መጠቃታቸውን የሲዲሲ ሪፖርት የሚያመለክት ሲሆን አብዛኛዎቹ ደግሞ በኒው ዮርክ ግዛት እንደሆነ ተገልጿል።

በአሜሪካ በአጠቃላይ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ከ800 ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን በአጠቃላይ ደግሞ ከ50 ሚሊየን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል።