ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
'ጥቅምት 24 ወታደሮቿ ብቻ ሳይሆኑ ኢትዮጵያም ተገድላለች' ፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በግፍ የተገደሉት የአገሪቱ ወታደሮች ብቻ ሳይሆኑ ኢትዮጵያም በዕለቱ ተገድላለች አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ከአንድ ዓመት በፊት የህወሓት ኃይሎች በሰሜን ዕዝ ላይ ፈጽመውታል የተባለውን ጥቃት ለማሰብ አዲስ አበባ ውስጥ በተዘጋጀ ሥነ ሥርዓት ላይ ነው።
"የኢትዮጵያ ሕዝቦች በዕለቱ ተጨፍጭፈዋል። እኛ ዛሬ በሕይወት ያለን፤ እኔም ወታደር ነኝ የምንል የኢትዮጵያ ልጆች፤ . . . አገራችንን ለመበተን የተነሱትን ኃይሎች በእጅ የማንል መሆናችንን . . . ዳግም ቃል ኪዳን የምንገባበት ዕለት ነው" ብለዋል።
በአገር መከላከያ ሚንስቴር ዋና መስሪያ ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ በተካሄደው ሥነ ሥርዓት ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም ጄነራል ብርሃኑ ጁላ፣ ምክትል ኤታማዦር ሹም አበባው ታደሰ እና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ተገኝተዋል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ ከአንድ ዓመት በፊት በህወሓት ኃይሎች በፈጸመባቸው ጥቃት ሕይወታቸው ላለፈ የአገሪቱ ሠራዊት አባላትን ለማሰብ የህሊና ጸሎት እና የሻማ ማብራት መርሃ ግብር ተካሂዷል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ዕለቱን በማሰብ በማኅብራዊ የትስስር ገጻቸው ላይ ባጋሩት ጽሑፍ፤ "አምና ጥቅምት 24 ግፍ የተፈጸመባቸው ጀግኖቻችን ታሪክ ፈጽሞ የሚረሳ አይደለም። . . . ዛሬ የቆምነው ለእኛ ሲሉ የግፍ ጽዋን በተጎነጩ ጀግኖቻችን አጥንት ላይ ነው። እነዚያ ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጆች "ከወገኔ በፊት እኔ ልቅደም" ብለው ደማቸውን ለአፈር፣ ሥጋቸውን ለአሞራ ባይሰጡ ኖሮ የዛሬው ቀን ዛሬን ባልመሰለ ነበር" ብለዋል።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት 24 የተቀሰቀሰው ጦርነት አስካሁን መቋጫ ያላገኘ ሲሆን ጦርነቱ ከትግራይ ክልል ባሻገር በአማራና በአፋር ክልሎች ውስጥ እየተካሄደ ይገኛል።